በአድዋ ተራሮች ግርጌ በተከበረው የአድዋ 124ኛ የድል በአል ላይ የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል፤‹‹ በአድዋ የተሰራው አንፀባራቂ የድል ታሪክ የብዙ ትምህርቶች ምንጭ የሆነ፤ አገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ ያለው ታሪካዊ ድል ነው።
አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ለአገራቸው ክብር፣ ብሄራዊ ጥቅም፣ ህልውናና ልዕልና ማስከበርና ማስጠበቅ ግዴታና ኃላፊነት ያላቸው መሆኑን በመገንዘብ፤ ከፍተኛ ስልጠናና ዝግጅት ካለው የኢጣሊያን ሰራዊት የማጠቃለያ ውጊያ በአድዋ በመግጠም ጦርነቱን በማሸነፋቸው ደካማ ተብለው የሚፈረጁ ህዝቦች ሳይለያዩ በጋራ ለጋራ ተራማጅ ህዝባዊ ዓላማ ከተነሱ ሊገመት የማይችል ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችሉ አድዋ ህያው ምስክር ነች ›› የሚል የአንድነትን ጠቃሚነት የሚያሳይ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
እርሳቸው ‹‹… ሰሞኑን የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ የቀረበው የውል ሰነድም ቆም ብለን ከውጫሌ ውል በመማር በውሉ የሰፈሩ ሃሳቦችና ቃላቶች በሉአላዊነታችን ላይ የመጡ፤ ከዚያም አልፈው ለሌላ ጂኦፖለቲካ አላማ ማስፈፀሚያ ገፀ በረከትና እጅ መንሻ ሆኖ እንዳያገለግል በከፍተኛ ጥንቃቄና ሃላፊነት መፈፀም ይገባዋል።
ወደ ጦርነት ካስገባን የውጫሌ ውል ሳንማር ቀርተን በአገር ላይ ጉዳት ቢደርስ ይህ ሌላ ስህተት ሳይሆን የሚያስጠይቅ ጥፋት መሆኑ አይቀርም›› በማለት ችግር ከማስተናገዳችን በፊት ደጋግመን ማስተዋል እንዳለብን የሚያመላክት መልዕክት አስተላልፈዋል።
በርግጥም ከ124 ዓመታት በፊት ኢጣሊያን ውጫሌ ላይ ያደረገው ውልና ያስከተለው የሃሳብ መፋለስ ስምምነት ባለማምጣቱ በርካታ ወገኖቻችን የህይወትና የአካል መስዋዕትነት በመክፈል፤ ሊነጠቅ የተሞከረው ነጻነታችን ከእጃችን ሳይወጣ ወራሪው የኢጣሊያ ወራሪ ከአገራችን እንዲባረር ተደርጓል፡፡
በቅርቡ በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ መካከል ሲደረግ የነበረው የግድቡን የውሃ አሞላል የተመለከተ የሦስትዮሽ ድርድር ካለስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ በታዛቢነት ተቀምጣ የነበረችው አሜሪካ በፈለገችው መስመር ውሉ እንዲፈረም ጫና ለመፍጠር እያደረገች ያለው ጥረት ከቀደመው ታሪካችን የውጫሌን ውል ተከትሎ የገባንበትን ያለመግባባት መንፈስ ዓይነት እንዳይሆንብን ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረጉ አማራጭ የለውም::
የአሜሪካን ገሀድ የወጣ ለግብፅ ያደላ አቋም የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚጋፋ ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ የራስዋ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሳይቀሩ ሲቃወሙት ተስተውሏል፡፡ የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር ዴቪድ ሺን ‹‹ የትራምፕ አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ እጁን ለማሳረፍ የሞከረው ለግብፅ ባለውለታ ለመሆን ካለው ምኞት የተነሳ ነው›› የሚል ትችት ሰንዝረዋል፡፡
ስለሆነም የአድዋ ድል የነጻነታችን ተምሳሌት እንደሆነው ሁሉ የህዳሴ ግድብም የሉአላዊነታችን መገለጫ በመሆኑ በማንም ጣልቃ ገብነት ብሄራዊ ጥቅማችን አሳልፈን የማንሰጥ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን የቀረበላትን ስምምነት እንድትፈርም አሜሪካ የምታስገድድ ከሆነ ግብጽን በወንዙ እና ግድቡ ላይ ባለሙሉ ስልጣን የማድረግ አላማ ያለው በመሆኑ ተገቢ አይደለም፡፡ ይህ ሀገሪቱን በገዛ ውሃዋ ላይ እንዳትጠቀም የሚያደርግ የአሜሪካ እና የዓለም ባንክ ተግባር ታሪክም ሆነ የዓለምአቀፉ ሕግ የማይዘነጋው ወንጀል ይሆናል።
ይህም የታላቋ ብሪታንያን የ1929ን የቅኝ-ግዛት ውልን ዘመን ትክክለኛ እና ተቀባይነት ያለው የ21ኛ ክፍለዘመን ሕጋዊ ሰነድ አድርጎ እንደማቅረብ ይቆጠራል። ስለሆነም ተገቢም ፍትሃዊም አይደለም፡፡
ዶክተር ደብረፂዮን ‹‹የድሮ ቅኝ ገዥዎች የሚፈልጉትን አገር ወርረው በጉልበትና በመሳሪያ ይገዙ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፤ የአሁኑ ቅኝ ገዥዎች ግን አገሮች የፖሊሲ ነፃነት እንዳይኖራቸው በሪፎርም፣ በብድርና እርዳታ ስም ለእነሱ የሚጠቅም ለውጥ እንዲደረግ በመጫን በቁጥጥራቸው ስር በማስገባት፣ ዜጋው በመሰለው አገሩን እንዳያስተዳድር የሚያደርጉ መሆኑን በመገንዘብ እኛም እንደ ቅድመ አያቶቻችንና አያቶቻችን አገራችንን ከማንኛውም የውጭ ጣልቃገብነት ጠብቀን ነፃነታችን አስጠብቀን ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ታሪካዊ ሃላፊነታችንና ግዴታችን መሆኑን መገንዘብ ይገባል ›› ሲሉ እንዳስተላለፉት ጠንካራ መልዕክት በአድዋ እንደታየው አንድነታችን በመቻቻል፣በመተሳሰብና በመረዳዳት የፀና አይበገሬ አንድነታችንን በማሳየት ክፉ የሚያስቡልንን ልናሳፍራቸው ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2012