
አዲስ አበባ፡- ለቻይና ባለሀብቶች አገልግሎት በመስጠት በኩል ከቋንቋ ጋር ተያይዞ ይታይ የነበረውን ውስንነት ለመፍታት አገልግሎት መስጠት የጀመረው የቻይኒዝ ዌብ ፓርታል የሀገሪቱ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ሲፈልጉ በቂ ዝግጅት አድርገው እንዲመጡ እያስቻለ መሆኑን ተገለፀ።
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ኃይሉ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ወደ ኢትዮጵያ ከሚመጡ ባለሀብቶች አብዛኛዎቹ የቻይና ባለሀብቶች ናቸው። ባለሀብቶቹ አሁንም በስፋት እየመጡ ሲሆን፣ በቀጣይም ይሄው እንደሚቀጥል ይጠበቃል።
ኮሚሽኑ በሀገራችን ሰፊ ተሳትፎ ላላቸው ለእነዚህ ባለሀብቶች የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አሰራር ዘርግቶ እየሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣በቋንቋ በኩል ያለውን ውስንነት ለመፍታት የሚያስችል የቻይኒዝ ዌብ ፓርታል ገንብቶ በመንደሪን ቋንቋ መረጃዎች እንዲደርሳቸው እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
አሰራሩም የቻይና ባለሀብቶች ስለ ኢትዮጵያ አጠቃላይ የኢንቨስትመንት አንቅስቃሴው፣ የኢንቨስትመንት እድሎች፣ ወዘተ መረጃ በቀላሉ እንዲያገኙ እያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ አሰራር ከመጀመሩ በፊት ኮሚሽኑ ለቻይናውያኑ ባለሀብቶች በእንግሊዝኛ መረጃዎችን ያደርስ አንደነበር አስታውሰው፣ ከጀመረም ወደ አንድ ዓመት እንደሚሆነው አመልክተዋል። በኮሚሽኑ ዌብ ፖርታል ላይ ያለውን የኢንቨስትመንት መረጃ በሙሉ ቻይናውያኑ በቋንቋቸው እንዲያገኙት በቻይኒዝ ዌብ ፖርታል ላይ መጫኑን ገልጸዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ ያሉት የኢንቨስትመንት ዘርፎች ምን ምን ናቸው፤ኢትዮጵያ በየትኞቹ ዘርፎች ላይ ትልቅ አቅም አላት፤ ኢትዮጵያን ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ ያደረጋት ምንድን ነው፣ ወዘተ. የሚሉትን በአጠቃላይ በዝርዝር የሚያ ሳይ መረጃ ነው በመንደሪን ቋንቋ ተተርጉሞ እንዲያገኙት የተደረገው።
ለእዚህ እንዲረዳም ቻይናዊ ባለሙ ያም በመቅጠር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በባለሙያው አማካይነት የማስተዋወቁ ስራም በቋንቋቸው እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።ይህ ስራ ቻይናዎቹ ወደ ኢትዮጰያ ሲመጡ ከቋንቋ ጋር በተያያዘ ምንም አይነት ክፍተት እንዳይፈጠርባቸው ማድረግ ማስቻሉንም አስታ ውቀዋል።
በርካታ የቻይና ባለሀብቶች ዌብ ፖርታሉን እየተጠቀሙበት ስለመሆኑ መረጃው አለን ያሉት አቶ መኮንን፣‹‹እኛም ጋ ሲመጡ በአንግሊዝኛ የተዘጋጀውን ሳይሆን በሀገራቸው ቋንቋ የተዘጋጀውን ዌብ ፓርታል እየተጠቀሙ እንደሚመጡ ተረድ ተናል።›› ብለዋል ።አሰራሩ በሀገራቸው ሆነው ኢንቨስት ለማድረግ በቅድሚያ የሚያስፈልጋቸውን እንዲያውቁ እና ለዚህም ዝግጅት አርገው እንዲመጡ ማስቻሉን አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2012
ኃይሉ ሣህለድንግል