
አዲስ አበባ:- ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ አሜሪካ ያወጣችውን መግለጫ ቅሬታ እንደፈጠረባት እና እንደማትቀበለው አስታወቀች።
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ ትናንት ከመንግሥት የተሰጠው መግለጫ እንደሚያመለክተው፤ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአሜሪካ የግምጃ ቤት ዲፓርትመንት ሴክሬታሪ በየካቲት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበትን ስብሰባ ተከትሎ የወጣውን የፕሬስ መግለጫ በከፍተኛ ቅሬታ ተመልክተውታል። ስብሰባው የተካሄደው
ኢትዮጵያ አስቀድማ ለግብጽ፣ ለሱዳን እና ለአሜሪካ ስብሰባው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ አሳውቃ እያለ ነው፡፡
የግድቡ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በመርሆዎች መግለጫ ስምምነቱ መሠረት የግድቡን ሙሌት ከግንባታው ትይዩ በፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም እና ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርሆዎች መሠረት የምታከናውን መሆኑን ጠቅሶ ኢትዮጵያ የግድቡን የመጀመሪያ ሙሌት እና የውሃ አለቃቅ መመሪያ እና ደንብ ለማዘጋጀት የሚደረገው ድርድር ተጠናቋል በሚል የተሰጠውን መግለጫ አትቀበልም ብሏል።
በዋሽንግተን ዲሲ የግብጽ ዐረባዊት ሪፐብሊክ ፈርሞበታል የተባለው “ረቂቅ” የሦስቱ አገራት የድርድርም ሆነ የሕግ እና የቴክኒክ ቡድኖች ውይይት ውጤት አለመሆኑን የጠቀሰው መግለጫው የቴክኒክ ጉዳዮች ድርድሩም ሆነ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅቱ ላይ የሚደረገው ድርድር አልተጠናቀቀም፡፡ ኢትዮጵያ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሌት እና የውሃ አለቃቅ መመሪያ እና ደንብ የሚዘጋጀው በሦስቱ አገራት ብቻ እንደሆነ አቋሟን ቀድማ አሳውቃለች።
ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በሚያውቁት እና በተስማሙበት እንዲሁም በመርሆዎች መግለጫ ስምምነት መርህ አንቀፅ ስምንት አድናቆታቸውን በሰጡት ሂደት መሠረት ሁሉንም የግድብ ደህንነት የሚመለከቱ ጉዳዮች በዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ምክረ ሐሳብ መሠረት የተሰጡትን ምክረ-ሐሳቦች መፈፀሟን እንደምትቀጥልም በመግለጫው ተመልክቷል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሌት እና የውሃ አለቃቅ መመሪያ እና ደንብን ለማዘጋጀት ቀሪ መሠረታዊ ልዩነቶችን ለመፍታት ኢትዮጵያ ከግብጽ ዐረባዊት ሪፐብሊክ እና ከሱዳን ሪፐብሊክ ጋር የጀመረችውን ሂደት ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗንም መንግሥት አስታውቋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 22/2012