አዲስ ዘመን፤ ለጸረተዋህሲያን ምርቶች እና ለንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ማዘጋጃ ግብዓትነት የሚውል ሦስት ሚሊዮን ሊትር <<ቴክኒካል አልኮሆል>> ምርት በሁለት ፋብሪካዎች በመኖሩ አምራቾች ገዝተው መጠቀም እንደሚችሉ የስኳር ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
የስኳር ኮርፖሬሽን ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጋሻው አይችሉህም እንደገለጹት፤ በፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ እና በመተሐራ ስኳር ፋብሪካዎች ለጸረተዋህሲያን ምርቶች እና ለተለያዩ ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ማዘጋጃነት የሚያገለግል ቴክኒካል አልኮሆል የተሰኘ ኬሚካል ይገኛል።
ሁለቱም ፋብሪካዎች በቀን 100ሺህ ሊትር ቴክኒካል አልኮሆል እያመረቱ በመሆኑ ፈቃድ ያላቸው የንጽህና ምርቶች የሚያዘጋጁ እንዲሁም ጸረተዋህሲያን ላይ የሚሰሩ ተቋማት ምርቱን ገዝተው መጠቀምና ለህብረተሰቡ ማድረስ ይችላሉ። እንደ አቶ ጋሻው ከሆነ፣ በተለይ የኮሮና ቫይረስ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል ከፍተኛ የጸረተዋህሶያን እና ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ለህብረተሰቡ መቅረብ እንዳለባቸው ሲታሰብ
ከስኳር ፋብሪካዎች የተገኘው የቴክኒካል አልኮሆል ምርት አስፈላጊነቱ ከፍተኛ ነው። በተለይ ከውጭ ይመጣ የነበረውን ቴክኒካል አልኮሆል በማስቀረት የንጽህና መጠበቂያ ቁሶችን በአጭር ጊዜ አምርቶ ለማቅረብ ጥሩ አማራጭ ቀርቧል። በመሆኑም ምርቱን ለሚጠይቁ አካላት አንዱን ሊትር ቴክኒካል አልኮሆል በ52 ብር ከ85 ሳንቲም ገዝተው መጠቀም ይችላሉ።
የስኳር ኮርፖሬሽን ለአዲስ ዘመን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው ደግሞ፤ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል የሚያገለግሉ የንጽህና መጠበቂያ ቁሶችን ለማዘጋጀት በግብዓትነት የሚውለውን ቴክኒካል አልኮሆል ምርት ለፈላጊዎች ከማዳረስ በተጨማሪ የምርት መጠኑን ለማሳደግ ኮርፖሬሽኑ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
ከስኳር ፋብሪካዎች የሚገኘው እና ከስኳር ተጓዳኝ ምርቶች መካከል አንዱ የሆነው ቴክኒካል አልኮሆል የተሰኘው ምርት 96 ከመቶ አልኮልነት ባህሪ ያለው ኬሚካል ነው። ኬሚካሉም ለሳኒታይዘር፣ ለደረቅና ፈሳሽ ሳሙና እንዲሁም ለመጸዳጃ ቤት ማፅጃ ምርቶች ማዘጋጃ ግብዓትነት ያገለግላል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 ቀን 2012 ዓ.ም
ጌትነት ተስፋማርያም