የዓድዋ 124ኛ ዓመት በዓል ነገ በመላው ሀገሪቱ በታላቅ ድምቀት ይከበራል። ዓድዋ ሲነሳ የኢትዮጵያውያን አንድነት ፣ ጀግንነት ፣ ለጠላት ጦር በአይበገሬነት የሠሩት ጀብዱ ሁሌም ይነገራል፤ ይዘከራል። ለሀገራቸው ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካዊያን ጭምር የሚያኮራ የነፃነት ድል የተጎናጸፍንበት ነው።
ጥቁር ለነጭ አልገዛም ብሎ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ፣ የሰለጠነ ወታደር አሰልፎ የመጣውን የጣሊያንን ጦር የረታበት ትልቅም ታሪክ የተመዘገበበት ነው። ይህ የድል ታሪክ ጥቁሩን ብቻ ሳይሆን ነጮችም ራሳቸውን ዞር አድርገው እንዲያዩ የመጀመሪያውን የእምቢተኝነት መንገድን የከፈተ ከጥቁሮች ነፃነት ያለፈ የድል ታሪክ ነው።
በዚህ የጦርነት አውድ ሴት ወንድ፤ ቋንቋና ዘር፣ ሃይማኖት ሳይል ልዩነት ያልተደረገበት ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት የተመመበትና የድል ባለቤት የሆነበት በዓል ነው። ዛሬም ድረስ በዓለም ደረጃ የምንደነቅበት አኩሪ ታሪካችን ነው። ለነፃነት ታግለን ነፃነታችንን አስከብረን በድሉ ብስራት እነሆ 124 ዓመታትን አስቆጥረናል።
በዓድዋ ጦርነት ሁሉም ሰው የተሳተፈበት ቢሆንም የሴቶች ተሳትፎ ከፍተኛ ነበር። ሴቶች አኩሪ ጀብድ የሠሩበት፣ ጥበበኞች መሆናቸውን ያስመሰከሩበት እንደነበር ይታወሳል። ጦሩን በፊት አውራሪነት ሲመሩ የነበሩት እቴጌ ጣይቱ ብጡል የጠላት ጦር እንዲንበረከክ የመጀመሪያው የጦር ፊታውራሪ በመሆን አኩሪ ታሪክ ሠርተዋል።
ለኢትዮጵያውያን ድል ማድረግ ትልቅ አስተዋጽዖ ያደረጉት ጣሊያኖች መቀሌ ምሽግ በተሸሸጉ ጊዜ ይህንን ሁኔታ የተገነዘበችው እቴጌ ጣይቱ የጣሊያኖችን የውሃ ምንጭ የነበረውን ስፍራ በራሳቸው ጦር በማስከበብና የጠላትን የውሃ ምንጭ በማቋረጥ የጠላት ጦር በውሃ ጥም እንዲረታ በማድረግ የሠሩት ሥራ ተጠቃሽ ነው። ይሄ የእቴጌ ጣይቱን ብልሀት ያሳየ ነበር።
ሌላው ለምሳሌ ካልተነገረላቸው ጀግንነታቸው መካከል እቴጌ የውጫሌን ውል ሲቃወሙ፣ “እኔ ሴት ነኝ፤ ጦርነት አልወድም። ግን እንደዚህ ዓይነት ውል ከምቀበል ሞትን (ጦርነትን) እመርጣለሁ” በማለት አፄ ምኒልክን ለጦርነት አነሳስተው ። ይሄ የእቴጌ ጣይቱ ቃል የመጀመሪያውን ጦርነት ያስጀመሩ “ጀነራል” እንድንላቸው ያስገድደናል። ለራሳቸው ባለቤታቸውን ተከትለው የዘመቱ በርከታ የሴት ሰራዊት አባላትን ያስከተሉ ሦስት ሺህ ጠብ መንጃ እና 600 ፈረስ እንደነበራቸው ጸሐፍት ይጠቅሳሉ።
የዓድዋ የድል በዓል ሲታሰብ ከጥቂት ተጠቃሽ ሴቶች በስተቀር የወንዶቹ ጀግንነት ጎልቶ ይሰማል። ሆኖም ግን እስከ ዛሬ ከተካሄዱ የጦርነት አውዶች ሁሉ በዓድዋ ጦርነት ላይ የተሳተፉ ሴቶች ቁጥር እጅግ በርካታ ነው። የታሪክ መዛግብት እንደሚያስነብቡት በዓድዋ ጦርነት ወቅት ከ20 ሺህ እስከ 30 ሺህ የሚደርሱ ሴቶች ተሳትፈዋል።
ትጥቅና ስንቅ በማዘጋጀትና በማቀበል እንዲሁም በጦር ሜዳው አብስሎ በመመገብ ፣ ቁስለኛ በማከም፣ ስሜት ቀስቃሽ ፣ ወኔ ሰጪ ዘፈኖችን በማቅረብ ለወንዶቹ ብርታት በመሆን ሠርተዋል። በአማካሪነት፣ በሰላይነት፣ በአስተርጓሚነት ሲሠሩ ሌላው ቀርቶ የመሳፍንት ወገን የሚባሉ ሴቶች ከአገልጋዮች ጋር እኩል በመሰለፍ ለአገር ሲሆን የመደብ ልዩነት ቦታ እንደሌለው አስመስክረዋል። ይሄ የሴቶች ተሳትፎ ባይኖር ምናልባት በጦርነት የማሸነፍ ታሪክ ላይኖር ይችላል። ምክንያቱም ሳይበላ የሚዋጋ አልነበረም።
ዛሬም ድረስ ሴቶች በተለያየ ሙያ ተሰማርተው አኩሪ ታሪክ በመሥራት ላይ ናቸው። ቀደም ሲል ሴቶች ያለ ቀለም ትምህርት፣ በልበ ቅንነት፣ በሀገር ወዳድነት በሠሩት ጀግንነት ታሪክ ያስታውሳቸዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሴቶች በተለያየ የስልጣን ደረጃ ተቀምጠው ሀገራቸውን ከድህነት ለማውጣት ያለሰለሰ ጥረት እያደረጉ ናቸው።
አመራር በመስጠት ፍትህ እንዳይጓደል ዜጋ እንዳይበደል ከወንዶች እኩል ተሰልፈው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ ናቸው። በሀገራችን ሰላም እንዲሰፍን ዴሞክራሲ እንዲጎለብት በሁሉም መስክ ከፊት ተሰላፊ ሆነዋል። እነዚህን ሴቶች ማክበርና ማድነቅ እንዲሁም ጀግንነታቸውን መዘከር ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 22/2012