አሜሪካ እና ግብፅ የኢትዮጵያን መንግስትና ህዝብ እጅ ለመጠምዘዝ ያደረጉት ሙከራ ህዝቡን አስቆጭቶታል፤ አሁንም የህዳሴውን ግድብ ድጋፍ ለማጠናከር ይህንን የህዝቡን ቁጭት መጠቀም ይገባል ሲሉ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ ተናገሩ።
ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የኢትዮጵያን ጥቅም የማያስከብር ስምምነት እንዲፈረም ግብፅ በአሜሪካን በኩል እጅ ለመጠምዘዝ የተጠቀመችበት መንገድ ህዝቡን ያበሳጨ መሆኑን በማስታወስ፤ ይህን ቁጭት ህዝቡ ለህዳሴው ግድብ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል በሚያስችል መልኩ መጠቀም እንደሚገባ አመልክተዋል።
ፕሮፌሰር ተስፋዬ፤ “ግድቡ በአባይ የመጠቀም መብታችንን ማሳያ ነው” ካሉ በኋላ፤ የእዚህ መብት መከበር ደግሞ የመላ ኢትዮጵያውያን ፍላጎት መሆኑን አስረድተዋል።
“እ.አ.አ በ2017 ያልቃል የተባለው ግድብ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም ከሶስት ዓመት በኋላ በ2020ም አላለቀም። አሁን ይህ ሁሉ ችግር የመጣው የግድቡ ግንባታ በመዘግየቱ ነው።
በተባለበት ጊዜ አልቆ ቢሆን አሁን የመጣው ጣጣ አይመጣም ነበር።” በማለት የተናገሩት ፕሮፌሰር ተስፋዬ፤ ያለፈው አልፏል።
ነገር ግን፤ እስካሁን በህዝቡ ሃይል እዚህ የደረሰው ግድብ የላቀ የህዝብ ድጋፍ ታክሎበት በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የአሜሪካ እና የግብፅ አቋም ያስቆጨውን ህዝብ የበለጠ አነሳስቶ መጠቀም እንደሚገባ አመልክተዋል።
የህዳሴው ግድብ ግንባታ 71 በመቶ መድረሱ የሚታወቅ ሲሆን፤ የውሃው ሙሌት ሥራ በመጪው ክረምት ይጀመራል ተብሏል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 14 /2012
ምህረት ሞገስ