
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንደሌሎቹ የዓለም አገሮች ሁሉ በኢትዮጵያ ከተከሰተ ሳምንት ተቆጠረ።ቫይረሱን ለመከላከል ከግለሰብ እስከ ተቋማት ሁሉም በተቻለው መጠን የሚያስፈልገውን ለማድረግ እየተጋ ቢገኝም፤ በየአካባቢው በተለይ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አካባቢ ርቀት አለመጠበቅ ይስተዋላል።
ስድስት ኪሎ አካባቢ የሚገኘው የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ የቅርንጫፍ አራት ጽህፈት ቤት፤ ተገልጋዮች እጃቸውን በመግቢያ በር ላይ ታጥበው ወደ አገልግሎት መስጫ ክፍል ይገባሉ።የአገልግሎት መስጫ ክፍሉ ግን ጠባብና ንፋስ በደንብ የሚያስገቡ መስኮቶች የሌሉትና የታመቀ ሲሆን፤ ብዙዎቹ ተገልጋዮች ተጠጋግተው በመቀመጥ ወረፋ ይጠብቃሉ።
በኤጄንሲው አገልግሎት ፈልገው መምጣታቸውን የገለጹት አቶ ከበደ ገመቹ፤ “ወደ ጽህፈት ቤቱ ስገባ እጄን በውሃና በሳሙና ታጥቤያለሁ። አንዴ ብቻ ሳይሆን ወጥቼ በመግባቴ ሁለት ጊዜ ታጥቤያለሁ” ይላሉ። ፈንጠር ብለው መቀመጣቸው ንኪኪ ለመቀነስ እንደሆነ ተናግረው፤ የህዝብ ብዛት ባለባቸው ተቋማት አካባቢ የሚደረገው ጥንቃቄ እንዳለ ሆኖ መንግሥት ለተወሰነ ጊዜ አገልግሎት ቢያቋርጥ ይሻላል የሚል እምነት እንዳላቸው ይገልፃሉ ።
ሌላኛዋ ተገልጋይ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ባለሙያዋና ውክልና ለመስጠት የመጡት ወይዘሮ ውቢቱ አበረ ናቸው። በመግቢያው በር ላይ እጃቸውን ታጥበው ወደ ውስጥ ሲዘልቁ አልኮል የተሰጣቸው መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ ውቢቱ፤ ባለጉዳይ ብቻ ወደ ውስጥ እንዲገባ መደረጉ ያለው ጭንቅንቅ የሚቀንስ በመሆኑ ፤ ቫይረሱን ለመከላከል ሁሉም ሰው በመገናኛ ብዙሃን የሚነገሩ መልእክቶች በመተግበር ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ይናገራሉ።
የሰነድ ማረጋገጥ ባለሙያዋ ወይዘሮ አለምጸሀይ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ የሰነድ ማረጋገጥን ስራ ከባድ የሚያደርገው የተገልጋዮች ቁጥር እንደየጉዳያቸው የሚወሰን በመሆኑ ነው። በአንድ ጊዜ በርከት ያሉ ተገልጋዮች በአንድ ላይ የሚስተናገድበት ሁኔታ መኖሩን በመግለጽ፤ ቫይረሱ ማንንም ከማንም የማይለይ በመሆኑ ጥንቃቄ መደረግ አለበት ይላሉ።
የሰነዶች ማረገገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ቅርንጫፍ አራት ጽህፈት ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ፍሬህይወት ዘውዴ እንደሚናገሩት፤ የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች በማቅረብ ሠራተኞችና ተገልጋዮች እጃቸውን እንዲታጠቡ ተደርጓል።ስራው ከተገልጋዮች ጋር በቃለመጠይቅ፤ በሰነድ በመቀባበል፤ በእጅ አሻራ የማስፈረም ሂደት ውስጥ የሚያልፍ በመሆኑ ከንክኪ የጸዳ አይደለም ይላሉ።
ወይዘሮ ፍሬህይወት፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተገልጋዮች ብቻ እንዲገቡ በማድረግ፤ የተገልጋዮች ቁጥር ቢቀነስም ወደፊት የሚጨምር ከሆነ ፈጣን መፍትሔ እንደሚወሰድ ይናገራሉ።
ሌላኛውና በካሳንቺስ አካባቢ በሚገኘው የፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴር መካከለኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤትም በየወለሉ ላይ ባሉ የማስታወቂያ ስክሪኖች እና በመወጣጫ ደረጃዎች ላይ ስለኮሮና ቫይረስ መልዕክት የሚያስተላልፉ ፅሁፎች ይታያሉ። በተወሰኑ ፎቆች ላይም ወጣቶች እጅ የሚያስታጥቡ ሲሆን፤ የተገልጋዮች ቁጥር በጣም ጥቂት ነው።
የቢሾፍቱው ነዋሪ ግብር ከፋይ አቶ ሳዲቅ አልማሃዲ፤ ወደመስሪያ ቤት ሲገቡ ከተለጠፈው ማስታወቂያ በተጨማሪ እጃቸውን ታጥበው መግባታቸውን ይናገራሉ።አቶ ሳዲቅ፤ ቫይረሱን ለመከላከል የራሳቸውን ጥንቃቄ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
የኤሌክትሮኒክስ ታክስ ማስተዋወቅ ድጋፍና ክትትል ባለሙያ አቶ ያሬድ መኩሪያ በበኩላቸው፤ ኮምፒውተር የሚጠቀሙ የግብር ከፋዮች አንዳንዶች የማይጠነቀቁ የመኖራቸው ያህል ብዙዎች ጥንቃቄ ያደርጋሉ፤ ይሁንና ህብረተሰቡ የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ አለበት ይላሉ።
የፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴር መካከለኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጁ ወይዘሮ ብርቱካን ግርማ እንደሚናገሩት፤ የኮሮናን ቫይረስ ለመከላከል ለሠራተኛው የንጽሕና መጠበቂያ በማቅረብ፤ የአሻራ ፊርማ በማስቀረት፤ እንዲሁም አሳንሰር (ሊፍት) ባለመጠቀም የጥንቃቄ ሥራ እየተሰራ ይገኛል።ወጣቶችን በፎረም በማደራጀት ግብር ከፋዮች እጃቸውን እንዲታጠቡ መደረጉንም ይናገራሉ።
ግብር ከፋዮች ባሉበት ሆነው ግብር መክፈል የሚችሉ ሲሆን፤ ሲስተሙ እምቢ ያላቸው ብቻ ወደ ጽህፈት ቤት የሚመጡ መሆኑን ስራ አስኪያጇ ይናገራሉ።አሁን ላይ ያለው የግብር ከፋዮች ቁጥር ማነስ በተለምዶ አብዛኛውን ጊዜ ወር በገባ ከ25 በኋላ የሚመጡ መሆኑን ገልጸው፤ የተገልጋዮች ቁጥር ሊጨምር የሚችልባቸውን ጊዜያት ታሳቢ በማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 14 /2012
ወርቅነሽ ደምሰው