
ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ ባለቤት ብትሆንም በወንዙ ላይ ያላትን መብትና ተጠቃሚነት በተመለከተ ሚዲያዎቿም ሆኑ ምሁኖቿ ለዓለም ማሕበረሰብ እውነታውን እምብዛም እንዳላስተዋወቀችና ግብጽ በአንጻሩ ውጤታማ የተግባቦት ስራ በማከናወኗ መብቷ ባልሆነው ጉዳይ ላይ ሰፊ ተቀባይነት ማግኘቷን ጸሀፊና የሚዲያ ተንታኙ አቶ ሞሃመድ አል አሩሲ ገለጹ።
አቶ ሞሃመድ የግብጽ ምሁራንና ሚዲያዎች ለበርካታ ዓመታት በሰሩት ስራ የአባይ ውሃ የህልውናቸው መሰረት እንደሆነ ለዓለም ህዝብ ሲያስረዱ መኖራቸውን ገልጸዋል። ይህም የዓለም ህዝብ ዛሬ ግብጽ የምታነሳቸው ጥያቄዎች ትክክለኛ ናቸው ብሎ እንዲቀበል የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ ባለቤት ብትሆንም በወንዙ ላይ ያላትን መብትና ተጠቃሚነት በተመለከተ ሚዲያዎቿም ሆኑ ምሁኖቿ ለዓለም ማሕበረሰብ እውነታውን እምብዛም አላስተዋወቁም። ይህም በኢትዮጵያ ተደማጭነት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። የግብጽ ሚዲያዎችና ሙሁራኖች ስለአባይ ወንዝ አበክረው መስራታቸው ዓለም ግብጽና የአባይን አስተሳስሮ እንዲመለከት እና ከግብጽ ወዲያ የአባይ ጉዳይ የሚመለከተው ሀገር የለም የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዙ ያደርጋል ብለዋል።
አቶ ሞሃመድ እንደሚያስረዱት በተለያዩ የዓለም በተለይም የአረብ ሀገራት ሚዲያዎች ተጋብዘው ሲቀርቡ ከሚቀርብላቸው ጥያቄ የመጀመሪያው ‹‹ የአባይ ወንዝ ጉዳይ የሚመለከተው ግብጽን ሆኖ ሳለ እናንተ ለምን ይመለከተናል ትላላችሁ›› የሚል ነው።
ከዚህ መረዳት የሚቻለው ግብጽ ምን ያህል አባይን አስመልክቶ የተሳሳተ መረጃ ለዓለም ስታቀርብ እንደነበረ ነው። አቶ ሞሃመድ እንደሚያስረዱት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን መብት ለዓለም ህዝብ ማሳወቅ የመንግስት ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የህዝቡ ነው። የግብጽ ሚዲያዎች ጠዋትና ማታ የአባይን ጉዳይ ርዕሰ ጉዳያቸው በማድረግ የተለያዩ መልዕክቶችን ለዓለም ህዝብ አስተላልፈዋል። ‹‹እውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል›› እንደሚባለው የግብጽ ሚዲያዎች አባይን አስመልክቶ በተደጋጋሚ የሚያስተላልፉት የተሳሳተ መረጃ በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ እውነት ተደርጎ መወሰዱን አቶ ሞሃመድ ያስረዳሉ ።
በግብጽ ያለው የፖለቲካ ልዩነት ህዝቡን የከፋፈለ፣ መንግስትን አመኔታ ያሳጣና መፍትሄ የማይገኝለት ቢመስልም የአባይ ጉዳይ ሲነሳ ግን ይህን ሁሉ ልዩነታቸውን ትተው በአንድ ድምጽ ኢትዮጵያ ላይ መዝመታቸውን ይገልጻሉ። እንደ አቶ ሙሃመድ ግብጾች በሀገራቸው ጉዳይ አንድ ላይ የሚያሰባስባቸው መንፈስ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥም መለመድ ይኖርበታል።
ኢትዮጵያዊያን ለጊዜው የውስጥ ችግሮቻቸውን አሳድረው በተፈጥሮ ሀብታቸውና በሀገራቸው ጥቅም ላይ የመጣውን አደጋ ለመመከት በጋራ መቆም እንዳለባቸው ይመክራሉ። ባለንበት ዓለም እውነትን ብቻ ይዞ መቀመጥ ብቻ እንደማያዋጣና ለዓለም ማህበረሰቡ ጉዳይን ደጋግሞ ማስረዳትን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። አቶ ሞሃመድ በተለያዩ ጊዜያት እንደ ቢቢሲ፣ አልጀዚራ፣ አልሀረም፣ አሻርኪ እና ሌሎች ሚዲያዎች ላይ በመቅረብ በኢትዮጵያ በኩል ያለውን እውነታና አቋም ለማስረዳት የሞከሩ ናቸው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 ቀን 2012 ዓ.ም እያሱ መሰለ