
(ኢ.ፕ.ድ)
ዓለምን ምጥ ያስያዘ፤ ህዝቧን ጭንቀት ውስጥ የዶለ፤ የሀያላንን አቅም የተፈታተነ ወረርሽኝ። ከሩቅ ምስራቅ እስከ ምዕራብ መዳረሻ ከሰሜን መነሻ እሰከ ደቡብ አጥናፍ ያለከልካይ በወራት ጊዜ ውስጥ ያዳረሰ የወቅቱ የዓለማችን ስጋት የሆነው ወረርሽኝ ኮቪድ-19 ። በዚህ ያልተጎዳ፤ ያልተነካ ሰብዓዊ ፍጡር ስለመኖሩ አጠራጣሪ ሆኗል።
በሳይንሳዊ መጠሪያዊ ኮዲቪ19 የተሰኘው ገዳይ ተህዋሲ በ21ኛ ክፍለ ዘመን ተከስቶ ሰለጠንኩ ያለውን የሰው ልጅ፤ ምድርን ተቆጣጠርን ያሉትን ሀያላን አንገት ያስደፋ፤ አደጋ ያጠላ የዘመን ጉዳይ ሆኗል። የዓለም የስልጣኔ ጥግ ላይ ደረስኩ ማለት መፍትሄ አልወለደም። የምድር ሁሉንም ተቆጣጠርኩ ማለት እዚህ ላይ አልሰራም።ለዚህ ማሳያው የእስካሁኑ መግቻ መድሀኒት አለመፈጠር ነው።
ዓለም ችግሩን ለማስቆም ከመከላከል አማራጭ ውጪ እስካሁን መፍትሄ አላበጀም። የዚህ ዘመን መፍትሄዎች ሁሉ ለወረርሽኙ ስርጭትና መገታት አላገለገሉም። መፍትሄ ሆነው ተህዋሲውን ማስቆም አልቻሉም።
ከአድማስ ማዶ መነሻውን አድርጎ አለምን ያዳረሰው፤ የሰውን ልጅ ከዳር እስከ ዳር ያደናበረው ተህዋሲ ተጠቂ የሆነ ግለሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱ አርብ መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ይፋ መሆኑን ተከትሎ ማህበረሰቡ ለመከላከል ይረዳኛል ያላቸውን ቁሳቁሶች ለመሸመት ወደሱቅና ፋርማሲዎች ተመመ።
ይህን የተመለከቱ፤ በጭንቅ አጋጣሚ መክበርን፤ በወገን ስጋት መበልፀግን የፈለጉ ራስ ወዳዶች በቁሶቹ ላይ ከልክ በላይ ዋጋ በመቆለል ህብረተሰቡን መበዝበዝ ጀመሩ። የመግዛት አቅም የሌለው አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል የባሰ ውጥረት ውስጥ ገባ።
ወጣት ሳራ ደበሽ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናት። የኮሮናን ዜና ስትሰማ እንደሌላው ለመከላከያ የሚረዱ መገልገያዎች ለመግዛት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጎፋ አካባቢ ወዳለ አንድ መድሃኒት መሸጫ ታመራለች። በብዙ ሰዎች መሀል ተሹለክሉካ ወደ መደብሩ ብትገባና የፈለገችን ብትጠይቅም አብዛኞቹ እንደሌሉና የተገኘውም ቢሆን ሌላ ጊዜ ከነበረው ዋጋ እጅግ ከፍ አድርገው ይነግራታል።
ኮሮናን ይከላከላል የተባለውን መጠበቂያ ለመግዛት የተሰበሰበውን ሰው የተመለከተችው ሳራ አንድ የመፍትሄ ርምጃ ለመውሰድ አቀደች። ባለሙያዎችን አማክራ በመደብሮች የለም የሚባለው የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ለመስራትና ለህብረተሰቡ በነፃ ለማደል አሰበች፤ እናም አደረገችው።
“ማህበረሰባዊ ኃለፊነቴን የተወጣሁ ለወገኔም ወሳኝ በሆነ ሰዓት ያቅሜን ያበረከትኩ ይመስለኛል በዚህም ደስተኛ ነኝ” የምትለው ሳራ፤ እስካሁን ለአንድ ሳምንት ያህል ብዙ ሰዓታትን የሚወስድና ያላትን ኢኮኖሚ አቅም በፈቀደ ያለ ስስት ለወገን ችግር ለበሽታው መከላከል ትልቅ አስተዋፅዖ ያላቸውን የፊት ጭንብሎችን ሰርታ በነፃ በማከፋፈል ላይ ትገኛለች።
ማህበረሰቡ በሚችለው ሁሉ ወረርሽኙን ለመከላከል የግል ጥረቱን ካጠነከረ ብዙም ጉዳት ሳያደርስ መከላከል እንደሚቻልም ታስረዳለች። ወጣት ሳራ ለመከላከያነት ይጠቅማሉ በተባሉ ቁሳቁሶችና እሱን ተከትሎ የተከሰተው የፍጆታ እቃዎች ላይ ዋጋ የጨመሩ ነጋዴዎች የሀብት ምንጫቸው ማህበረሰቡ መሆኑን አውቀው ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ ትመክራለች።
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ሪቼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባለው አንድ የመድሃኒት መሸጫ ሱቅ ውስጥ “ለኮሮና ቫይረስ መከላከያነት የሚረዱ ቁሳቁሶች ለአረጋዊያንና ለአቅመ ደካሞች በነፃ እናቀርባለን” የሚል ፅሁፍ ከመግቢያው በር ላይ ተለጥፎ ይታያል። ገንዘብ የሌለውና እድሜው ከጎልማሳነት የተሻገረ ማንኛውም ሰው ገብቶ የሚፈልገውን ጠይቆ ተሰጥቶት ሳይከፍል ይወጣል።
አቶ ፍቅሬ ሰይፉ በመድኃኒት መደብሩ ውስጥ ይህንን አገልግሎት ለአንድ ሳምንት ያህል ሲሰጡ ቆይተዋል። “ይህንን ዓለማቀፋዊ ችግር መፍታት የሚቻለው ሰዎች ሁሉ ተባብረውና ተደጋግፈው መሆን አለበት” የሚሉት የመድኃኒት ባለሙያው “እኛም ስርጭቱን ለመግታት የምንችለውን እያደረግን ነው” በማለት በጎ ተግባራቸውን ያስረዳሉ።
“ህብረተሰቡ ከሌለ እኛም ስራዎችን እየሰራን መለወጥ እንችልም፤ ስለዚህ ማህበረሰቡን መጠበቅ ግዴታችን ነው” በማለት በጎ ለመስራት ያነሳሳቸውን ምክንያት ይጠቁማሉ።
ወጣት ቴዎድሮስ ታሪኩ በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ጎፋ የሚባል አካባቢ ነዋሪ ነው።
ግምታቸው ከ150 ሺህ ብር በላይ የሚሆኑ ለኮሮና ወረርሽኝ መከላከያነት የሚረዱ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ለአካባቢው ማህበረሰብ አበርክቷል። ቴዎድሮስ፤ “ኮሮናን ለማስቆም የበኩሌን ነው የተወጣሁት ይህ ደግሞ ማህበራዊ ኃላፊነቴ ነው” በማለት ያስረዳል።
“ይህን ወረርሽኝ መግታት የሁላችንም ግዴታ ነው፤ ስለዚህም ሁሉም ማህበረሰብ የኮሮናን ስርጭት ለመከላከል የበኩሉን ሊወጣ ይገባል” ሲል በማህበራዊ ኑሮ ያልተቆጠበ ተሳትፎና መደጋገፍ ተገቢ መሆኑን ይመክራል።
እነዚህ በግል ተነሳሽነት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የቆረጡ ፀሀዮች በሰሩት መልካም ተግባር ከወገን ፍቅርና ጤንነት ይልቅ የግል ጥቅም ያስቀደሙ ነጋዴዎች ያወረሱትን ጽልመት በእርግጥም አፅድተውልናል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 14 /2012
ተገኝ ብሩ