<<የአዲስ አበባ ሳንባ ነው>> እየተባለ ከሚሞካሸው ደን መሃል እና ከታሪካዊቷ እንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን አቅራቢያ የግንባታ ተሽከርካሪዎች ይታያሉ። ሠራተኞች ደግሞ ጸጥ ባለው ጫካ ውስጥ ያለፋታ ሲሰሩ ይታያሉ። የእንጦጦ እና አካባቢው የቱሪስት መዳረሻ ፕሮጀክትን እውን ለማድረግ ቀን ከሌሊት ስራ ላይ ናቸው።
ፕሮጀክቱ ከተጀመረ አራት ወራትን አስቆጥሯል። ወርሐ ታህሳስ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ኃላፊ ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ በእንጦጦው ፕሮጀክት ተገኝተው ጉብኝት ሲያደርጉ ከተቆፋፈረ መሬትና አንዳንድ ስራዎች በስተቀር ግንባታው ጅማሮ ላይ ነበር።
አሁን ላይ ግን ለብስክሌት እና እግረኛ ብቻ የሚያገለግል ስድስት ኪሎሜትር አስፓልት ግንባታን ጨምሮ የቤተመጻህፍት፣ የዘመናዊ ካፍቴሪያ እና አነስተኛ ስታዲየም ግንባታዎች ተጠናቀዋል። የፈረስ መጋለቢያውም ቢሆን የአካባቢው ልዩ መዝናኛ ቦታ ነው። ፓርኩን የሚገነቡ ኢንጂነሮች እንደሚሉት ከሆነ በወርሐ ግንቦት 2012 ዓ.ም 14 ኪሎሜትር የውስጥ ለውስጥ የብስክሌትና እግረኛ አስፓልት መንገድ እና የቴሌስኮፕ ማማ ግንባታዎች ተጠናቀው ፓርኩ ለህዝብ ክፍት ይደረጋል።
ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው ፕሮጀክቱን አስመልክተው የዛሬ ሳምንት ባደረጉት ንግግር ከተሞቻችን አንጡራ ሀብት በውስጣቸው ይዘዋል ማለታቸው አይዘነጋም። <<በእንጦጦ ፕሮጀክት ጉብኝት እንደተመለከትኩት፣ ለውጡ አስደናቂ ነው። ሥራው ሲጠናቀቅ ደግሞ አያሌ የቱሪስትና የሥራ ዕድሎችን ይፈጥራል። ዕምቅ ሀብታችንን ለኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዕድገታችን በጥቅም ላይ ለማዋል አብራችሁኝ እንድትጓዙ እጠይቃለሁ>> ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
የግንባታውን ሂደት የሚከታተሉ ኢትዮጵያውያንም ደግሞ የፓርኩ የቱሪስት መዳረሻ ልማት ግንባታ እንዳስደሰታቸው ይናገራሉ። የእንጦጦ አስጎብኚ ድርጅት ማናጀር አቶ ኤርሚያስ ኃይሉ እንደሚናገሩት፤ አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ የከተማ ጥቅል የጉብኝት አማራጮች ውስጥ የእንጦጦ ፕሮጀክትን ለማካተት የሚያስችል ስራ እየተከናወነ መሆኑ አስደሳች ነገር ነው።
እንጦጦ ላይ ሆኖ አዲስ አበባን በቴሌስኮፕ ለመመልከት እና በጫካ ውስጥ በብስክሌት ለመጓጓዝ የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች እየተሟሉ መሆኑ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ጎብኚዎች ዘንድ አካባቢውን ተመራጭ ቦታ ያደርገዋል። አስጎብኚዎች የቤተመንግስት አንድነት ፓርክን በጥቅል የጉብኝት አማራጫቸው ውስጥ አካተውት በርካቶች እንዲዝናኑበት ማድረጋቸው የቱሪዝሙን ገቢ እያሳደገው መሆኑን የገለጹት አቶ ኤርሚያስ፤ የእንጦጦም ፕሮጀክት ግንባታም በአስደናቂ ፍጥነት እየተከናወነ በመሆኑ በጥቂት ወራት ውስጥ ለጎብኚዎች አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ብለው እንደሚያምኑ ይገልጻሉ።
በየሳምንቱ ቅዳሜ የእንጦጦ ፕሮጀክትን በመጎብኘት የሚዝናኑት አቶ ሞገስ ታምራት በበኩላቸው፤ በአካባቢው ያለው የስራ ባህል አስደሳች መሆኑን እና በግንባታው ፍጥነት ምክንያት ከሳምንት ሳምንት ለውጥ እንደሚያዩበት ይናገራሉ። የእንጦጦን ደን ሰንጥቆ የሚያልፈው ግንባታ እና የመዝናኛ ቦታዎች አካባቢውን በማይበክል እና ስነምህዳሩን በማይለውጥ መልኩ እየተገነቡ መሆናቸው ደግሞ ሌላኛው የቦታው ሳቢ
ክፍል መሆኑን ያስረዳሉ። እንደ አቶ ሞገስ ከሆነ፤የእንጦጦ ፕሮጀክት በጣውላ እና በተለያዩ አካባቢውን በሚወክሉ ቁሳቁሶች የተገነባ በመሆኑ የእንጦጦን የመዝናኛ ስፍራ ማራኪ ገጽታ አላብሰውታል። በይበልጥ ደግሞ ከአዲስ አበባ እምብርት በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ መዝናኛ ቦታ በመሆኑ በርካቶች የሚጎርፉበት ቦታ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በፕሮጀክቱ ስር ተቀጥራ እየሰራች የምትገኘው ወጣት ቅድስት ደስታ በበኩሏ እንደምትናገረው፤ ግንባታው ቀንም ማታም እየተከናወነ ይገኛል። ለአካባቢው ወጣቶችም የስራ እድል ፈጥሯል። ለአብነት በአንዱ የመዝናኛ ክፍል ብቻ 70 ሰራተኞች ተቀጥረዋል። ግንባታው ሲጠናቀቅም እንዲሁ ለተለያዩ ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ወጣት የምስራች ትናገራለች። በቀጣይ ደግሞ ጎብኚዎች በብዛት ሲመጡ በተጓዳኝ አገልግሎት ለሚሰጡ የእደጥበብ ውጤቶች አምራቾች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች እና ምግብ እና መጠጥ ለሚያቀርቡ ሰዎች ሰፊ የገበያ አማራጭ የሚከፍት ሀገራዊ ፕሮጀክት መሆኑንም ታስረዳለች።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 ቀን 2012 ዓ.ም
ጌትነት ተስፋማርያም