በአፍሪካውያን መካከል ለሚካሄድ ድርድር አትላንቲክን አቋርጦ ዋሽንግተን ዲሲ ድረስ መሄዱ አስፈላጊ አይደለም። ውይይቱን እዚሁ አፍሪካ ውስጥ ማካሄድ የተሻለ ነው። የአፍሪካ ህብረት ዋነኛው መፈክር “ለአፍሪካውያን ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚል ነው። ስለዚህ አፍሪካውያኑ ኢትዮጵያውያን፤ ግብፃውያንና ሱዳኖች እራሳቸው ተወያይተውና ተደራድረው ችግሩን መፍታት ይችላሉ።
በእርግጥም ለአፍሪካውያን የሚያሻው አፍሪካዊ መፍትሔ ብቻ ነው።ቀድሞ ነገር አስራ አንዱም የናይል ተፋሰስ አገራት አፍሪካ ውስጥ ያሉ ናቸው።መጠነ ሰፊ ችግር ቢያጋጥም እንኳ በድርድሩ ሊሳተፉ፤ ሊወያዩና የጋራ መፍትሔ ሊያስቀምጡ የሚገባቸው እነዚህ አገራት እንጂ፤ የተፋሰሱ አካል ያልሆኑ፤ ጭራሽም በአህጉሩ የሌሉና ከአገራቱ የራቁ ወገኖች መሆናቸው ፍፁም ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ነው።ሁሌም ቢሆን፤ ጉዳዩ የሚመለከተው እና የሚያሳስበው በቅርብ ያለው ይቀድማል።
አባይ የግብፅ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም ሃብት ነው። እንዲያውም ከአናት ያለችውና ከውሃው ከ85 በመቶ በላዩን የምታበረክተው ኢትዮጵያ ናት።ምንም እንኳን አናት ላይ የተቀመጠችው ኢትዮጵያ የአባይ ምንጭ ብትሆንም ግብፅን የመጉዳት ፍላጎትም ሆነ ሀሳብ የላትም።ግብፅ ምን ያህል በአባይ ላይ ጥገኛ እንደሆነች ትገነዘባለች። እናም ራሷን ወደልማት እያስገባች ይህች አገርም ሆነች ህዝቦቿ እንዲራቡም ሆነ እንዲጠሙ በፍፁም አትፈልግም።ነገር ግን ሊረሳ የማይገባው ጉዳይ፤ ኢትዮጵያም የራሷን በሚሊዮን የሚቆጠርና በኩራዝ ጭስ የሚጨናበሰውን ህዝቧን የኤሌክትሪክ ብርሀን እንዲያገኝ የማድረግ ታሪካዊ ሀላፊነት ተሸክማለች። ህዝቡም በወንዙ የመልማትና የመጠቀም መብቱ ሊከበርለት ይገባል።
ግብፅም ይህንን መገንዘብ፤ ለተግባራዊነቱም አብራ መቆም ይጠበቅባታል።እናም የግብፅ መስገብገብ ተገቢ አይደለም። እኔ ብቻ ልጥገብ፤ ኢትዮጵያ እንደደቀቀች ትኑር ማለት አይገባም። ይህ ትክክል አለመሆኑን የግብጽን ሕዝብ ጨምሮ መላ አፍሪካውያን ሊገነዘቡት ይገባል።
የሁሉም ሃብት የሆነውን የአባይ ወንዝ “የኔ የፈጣሪ ስጦታዬ ነው” ብሎ አጉል ተረት ይዞ ግትር ማለት ተገቢ አይደለም።“ያለ እኔ ይሁንታ ጠብታ ውሃ የትኛውም አገር መጠቀም አይችልም” ብሎ ድርቅ ማለትም ዘመናዊነት አይደለምና አያዋጣም። የሃብቱ ባለቤት የሆነ ሁሉ በሌሎቹ አገራት ላይ ጉልህ ጉዳት እስካላስከተለ ድረስ በተገቢው መጠን ኃብቱን ይጠቀማል። ዓለም አቀፍ ህግ የሚፈቅደውና ኢትዮጵያም እያደረገች ያለችው ይህንኑ ነው። ኢትዮጵያ ግድቡን ልገንባ ስትል መነሻዋ ግብፅን መጉዳት አይደለም።ዓላማዋ ህዝቧን ከድህነት ማውጣት ነው።በዚህ ሂደት ግብፅም ሆነች ሱዳን ጉልህ ጉዳት እንደማይደርስባቸው ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ቃል የገባች ሲሆን፤ ይህንን ቃሏንም ታከብራለች።
የቃሏ መነሻ የህዳሴው ግድብ ውሃው ተርባይኑን መትቶ ከማለፍ ውጪ የሚሰራው የለውም። ዞሮ ዞሮ ውሀው ወደሱዳንና ወደግብፅ መውረዱ የማይቀር ነው።ይልቁኑ አፈሳሰሱ ከዓመት እስከ ዓመት የተስተካከለ ሆኖ ከጎርፍ አደጋም የሚታደጋቸው ነው።ይህንን ለመቀበል ግብፅ ልቧን መክፈት አለባት።
ኢትዮጵያ የግድቡን መገንባት ለግብፅ ግልፅ ከማድረግ አልፋ በአካል አስጎብኝታለች። ብዛት ያላቸውን ድርድሮችም አድርጋለች።ያ ሁሉ ሲሆን ግብፅ ሃሳቧን በተለያየ መልኩ እየቀያየረች፤ የነበረውን ስምምነት እያደፈረሰች ትረብሻለች። እልህ አስጨራሽ ድርድር ሲደረግ ኢትዮጵያ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች በትዕግስትና በእምነት ምላሽ ስትሰጥ ቆይታለች።
አሁን ግን በሃብቷ የመጠቀም መብቷን በመጋፋት ሉዓላዊነትን በሚፈታተን መንገድ ጫና ለማሳደር ጥረት እየተደረገ ነው። በተለይ ሰሞኑን ግብፅ አሜሪካንን ተጠቅማ የኢትዮጵያን እጅ ለመጠምዘዝ የሄደችበት መንገድ እጅግ አሳዛኝና ተቀባይነት የሌለው ነው።አሜሪካ ከታዛቢነት የዘለለ ተሳትፎ በማድረግ ያልተገባ ውሳኔ እንዲፈረም እስከማስገደድ የደረሰ ጣልቃ ገብነት መፈጸሟም ያስተዛዝባል።
አሁን ግን መፍትሔው የሚመነጨው ከአፍሪካውያን ነው።ሁለቱንም በእኩል አይን በማየት መደራደር ያለባቸው አፍሪካውያን ናቸው። ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ደቡብ አፍሪካ በማምራት የአፍሪካ ህብረት የወቅቱን ሊቀመንበር አነጋግረዋል። እርሳቸውም ለማደራደር ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። ስለዚህ ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ሥር መቀጠል አለበት።
ለአፍሪካውያን ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለው መፈክር ተግባራዊነቱ በአባይ ቢጀምር ጥሩ ነው።ለአፍሪካውያን ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ ከአፍሪካውያን ይመነጫል። አሁንም ኢትዮጵያ፤ ሱዳንና ግብፅ ወደ ድርድር መመለስ አለባቸው። መፍትሄው ድርድርና ድርድር ብቻ ሲሆን፤ አደራዳሪዎቹ ደግሞ አፍሪካ እና አፍሪካውያን ብቻ ይሆናሉ። ማንም ጉልህ ጉዳት አይደርስበትም። ሁሉም ተገቢውን ብሔራዊ ጥቅም ያገኛሉ። መፍትሔውም ይህ ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 14 /2012