የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በተለያዩ የዓለም አገራት በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ እንደሆነ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ መንግስት ከማህበረሰቡ ጋር ተቀናጅቶ ጥብቅ ከትትልና ቁጥጥር እያደረገ በመሆኑ የስርጭት ሁኔታውን ከቁጥጥር እንዳይወጣ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ። በጤና ጥበቃ ሚንስቴር የአቅርቦት አሰራርና የሎጂስቲክስ ዳይሬክተር አቶ ረጋሳ ባይሳ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በተለያዩ የዓለም አገራት በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ እንደሆነ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ መንግስት ከማህበረሰቡ ጋር ተቀናጅቶ ጥብቅ ከትትልና ቁጥጥር እያደረገ በመሆኑ የስርጭት ሁኔታውን ከቁጥጥር እንዳይወጣ ማድረግ ተችሏል። በመሆኑም ትክክለኛ መረጃ ላይ በመመስረት ሕብረተሰቡ ከመንግስት ጋር ተቀናጅቶ መስራቱን መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ የሚቀርቡ ግብዓቶች በሶስት የሚከፈሉ ናቸው። ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ግብዓቶች(ግላብ፣አልኮል፣የእጅ ንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ሳሙናና ውሃ)፣ ለምርመራ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች(ኪቶችና ሪጀንቶች) እና ለሕክምና የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እንደሆኑ ገልጸዋል።
የግብዓት አቅርቦት ፍላጎት ጨምሯል። በመሆኑም አልኮል 200 ሚሊዮን ሊትር በመሰራጨት ላይ ይገኛል።ተጨማሪ 200 ሺ ሌትር በግዥ ሂደት ላይ ነው። የፊት ማስክ ከበፊት የተሰራጨውን ሳይጨምር ሁለት ሚሊዮን በመሰራጨት ላይ ይገኛል።ሶስት ሚሊዮን በመጠባበቂያ እና 20 ሚሊዮን ደግሞ በግዥ ሂደት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል። መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ መቆጣጠር በሚያስችልበት ደረጃ በሙሉ አቅም እየሰራ ነው።
ሰው ምልክቱ እንደታየበትና ራሱን በሚጠረጥርበት ጊዜ በቅንነት መጥቶ መታከም አለበት፤ለሕብረተሰቡና ለቤተሰቡ ጤንነት ማሰብ እንደሚገባው ተናግረዋል። የሚቀርቡት ግብዓቶች መጠን እንደየ ዓይነታቸው የሚለያዩ እንደሆኑ የገለጹት አቶ ረጋሳ፤ የሕብረተሰቡ አጠቃቀምም ክፍተቶች እንዳሉበት ተናግረዋል። ለምሳሌ፡- ለሕክምና አገልግሎት የሚውለውና መታመማቸው የተረጋገጡ ሰዎችና እነሱን የሚከታተሉ አካላት የሚለብሱትን የፊት ማስክና አፍና አፍንጫ መሸፈኛ በየታክሲው ውስጥም ተለብሶ ይታያል።
በመሆኑም እንደ አገር የቀረቡ ግብዓቶች እጥረት እንዲፈጠር እያደረገ እንደሆነም አብራርተዋል። የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ በበኩላቸው፤ የስርጭቱን ሁኔታ በተመለከተ በሁለት መንገድ ከፍሎ ማየት ተገቢነት እንዳለው ያስረዳሉ። የመጀመሪያው ተጠርጣሪውን እና በዙሪያው ያሉትን ቤተሰቦቹን መርምሮ ሳይሰራጭ እዚያው መቆጣጠር የሚቻልበት መንገድ ነው።
መዘግየት በተፈጠረ ጊዜ ስርጭቱ ሰፍቶ ከቁጥጥር ውጪ የሚሆንበት ሁኔታ ሊገጥም እንደሚችል ገልጸው፤ ሁለተኛው ደግሞ በአቅም ውስንነት ወይም መቆጣጠር ሳይችሉ በመቅረት በኋላ ላይ ግን ወደ ምርመራው ሲገባ ብዙ የተያዙ ሰዎች የሚገኙበት አግባብ እንደሆነ አስረድተዋል። ዶክተሩ እንዳሉት፤በመንግስት በኩል በሶስት ምዕራፎች የተከፈሉ ክትትልና ቁጥጥሮች እየተደረጉ ነው። የመጀመሪያው በመግቢያ በሮች ላይ የሚደረገው የሙቀት ልየታ ነው።
ሁለተኛው በተለያየ ሁኔታ የሙቀት ልየታውን ያለፈ ሰው ሊኖር ይችላል። ለአጭር ጊዜ ከውጭ የመጣን ሰው ክትትል የሚደረግለት ሂደት ይጠቀሳል፤ ወይም ምልክት ያሳየን ሰው 24 ሰዓት ክትትል ለሚያደርገው የተዘጋጀ አካል እንዲያውቅ የሚደረግበት መንገድ ነው። ከተገኘበት ወደማቆያ የሚሄድበት አሰራር እንደሆነም ገልጸዋል። ሌላው ስርጭቱ በአለም ላይ በብዙ አገሮች ስለተዳረሰ በትኩረት ከተለዩት አገራት ውጪ ለመመርመር ይከብዳል። በመሆኑም ሳይመረመር በማለፍ ከሕብረተሰቡ ሊቀላቀል ይችላል።
እክል ሲገጥማቸው ጤና ጣቢያ ይሄዳሉ።እዚያ ተመርምረው ወደ ማቆያ የሚሄዱበት ሶስተኛው መንገድ እንደሆነ አስረድተዋል። እነዚህን ሂደቶች በመከተል ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅት በመሰራቱም ውጤት ተገኝቷል። ለሞት የበቃ የለም። በቀጣይም መንግስት ከሕብረተሰቡ ጋር በትኩረት እንደሚሰራ ዶክተር ኤባ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 ቀን 2012 ዓ.ም
ሙሐመድ ሁሴን