አዲስ አበባ፡- ከ600 ሺ በላይ “ሀስ” የተባለ የአቮካዶ ዝርያን ለአርሶ አደሮች ለማሰራጨት መዘጋጀቱን የኦሮሚያ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የኦሮሚያ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ሀላፊና የቡናና ፍራፍሬ ዘርፍ ቡድን መሪ አቶ መሀመድሳኒ አሚን በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ክልሉ ለአትክልት ምርት ምቹ ቢሆንም ትኩረት ተነፍጎት የቆየ በመሆኑ አርሶ አደሩ ሳይጠቀም ቢቆይም በቅርቡ ትኩረት በመሰጠቱ ፍራፍሬ በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆን በትጋት እየሰራ ነው፡፡
አቶ መሀመድሳኒ ከስድስት ወር በፊት በምስራቅ ሸዋ ዞን በአዳ ወረዳ በ105 ሄክታር ላይ 45 ሺ የአቮካዶ ችግኞች 219 አርሶ አደሮች በክላስተር እንዲለማ ተደርጎ ከሰማንያ አምስት በመቶ በላይ የሆነው መፅደቁን ጠቅሰው፤ በተያዘው አመት መጨረሻ ላይ ለ12 ዞኖች በማከፋፈል በርካታ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
እንደ አቶ መሀመድሳኒ ገለፃ፤ የሚሰራጨው የአቮካዶ ዝርያ ትልልቅ ፍሬ የሚይዝና የፕሮቲን መጠኑ ከፍተኛ በመሆኑ በአለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ ነው፡፡ ወደፊት ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት እጥረቱን ይፈታል፡፡ ዘሩን ለአርሶ አደሩ ከማሰራጨት ባለፈ ባለሙያ በመመደብ የጉድጓድ አቆፋፈር߹ ተከላና እንክብካቤ ላይ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በዝናብ እጥረት ምክንያት እንዳይደርቅ በመስኖ እንዲጠቀሙ ለማድረግ የውሃ ፓምፖች በስፋት ለአርሶ አደሩ እየቀረበ ነው ፡፡
አቶ መሀመድሳኒ ለአርሶ አደሮች ሲደረግ የነበረውን ድጋፍና ማበረታቻ በማጠናከር ምርቱ ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሌሎች ክልሎች ተሞክሮ በመውሰድ የአርሶ አደሩን ህይወት መለወጥ እንዲችሉ ድጋፍ እንደሚደረግና በቀጣይም በርካታ አርሶ አደሮች በዘርፉ እንዲሰማሩ የሚያበረታታ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 16 /2012
ሞገስ ፀጋዬ