
ከ500 በላይ አምቦላንሶችም ተዘጋጅተዋል
አዲስ አበባ፤ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በሀገሪቱ የተከሰተውን የኖቭል የኮሮና ቫይረስ በሽታን ለመከላከል ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡንና ከ500 በላይ አምቦላንሶችን ማዘጋጀቱን አስታወቀ። ትናንት በጽህፈት ቤቱ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የማህበሩ ዋና ጸሀፊ ዶክተር መሸሻ ሸዋረጋ እንደተናገሩት ክስተቱ በአለም አቀፍ ደረጃ መሰማት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት ሁለት ወራት ማህበሩ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ሲሰራ ቆይቷል። ወደ ክልሎችም በመውረድ ጽህፈት ቤቶች በሚገኙባቸው 132 ወረዳዎችና ቀይ መስቀል ጽህፈት ቤት ባልከፈተባቸውም አካባቢዎች አገልግሎቱን ለማድረስ በጎ ፈቃደኞችን እያሰለጠነ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅትም ከመቶ በላይ በጎ ፈቃደኞች በአዲስ አበባ ባሉ ከነማ መድሀኒት ቤቶች አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን በአዲስ አበባ፤ በኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ 200 ተንቀሳቃሽ በጎ ፈቃደኞች ሙያዊ ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል። የኢቮላ በሽታን ለመከላከል ስልጠና ወስደው የነበሩ 16 በጎ ፈቃደኞችም ከኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ኢኒስቲትዩት ቡድን ጋር በመሆን በአዳማ፤ አሰላና ዴራ ኬሚካል በመርጨት ተግባር እንዲሰማሩ ተደርጓል።
በአዲስ አበባና በክልል አውሮፕላን ማረፊያዎችና ከአጎራባች ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ መግቢያ ኬላዎች ላይ ከጤና አጠባበቅ ኢኒስቲትዩት ጋር የሙቀት ልየታ እና የተዋህስያን ማንጻት ስራ የሚሰሩ በጎ ፈቃደኞች ተመድበዋል። ከአራት ሺ በላይ ለሚሆኑ ባለድርሻ አካላትና ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍል ስለቫይረሱ የግንዛቤ ማስጨበጫ
የተሰጠ ሲሆን ከሶስት ሺ 800 በላይ ገላጭ በራሪ ወረቀቶችም በባንኮች፤ የትራንስፖርት ማእከላትና ህዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ተደርጓል። ለማረሚያ ቤቶችና አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ፈሳሽ ሳሙናና ንጽህና መጠበቂያዎች የተሰራጩ ሲሆን በቀጣይም ይህ ጥረት የሚቀጥል መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከ500 በላይ አምቦላንሶች አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቀው በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን የገለጹት ዶክተር መሸሻ፤ አምቡላንሶችን በመጠቀም ቫይረሱን እንዴት መከላከል እንደሚቻልና መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ የግንዛቤ ማስጨበጫ በአዲስ አበባ፤ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ባሉ በትልልቅ ከተሞች እየተሰጠ ሲሆን ወደ ዞንና ወረዳ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል። በአቅርቦት ረገድም እስካሁን ከአምስት ሺ በላይ የንጽህና መጠበቂያዎች የተሰራጩ ሲሆን፤ ከአለም አቀፍ የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽንና ከእህት ማህበራት ጋር በመሆን 5 ሺ የፊት ማስክ፤ 6ሺ ሰርጂካል ጓንት 1ሺ500 የህክምና ጫማ አንድ ሺ የፕላስቲክ የፊት መከላከያና 5ሺ የመለያ ገዋኖች ለመግዛት መታቀዱንም ጠቁመዋል።
ዶክተር መሸሻ ጨምረው እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር 192 ሀገራትና ማህበራት ያሉት የዓለም አቀፉ ቀይመስቀል ፌዴሬሽን አባል ነው። በመሆኑም እነሱን በመጠቀም አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ወደሀገር የማስገባት ስራ የሚሰራ ሲሆን ከእነዚህ አጋር ድርጅቶች መካከል ኢትዮጵያ ውስጥ በመጋዘኖቻቸው ያስቀመጡም ስላሉ እነሱንም ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚሰሩ ተናገረዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 ቀን 2012 ዓ.ም
ራስወርቅ ሙሉጌታ