
አዲስ አበባ፡- መንግስት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ30 አገሮች በረራ እንዳያደርግ አገደ፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ የመሸታ ቤቶች ላልተወሰነ ጊዜ እንዲዘጉ ከመወሰኑ በተጨማሪ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሰዎች 14 ቀን ለይቶ መቆያ እንዲቆዩ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የኮሮና ቫይረስ መዛመትን ለመግታት የተወሰዱ እርምጃዎችን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ፤መንግስት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ቀደም ሲል ከወሰዳቸው እርምጃዎች በተጨማሪ የኢትዮጵያ አየር መንገዱ ከትናንት ጀምሮ የቫይረሱ ስርጭት በስፋት ታይቶባቸዋል በተባሉ ከ30 በላይ አገራት በረራ እንዲያቋርጥ ተደርጓል፡፡
ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገባ ማንኛውም ሰው 14 ቀናት በለይቶ ማቆያ መቆየት እንዳለበትም ተወስኗል፡፡ ኢትዮጵያ 110 ሚሊዮን ህዝብ ስላላትና ወደብ ስለሌላት አንዱ ከውጭ የሚያገናኘውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተዘጋ መድሃኒትና የኮሮና መመርመሪያን ከውጭ ማስገባትን ጨምሮ በርካታ ችግር ሊያጋጥም ስለሚችል በጥናትና በእውቅት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለመወሰን ጉዳዩ ሲታይ ቆይቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኮሮና ቫይረስ የበሽታን ስርጭት ለመግታትም አየር መንገዱ ከትናንት ጀምሮ ከ30 በላይ አገራት በረራ እንዲያቋርጥ ተወስኗል ብለዋል።
አየር መንገዱ በ30 አገራት በረራ አንዳያደርግ የተወሰነ ቢሆንም ከእነዚህ አገራት ውጭ የሚመጡ ሰዎች 14 ቀናት ለይቶ ማቆያ መቆየት እንደሚኖርባቸው የተወሰነ መሆኑን ገልጸው፤ ከውጭ አገራት የሚመጡ ሰዎች በማቆያ ውስጥ በሚያሳልፏቸው ጊዜያት የሚያስፈልጓቸው ወጪዎች በሙሉ የሚሸፈነው በግለሰቦቹ መሆኑን ተናግረዋል። ለለይቶ ማቆያ የሚሆኑ ሆቴሎችና መለስተኛ ቦታዎች እንደ ሰዎቹ አቅም ለማዘጋጀት ሙከራ መደረጉን አመልክተው፤ ኢትዮጵያ የሚገባ ማንኛውም ሰው 14 ቀናት ቆይቶ በሽታው እንደሌለበት ሲረጋገጥ ከህዝብ ጋር እንዲቀላቀል የተወሰነ መሆኑን አብራርተዋል።
ከእምነት ተቋማት ጋር ተያይዞ መሳለም፣መስገድና ሰብሰብ ብሎ ትምህርት መከታታል የመሳሰሉት የአምልኮ ስርዓቶች የእምነቱ ተከታዮች ለበሽታው የሚያጋልጡ በመሆናቸው የሃይማኖት ተቋማት የተለየ መንገድ እንዲጠቀሙ ከእምነት አባቶች ጋር ስምምነት የተደረሰ በመሆኑ የእምነት አባቶች ለተከታዮቻቸው መልዕክት በማስተላለፍ የተከታዮቻቸውን ህይወት እንዲታደጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ከማረሚያ ቤት ጋር ተያይዞም በሽታው ከገባ ሊዛመት ስለሚችል የተጨናነቁ ማረሚያ ቤቶች ተጨማሪ ቦታዎች የማዘጋጀትና የማስፋት ስራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ወደ ማረሚያ ቤቶች አዳዲስ ታራሚዎች የሚገቡ ከሆነ በበሽታው ያለመያዛቸው ተረጋግጦ እንዲገቡ ፣የታራሚዎች የቤተሰብ ጥየቃ ላልተወሰነ ጊዜ የተከለከለ መሆኑን እንዲሁም ህጻናት የያዙ፣ የአመክሮ ጊዜያቸው የደረሰ፣ ጉዳያቸው ቀላል የሆኑ ታራሚዎች ተለይተው እንዲፈቱ ተወስኗል ብለዋል። የኢትዮጵያ ህክምና ባለሙያዎች አስካሁን ባልተሟላ ሁኔታና ቁሳቁስ በበሽታው የተጠቁ ሰዎችን ለመደገፍ ላደረጉት ጥረት መንግስት አድናቆትና ምስጋናው ከፍ ያለነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ በሽታው የሚዛመት ከሆነ በትምህርትም ሆነ በስራ ላይ ያሉ የህክምና ባለሙያዎች ልክ እንደአገራዊ ግዳጅ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁና በሽታውን ለመግታት ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
መንግስት በራሱ ስር የሚገኙት ሆስፒታሎች በሽታውን ለመከላከል ዝግጁ እንዲሆኑ ማድረጉን አውስተው፤ የግል ሆስፒታሎች በራሳቸው ዝግጅት እንዲያደርጉና አገራዊ ችግሩን በትብብርና በመረዳዳት ለማለፍ ሁለንተናዊ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። የቢል ጊት ፋውንዲሽን ጨምሮ ሌሎች የልማት አጋሮች ኢትዮጵያ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት እየደገፉ መሆኑን ጠቁመው የዓለም ባንክም በሽታውን ለመቆጣጠር ለሚደረገው ጥረት ከ 80ሚሊዮን ዶላር በላይ ለመደገፍ ውሳኔ ማሳለፉን ገልጸዋል።
ክልሎችም በሽታውን ለመከላከል አስፈላጊ የሆኑ የህክምና መሳሪያዎች እንዲሟሉላቸው መደረጉን ተናግረዋል። የመሸታ ቤቶች ለበሽታው መሰራጨት የስጋት ቦታዎች መሆናቸውን አመልክተው ከ10 ሰዎች በላይ የሚገኙባቸው የአዲስ አበባ የመሸታ ቤቶች ከትናንት ጀምሮ እንዲዘጉ የተወሰነ መሆኑን ጠቁመዋል። ቫይረሱ ከተከሰተ በኋላ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና ማስከተሉንም በመግለጫቸው አስታውቀዋል። ለአብነትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ በቫይረሱ መቀስቀስ ምክንያት ከ190 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ማጣቱን ጠቅሰዋል።
የወጪ ንግድ ዘርፉን በተለይም የአበባ እና የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች ተቀባይ ሃገራት ምርቶቹን መቀበል በማቆማቸው ዘርፉ መቀዛቀዙን አንስተዋል። ህብረተሰቡ በሽታው እንዳይዛመት የበኩሉን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትና መዘናጋትን ማስወገድ እንደሚገባው ገልጸው መዘናጋቶች እንደ አገር ከፍተኛ ዋጋ ስለሚያስከፍሉ መላው ህዝብም በሽታውን ለመከላከል አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። በአሁኑ ጊዜ የኮሮና ቫይረስ 172 አገሮች የተዛመተ ሲሆን እስካሁን ድረስ ከ10ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ ከ200ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው የተጠቁ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በኢትዮጵያም 9 ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸው ይታወቃል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 ቀን 2012 ዓ.ም
ጌትነት ምህረቴ