ከአስተማሪው ፊት ለፊት ካልተቀመጠ ትምህርት እንደማይገባው የሚያስብ የትምህርት ቤት ጓደኛ አልገጠማችሁም? የጥናት ክፍል ስላላዘጋጀሁለት፣ አስጠኚ ስላልቀጠርኩለት፣ ላፕቶፕ ስላልገዛሁለት ወዘተ… ልጄ በትምህርቱ ሰነፍ ሆነ የሚል ቀልማዳ ወላጅስ ታዝባችሁ አታውቁም? አዎ! እንዲያው የድክመት መጠቅለያው ሰበብ ሆኖ እንጂ ልበ ብርሃኖችማ ጥበብ መቅሰሚያቸው የትም ነው፤የትም፡፡
አሁን አሁንማ‹‹ የአባቱ ልጅ..›› ይሉት ብሂል ‹‹የሰበብ ልጅ… ›› በሚል የተተካ ይመስላል፡፡ የአገሪቱ ወጣት የሰበብ ውላጅ ሰበባም ሆኗል፡፡ ወጣቱ ውስጣዊ ልበ ሙሉነት ከድቶታል፡፡ ምክንያታዊ ሆኖ ራሱን ችሎ መቆም ተስኖት ተዛሟል፡፡ ለነገሩ የሕዝብ አመል እንደአሳዳሪው/እንደገዥው/ ነው፡፡ ከቅኝቱ ሆነና ነገሩ በሰው ቁስል ሳይሆን በራሱ ቁስልም ትምህርት የሚወስድ ወጣት ጠፍቷል፡፡ አሁን ይሄን ከአያቶቹና ከቅድመ አያቶቹ ትምህርት ያልቀሰመ ትውልድ ብሎ ግብሩን ማንሳት እንደምን ይቻላል?፡፡
ከሰሞኑ በማህበራዊ ሚዲያው እንደ እንዝርት ከሚሾሩ ቀልብ ሳቢ ወሬዎች አግራሞትን የሚጭሩ ነበሩ፡፡ አገርና መንግስትን መለየት የተሳነው ወጣት ትውልድ መብቀሉን የሚያመላክትም ነበር:: ወቅቱ የአድዋ ድል የሚከበርበት በመሆኑ ከዛሬ ሰባት አመታት በፊት በበጎ ፈቃደኞች በእነ ያሬድ ሹመቴ አነሳሽነት እና በመንግስት ይሁንታ በየዓመቱ የአርበኞችን ተጋድሎ ለመዘከር የአድዋ ተጓዦች በእግራቸው ይተማሉ፡፡ ወጣቶቹ በየደረሱበት ቀዬ ታሪክን ከእውነታው እያመሳከሩ ከሺህ በላይ ኪሎ ሜትሮችን ያቋርጣሉ፡፡
እችላለሁ የሚል ወኔ ለሰነቀ ወጣት የማይቻል አለመኖሩን በተግባር ያስተምራሉ:: የኋላ ታሪክን ማወቅ ወደፊት መሄድ ያስችላል ባይ ናቸው፡፡ እናም ከዘንድሮ አድዋ ተጓዥ ወጣቶች አንዱ አድዋ ከተማ ከሚገኝ አንድ ሱቅ ጎራ ይላል፡፡ ምን እግር እንደጣለውም ሱቅ ሻጯ ትጠይቀውና የአድዋ ድል በዓልን በቦታው ለመታደም በእግሩ እንደመጣ በልበ ሙሉነት ይነግራታል፡፡ እሷም ምነው ስራ የለህም? ምን አለፋህ? ምን ታገኛለህ? ብላው እርፍ! እውነታው የታሪክን ሃብትነት አለመረዳትን ያሳያል፡፡ አለያም የመንግስትና የአገርን ልዩነት ወጣቱ ስቷል፡፡
በተጨማሪም መንግስት ቦታውን የሚያስታውስና ማህበረሰቡን የሚጠቅም አንዳች የሚፈይድ ነገር አልሰራልንም የሚል መልዕክት አለው፡፡ እውነት ነው ቀን እየቆጠሩ የሚደረግ ሆይ ሆይታ እንጀራ አይሆንም፡፡ የዚያ ታሪክ ሰሪ ሕዝብ ሐረግ ነገ የራሱን አሻራ እንዲያስቀምጥና ታሪክ እንዲሰራ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ በዚህ የተነሳ የመንግስት ባለስልጣናት በየደረጃው ለቁጥር በሚያታክት የመሰረት ድንጋይ ሕብረተሰቡን ዋሽተዋል፡፡ የመሰረት ድንጋይ ብዛት ዳቦ አልሆን ያለው ማህበረሰብ ፊቱን ቢያጠቁር እንደምን ይፈረድበታል፡፡
ስህተቱ በመንግስት በኩል አቅምን ካለማወቅ የመጣ አድርጎ ብቻ ማየት ተገቢ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም በአገሪቱ የመንግስታዊ ስርዓቱ አመጣጥ እኔ ነኝ የሰራሁልህ፡፡ እኔን ብቻ ውደድ እና በእኔ ተመካ የሚል የተሳሳተ እምነትን በማህበረሰቡ ላይ ማስፈን ከመፈለጉ የተነሳ አገራዊ ሀብትና መኩሪያ የሆኑ ነገሮችን ያለምህረት ያጠፋል፡፡
የአድዋ በዓልን በፉከራ ከማክበር ያለፈ ማህበረሰቡን የሚጠቅም ፕሮጀክት የመስራት ቁርጠኛ ፍላጎት በመንግስት በኩል ስለመኖሩ ያጠራጥራል፡፡ የአድዋ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ ለቪኦኤ የአማርኛው ዝግጅት ክፍል እንደገለጸው ባለፉት አስር ዓመታት ብቻ የአድዋን ድል ለማሰብ ይሰራሉ ተብለው የታሰቡ የተለያዩ አስራ ሁለት ፕሮጀክቶች የመሰረት ድንጋዮች የተጣሉ መሆናቸውን አስታውሰው፤ እስከ አሁን ድረስ የተጀመረ አንድም ነገር አለመኖሩን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
‹‹ የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ›› ይል ነበር ያገሬ ሰው፡፡ በተናገረው እና ከአንደበቱ በወጣው ቃል ከሚያፍር አለያም ቀላባይ ሆኖ ከሚገኝ የወለደውን የአብራኩን ክፍይ ቢያጣ እንደሚመርጥ ከአባቶቻችን ልንማር በተገባ ነበር፡፡ የእኛዎቹ መሪዎች ባህሪ ግን የውሃ ሙላት አይነት ነው፡፡ በትኩሱ በስሜት ተገፋፍተው ቃል ይገቡና ውለው ሲያድሩ መቋጫው ያጥራቸዋል፡፡ የሚገርመው ደግሞ አንዱ ከሌላው ተሽለው አለመገኘታው ነው፡፡
ከአገር ውስጥ መሪዎች እስከ ባህር ማዶዎቹ በቃል የሚሸነገለው የዓድዋ ፕሮጀክቶች አስታዋሽ ማጣታቸውን የሰበረ አንድ ክስተት ለመሃላ ያህል ጭልጭል በማለት ላይ ይገኛል፡፡ ይኸውም በፊንፊኔዋ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በመገንባት ላይ የሚገኘው የአድዋ ድልድይ ነው፡፡ አንተንም ፕሮጀክቱንም ከአይን ይጠብቅህ ቢባል የሚያንስበት አይሆንም፡፡
እኛ አንቀበላቸውም እንጂ እኮ የአድዋን ድል በድልነቱ ሳይሆን በመከኑ ፕሮጀክቶቹ ትዝ እንዲለን ወይም እንድናስታውሰው ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ በማይበላ የቃል ተስፋ ወይም በመሰረት ድንጋይ ድርደራ ጀግንነት እንደማይገለጽ ኧረ ለመሪዎቻችን ማን በነገረልን፡፡ እኔምለው ቤተሰቦቻቸውንም ልክ እንደእኛ ይዋሿቸው ይሆን?
የቀድሞው ፕሬዚደንት ግርማ ወ/ ጊዮርጊስ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የዩጋንዳው ዩዮሪ ሙሴቪኒ፣ የአፍሪካ ሕብረት የአንድ ወቅት ምክትል ሊቀመንበር ፓትሪክ ማዜማካ፣ የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊዎች እና ሌሎቹም ባለስልጣናት በተለያዩ ጊዜያት የመሰረት ድንጋዮችን አስቀምጠው መሬት መታጠሩ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
በአለም የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ትልቅ ቦታ ባለው እና ኢትዮጵያን ከቅኝ ገዥዎች በታደገው በዚህ የአድዋ ድል ላይ መቀለድ ግን በእውነቱ ዋጋ እንደሚያስከፍል መሪዎቻችን በግልጽ እንዲያውቁት ማድረግ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡
ሁነቱ በተካሄደበት አድዋ ድሉን ያስታውሳሉ ተብለው ከመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ ካልዘለሉት ፕሮጀክቶች መካከል የፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ፣ የጀግኖች መታሰቢያ ሐውልቶች፣ ፓርኮች፣ ቤተመዘክሮች፣ የብሔር ብሔረሰቦች ሙዚየም፣ የወጣት ማዕከላት እና ሌሎችም እንደሚገኙበት የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮን መረጃ ጠቅሶ ቪኦኤ ገልጾ ነበር፡፡
የአድዋ ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቱሪዝም መስህብ ባለሙያው አቶ ሐይላይ ታደሰ፤ የአድዋ በዓል በሚከበርባቸው ወቅቶች በሚፈጠሩ ግለቶች የሚቀመጡ የመሰረት ድንጋዮች አስታዋሽ እንደሌላቸው ገልጸው ነበር፡፡ የሚገርመው የፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲን ፕሮጀክት መሰረት ድንጋይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከአፍሪካ መሪዎች ጋር የመሰረት ድንጋይ ሲያስቀምጡ ድንጋይ አትደርድሩልን፡፡ እስካሁን ያስቀመጣችሁትን መጀመሪያ በሰራችሁ፡፡ አካባቢውንም ማህበረሰቡንም የሚጠቅምና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ የሚያስገኝልን እንጂ ለፖለቲካ ፍጆታ ድንጋይ ስትተክሉ አትኑሩ በሚል ሰፊ ሐሳብ ተነስቶባቸው ነበር፡፡ እርሳቸውም ምንም ስጋት እንዳይገባቸውና ይሄ እንደሌሎች እንደማይሆን በጀት ጭምር እንደተያዘለት ገልጸው እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
አርሶ ከሚበላበትና ልጆቹን ከሚያሳድግበት መሬት ተነስ ተቀመጥ ሲባል የኖረው የአድዋ አርሶ አደርም ለመሰረት ድንጋይ የለቀቃቸውን ቦታዎች ተመልሶ ማረስ መጀመሩን፣ ታጥረው የነበሩትም ለተሽከርካሪ ማሰልጠኛና የእግር ኳስ ሜዳ መሆናቸውን ባለሙያው አስታውሰዋል፡፡
የአድዋን በዓል ተንተርሰው አድዋን የማይመጥኑ የውሸት (የማይተገበሩ) ቃልኪዳኖች መግባት የጥቁር ሕዝቦች አሻራ ያረፈበትን አድዋን ክብር የማይመጥን ነው:: ለትውልዱም የሚያስተላልፈው መልዕክት ርባና የለውም በመሆኑም መሪዎቻችንን ቀልባቸውን ይመልስላቸው፤ ለወጣቶችም የአያቶቻችንን ወኔ ይስጣቸው፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 25/2012
ሙሐመድ ሁሴን