
ዳሽን ባንክ በአሁኑ ወቅት የዓለም ስጋት የሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለውን ጫና ለመቀነስ ከዛሬ ጀምሮ የተለያዩ የክፍያ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርግ አስታወቀ።
የዳሽን ባንክ ማርኬቲንግ እና የደንበኞች አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አስቻለው ታምሩ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ባንኩ የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከሚያስከትለው የጤና እና ማህበራዊ ጉዳት ባለፈ በአገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለውን ጫና መቀነስ እንዲቻል ከዛሬ መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 60 ቀናት የሚቆይ የተለያዩ የአገልግሎት ማሻሻያዎችን ለደንበኞቹ ማቅረቡን ገልፀዋል።
ዳሽን ባንክ እንደምንጊዜውም ሁሉ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ዝግጁ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በአሁን ወቅትም በዓለም ደረጃ እየተስፋፋ የመጣው የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ በመገንዘብ ባንኩ አንድ መግለጫ ማውጣቱን አስታውሰው፤ በዚህም ባንኩ ቀድሞ ደንበኞች በኤቲኤም ያወጡ የነበረውን የገንዘብ መጠን ከአራት ሺህ ወደ አስር ሺህ ብር ያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል።
ደንበኞች ማንኛውንም ገንዘብ በሚያወጡበት ጊዜም የነበረው የአገልግሎት ክፍያ ሙሉ በሙሉ ነፃ መደረጉንም ተናግረዋል።
በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከዳሽን ባንክ ጋር የሚሰሩ፤ በተለይም አስመጪዎች ኤልሲ ከፍተው በርካታ ሸቀጦችን እና የተለያዩ መገልገያ መሳሪያዎችን ከውጭ የሚያመጡ ሲሆን፤ እነዚህ አስመጪዎች ከዚህ በፊት ኤልሲ ይራዘምልኝ የሚል ጥያቄ ሲያነሱ የሚከፍሉት ክፍያ መኖሩን የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ ዓለም አቀፍ ወረርሽኙን ምክንያት በማድረግ ከዛሬ መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 60 ቀናት ጥያቄው ከመጣ ሙሉ በሙሉ ከክፍያ ነፃ እንደሚሆንም አብራርተዋል።
በተመሳሳይ ከግዥ ማዘዣ ጋር በተያያዘ የይራዘምልኝ ጥያቄ ሲመጣም ዳሽን ባንክ ከዚህ ቀደም ሲያስከፍል የነበረውን 50 በመቶ ክፍያ ነፃ አድርጓል። እንዲሁም፤ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ለሚነሱ የብድር መክፈያ ጊዜ ይራዘምልኝ ጥያቄዎች ደንበኞች ከክፍያ ነፃ ይሆናሉ ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዋናነት የሚተላለፈው በንክኪ እንደመሆኑ ደንበኞች ከንክኪ ነፃ የሆነውን መንገድ “አሞሌ” እንዲጠቀሙም አሳስበዋል።
ባንኩ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአገራችን ከመከሰቱ አስቀደሞ ሰራተኞችን ጨምሮ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እራሱን ከቫይረሱ ለመጠበቅ ማድረግ የሚገባውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አራት መቶ ሺህ ተከታዮች ባሉት የዳሽን ባንክ የፌስ ቡክ ገፅ ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ሲሰራ መቆየቱን የገለፁት አቶ አስቻለው፤ በቀጣይም ባንኩ የቫይረሱን ስርጭት አሳሳቢነት በመከታተል ጉዳቱን ለመቀነስ የሚያደርገውን እንቅስቀሰቃሴ ሁሉ ለመላው ህብረተሰብ የሚያሳውቅ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 14 /2012
ፍሬህይወት አወቀ