
• የህዳሴግድቡ የኢትዮጵያ ፍላጎትና ጥቅም በሚጠብቅ መልኩ እንደሚሠራ አስታወቀ
• የቋንቋ ልማትና አጠቃቀም ፖሊሲ በሥራ ላይ እንዲውል ወሰነ
• የኮሮና ቫይረስ መከላከልና ክትትል የሚያደርግ ብሔራዊ የሚኒስትሮች ኮሚቴ አቋቋመ
አዲስ አበባ፡- የህዳሴ ግድቡ የኢትዮጵያ ፍላጎትና ጥቅም በሚጠብቅ መልኩ እንደሚሠራ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስታወቀ ። ምክር ቤቱ በ80ኛ መደበኛ ስብሰባው የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ገልጿል፡፡
ምክር ቤቱ ትናንት ባካሄደው ስብሰባ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ማንኛውም ነገር የኢትዮጵያ ፍላጎትና ጥቅም በሚጠበቅ መልኩ ብቻ እንደሚከናወንና የብሔራዊ ጥቅም የሚነካ ድርድር የኢትዮጵያ መንግሥት እንደማያደርግ አስታውቋል፡፡
በቋንቋ ልማትና አጠቃቀም ረቂቅ ፖሊሲ ላይ የተወያያ ሲሆን፤ የቋንቋ ፖሊሲውን ማዘጋጀት አስፈላጊ እንደሆነ አምኖበታል፡፡ የቋንቋ ፖሊሲው
መኖር የቋንቋ መብት በሕገ መንግሥቱ እውቅና እንዲያገኝ ያስችላል፡፡ በቋንቋ አጠቃቀም ፣ ልማትና ጥበቃ ረገድ የሚነሱ ችግሮች በአሠራር እንዲፈቱ ያደርጋል ብሏል፡፡
የቋንቋ ፖሊሲ መታየት ያለበት ከመብትና እኩልነት አንፃር ብቻ ሳይሆን እንደ አገር ከምንፈልገው አንድ የጋራ ማህበረሰብ ግንባታና ከምንጋራው ራዕይ ጋር የተቆራኘ ጭምር በመሆኑ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያዘጋጀው ረቂቅ የቋንቋ ልማትና አጠቃቀም ፖሊሲው አንዳንድ ማስተካከያዎች ተደርገውበት በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ መወሰኑን አመልክቷል፡፡
እንዲሁም ምክር ቤቱ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ፣ክትትልና ብሔራዊ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ማቋቋም ላይ የተወያየ ሲሆን፤ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚመራና ስድስት አባላት ያሉት ኮሜቴ አቋቁሟል። አባላቱም ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ አቶ አህመድ ሸዴ፣ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ እንዲሁም ዶ/ር ሊያ ታደሰ ናቸው።
ምክርቤቱ ሌላው የተወያየው የአርብቶ አደር ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ላይ መሆኑን መግለጫው ጠቅሶ፤ የአርብቶ አደሩን ህዝብ ለየት ያለ አኗኗር፣ የኑሮ መሰረትና ሥነምህዳር ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በየሴክተሩ ተበታትነው ሲተገበሩ የነበሩ ፖሊሲዎችን ወደ አንድ በማምጣት በተደጋጋፊነት ለመስራትና የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንዲሁም አገሪቱ አሁን ከደረሰችበት የእድገት ደረጃ አኳያ በመቃኘት ሁሉም የልማት ሀይሎች ለአርብቶ አደሩ መሻሻል የድርሻውን በተጠያቂነት መርህ መወጣት እንዲችሉ የሰላም ሚኒስቴር ያዘጋጀውን የአርብቶ አደር ልማት ረቂቅ ፖሊሲ በጥልቀት አይቶ አንዳንድ ማስተካከያዎች በማድረግ ሥራ ላይ እንዲውል መወሰኑ ተገልጿል፡፡
እንዲሁም የቆላ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል 65‚330‚000.00 ኤስ.ዲ.አር. የብድር ስምምነት ላይ የተወያየ ሲሆን፤ የብድር ሥምምነቱም የተደረገው ከአለምአቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ጋር ሲሆን አላማውም የአርብቶአደርና ከፊል አርብቶአደር ማህበረሰቦች የኑሮ መሰረት እንዲሻሻል ለማድረግ ነው።
ብድሩ ምንም አይነት ወለድ የማይታሰብበት፣ በረጅም ዓመታት የሚከፈልና ከአገሪቱ የብድር አስተዳደርና ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣም በመሆኑ አዋጁ እንዲጽድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት እንዲተላለፍ መወሰኑን መግለጫው ጠቅሷል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 22/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው