
አዲስ አበባ፤ የኮሮና በሽታ ሥርጭትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የአልኮል መጠጥ ምርቶቹን ለጊዜው በመቀነስ በሰዓት አምስት ሺህ ሊትር ጸረተዋህሲያን የእጅ ንጽህና መጠበቂያ <<ሳኒታይዘር>> እያመረተ መሆኑን ቪቭ ቢቨሬጅ ማምረቻ አክሲዮን ድርጅት አስታወቀ። ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 200 ሺህ ሊትር ሳኒታይዘር እያቀረበ እንደሚገኝም ተገልጿል። ሸኖ ከተማ መግቢያ ላይ የሚገኘው የሳኒታይዘርና አልኮል መጠጦች ማምረቻ ፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ ኤልያስ አበበ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ፋብሪካው የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ለመሳተፍ ለአልኮል መጠጦች ምርቶቹ የሚገለገልባቸውን ማሽኖች ለጸረተዋህሲያን ኬሚካሎች ማምረቻነት በማዋል ላይ ይገኛል። በዚህም መሰረት በቀን ከ50ሺህ
እስከ 60ሺህ ሊትር የሚደርስ ሳኒታይዘር ምርት ለተቋማት እና ለህብረተሰቡ እያቀረበ ይገኛል። እንደ ስራ አስኪያጁ አቶ ኤልያስ ገለጻ፤ የኮሮና በሽታን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ምክንያት ፋብሪካው አቅሙን በማጠናከር የሳኒታይዘር ምርቱን በእጥፍ ለማሳደግ አቅዷል። ለዚህም እንዲረዳ በሌሊትም ጭምር በመስራት በሦስት ፈረቃ የምርት ሂደቱን በማከናወን ላይ ይገኛል። በመሆኑም ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ ተጨማሪ ሠራተኞች በመቅጠር በቀን ከ100ሺህ ሊትር በላይ ሳኒታይዘር ለማምረት ዝግጅት አድርጓል። አቶ ኤልያስ እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የፌዴራል ተቋማት እና የተለያዩ ድርጅቶች የሳኒታይዘር ምርቱ እንዲቀርብላቸው ጥያቄ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅትም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚውል 200ሺህ ሊትር ሳኒታይዘር እየቀረበ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪ የቁስል አልክሆል ምርት
እንዲዘጋጅላቸው የሚጠይቁ ተቋማት በመኖራቸው ከሳኒታይዘር በተጨማሪ ለጸረተዋህሲያን ማጽጃነት የሚያገለግለውን የቁስል ማጠቢያ አልክሆል እየተመረተ ይገኛል። የጸረተዋህሲያን ማጽጃ የሚያገለግሉት ምርቶቹ በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ፋብሪካ ባለሙያዎች አስፈላጊው ፍተሻ ተደርጎባቸው ለፋብሪካው የብቃት ማረጋገጫ ስለተገኘ ምርቱ በየአካባቢው መከፋፈሉን ቀጥሏል። የከተማ አስተዳደሩ በተለይም ከንቲባው ሳኒታይዘሩ በጥቂት ቀናት ውስጥ የማምረት ስራው እንዲጀምር ያደረጉት ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን የተናገሩት አቶ ኤልያስ፤ ፋብሪካው ምርቱን በሊትር በ80 ብር ካቀረበ በኋላ ከተማ አስተዳደሩ ምንም ብር ሳይጨምር በተገዛበት ዋጋ ለህብረተሰቡ እያቀረበ ይገኛል። በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኩል በተለያዩ የሽያጭ አማራጮች ምርቱ የመቅረብ እድሉ እየሰፋ በመሆኑ ህብረተሰቡ
በህገወጥ ነጋዴዎች አማካኝነት ከሚደርስበት ብዝበዛ እና ምርቱን ለመግዛት ከሚደረግ አላስፈላጊ ሰልፍ እራሱን ሊጠብቅ እንደሚገባ ተናግረዋል። ሳኒታይዘሩ በአሁኑ ወቅትም ተመርቶ ለገበያ እየቀረበ በመሆኑ ህብረተሰቡ የምርት እጥረት ስጋት ሊሰማው እንደማይገባ ገልጸዋል። እንደ አቶ ኤልያስ ከሆነ፤ ከውጭ ምንዛሬ ጋር በተያያዘ ለምርቶቹ ማሸጊያ የሚሆን የፕላስቲክ ምርት እና ግሪሲሊን እንዲሁም የተወሰኑ ኬሚካሎች እጥረት ቢኖርም ለሳኒታይዘሩ ማምረቻ ይሁንና ዋነኛ ግብዓቱ የሚሆነው ቴክኒካል አልክሆል የተሰኘው ምርት ከኦሞ ስኳር ፋብሪካ በኩል በበቂ ሁኔታ እየቀረበ ይገኛል። ስኳር ኮርፖሬሽን በበኩሉ ባደረገው ድጋፍ ግብዓቱ በወንጂ እና ሌሎች በአቅራቢያ በሚገኙ ፋብሪካዎች በኩል እንዲቀርብ እድል ተመቻችቷል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 ቀን 2012 ዓ.ም
ጌትነት ተስፋማርያም