
አዲስ አበባ:- ዓለም አቀፍ ስጋት የሆነውን የኖቭል ኮሮናን ቫይረስ ስርጭት መቆጣጠር እንዲቻል የግል ፍላጎቶቻችንን ለጊዜው ገታ ማድረግ እንደሚገባ ዶክተር አሰፋ አድማሴ ገለጹ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር አሰፋ አድማሴ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሆነውን የኖቭል ኮረና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እያንዳንዱ ግለሰብ ለጊዜው የግል ፍላጎቱን ገታ በማድረግና ቆም ብሎ በማሰብ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
አሁን ላይ የገጠመን ችግር በጣም አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ ውስብስብና በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ወረርሽኙ ቢከሰት ለመቆጣጠር አዳጋች መሆኑን የገለፁት ዶክተር አሰፋ፤ ወረርሽኙ ቢከሰት በጤና፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ እንቅስቃሴያችን ላይ የሚያስከትለው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ጥንቃቄ ሳይለየን የግል ፍላጎቶቻችንን ለጊዜው ገታ የምናደርግበት ፈታኝ ወቅትነው ሲሉ ጠቁመዋል።
የኖቭል ኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ እንደ ህብረተሰብ የመቆምና ያለመቆም፤ እንዲሁም የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ውስጥ የሚከትት በመሆኑ፤ የግል ፍላጎታችንን ጨምሮ እንቅስቃሴያችን በሙሉ በተለመደው መልኩ መቀጠል የለበትም። በተጨማሪም፤ ከዚህ ችግር ለመውጣት ብቸኛ አማራጭ ተብለው ከመንግስት የሚተላለፉ መልዕክቶችን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ዓለም አቀፉን ወረርሽኝ ተከትሎ የገጠመን ችግር ፈታኝ መሆኑን ያስታወሱት ዶክተር አሰፋ፤ የችግሩ አሳሳቢነት እንደ ህብረተሰብ የመቀጠል እና ያለመቀጠል ጥያቄ በመሆኑ የግለሰቦች የግል ፍላጎት መገታት አለበት እንጂ እያንዳንዳችን የግል ሀብት የምናጋብስበት እና የተለያዩ ፍላጎቶችን የምናሟላበት ወቅት አይደለም ብለዋል።
“በተለይም አንዳንድ ነጋዴዎች ይህን ፈታኝ ወቅት እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመመልከት ፍፁም ሰብዓዊ ያልሆነና እጅግ የሚያሳዝን ተግባር መፈፀማቸው አሳፋሪና አንገት የሚያስደፋ ነው።” ያሉት ዶክተር አሰፋ፤ “ነጋዴው ዛሬ ቢያተርፍ ነገ ሊጠቀምበት አይችልም። ትርፉን ሊጠቀምበት የሚችለው ሰላም ሲኖርና ህብረተሰብ ተረጋግቶ መቆም ሲችል ብቻ ነው።” ያ ካልሆነና ሰላም ከሌለ ግን የበለጠ ቀውስ ይፈጠራል ሲሉ ገልፀዋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በቀዳሚነት የጤና ችግር የሚያስከትል ይሁን እንጂ፤ በቀጣይ ኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ በጣም አስፈሪ መሆኑን በመግለፅ ችግሩ በተለይም “እንደ ኢትዮጵያ በቂ የመጠባበቂያ ክምችት የሌለን፤ ችግሮችን ለመጋፈጥ አቅማችን በጣም ውስን የሆንን አገሮች ላይ አደጋውን የከፋ ያደርገዋል” የሚሉት ዶክተር አሰፋ፤ ወረርሽኙ በጊዜ መፍትሔ ካላገኘ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለው ችግር ወደፊት የሚታይ መሆኑን ተናግረዋል።
የኖቭል ኮረና ቫይረስ ወረርሽኝን አስመልክቶ መንግስት ሊያደርግ የሚችለው የእያንዳንዳችንን አስተዋፅኦ ሊያጎለብቱ የሚችሉ አቅጣጫዎችን ማሳየት እና ማስተማር ሲሆን፤ ህብረተሰቡ መንግስት እና የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር ተግባራዊ በማድረግ እራሱን እና ቤተሰቡን በመከላከል ቫይረሱን ሊቆጣጠረው እንደሚገባ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 14 /2012
ፍሬህይወት አወቀ