
የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካና የጥቁር ህዝቦች ድል እንደሆነ የሚነገርለት የዓድዋ ድል 124ተኛ ዓመት እየተዘከረ ይገኛል። በድሉ ዋዜማ ብዙ ሁነቶች ከተከናወኑባቸውና ዘመን ተሻጋሪ ገድል ከተሠራባቸው ከተሞች መካካል ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ወረኢሉ ከተማ አንዷ ናት።
ከተማዋ ከድሉ በፊት የዓድዋው ንጉሥ ዳግማዊ ምኒልክ መቀመጫም ነበረች። በኋላም ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ለሸዋ ህዝብ መሰባሰቢያነት የክተት አዋጅ የታወጀባትና ንጉሡን ጨምሮ የሸዋ መኳንንትና የጦር አበጋዞች ወታደሮቻቻውን ይዘው አገር ለማዳን ጉዞ የጀመሩባትም ነች።
የወረኢሉ ህዝብ ከአዲስ አበባ የተነሳውን የዓድዋን በዓል አክባሪ ለመቀበል ዝግጅቱን አጠናቋል። የተለያየ የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ የለበሱ ተማሪዎች በአስፋልቱ ቀኝና ግራ ተሰልፈው ያጨበጭባሉ። ልብሰ ተክህኖ ለብሰው ጥላ የያዙ ካህናትና የእስልምና እምነት አባቶች ዝግጅቱን ኢትዮጵያዊ ማንነትን አጎናፅፈውታል፤ አንድ አዝማሪ በሰልፈኛውና በታዳሚው መካከል እየተንጎማለለ ፉከራና ቀረርቶውን ያንቆረቁረዋል።
በዚህ ድምቀት የታጀቡት የዓድዋ ድል በዓል ለማክበር የታደሙት እንግዶች በ1220 በንጉሥ ነዓኩቶ ለአብ በተመሰረተው፤ ከዓድዋ ድል በኋላም በዳግማዊ ምኒልክ እንደገና ወደ ታነፀው ደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ሲገቡ ለማየት የሚናፍቁትን ኢትዮጵያዊ ፍቅር በገሐድ ይመለከቱ ጀመር።
በጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ያለው ድባብ ከወትሮው የተለየ ነበር። ነጫጭ ነጠላ የለበሱ ሴቶችና ወንዶች ይታዩበት የነበረው የቤተክርስቲያኑ ቅፅረ ግቢ ዛሬ ሂጃብ በጠመጠሙ የእስልምና እምነት ተከታይ ሴቶች ተሞልቷል። ለውትሮው በካህናትና ዲያቆናት ይከበብ የነበረውም ዓውደ ምህረት ዛሬ የእስልምና እምነት ተከታዮችና ታላላቅ አባቶች ከካህናቱ በስተቀኝ ታድመውበታል። ምክንያቱም ዝክረ ዓድዋ ነው።
«ዛሬ ከጣሊያን ወረራ የባሰ ችግር ከፊታችን ተደቅኗል፤ ይህንን ክፉ ቀን ለመሻገር የዓድዋ ድል ጥሩ ትምህርት ይሆነናል» ያሉት የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት አቶ መሐመድ አማን ናቸው። እንደ አቶ መሐመድ ገለፃ ጣሊያን ኢትዮጵያን ሲወር የእምነትና የዘር ልዩነት አድርጎ አልነበረም።
ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን እንጂ። አባቶቻችንና አያቶቻችንም ዘርና ሃይማኖት ሳይለዩ በአንድነት ተሰልፈውና አንድ መአድ ቆርሰው ወረራውን አሸንፈዋል። የአሁኑ ትውልድም ዛሬ የሚታየውን በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በጎሳ የመከፋፈል ነገር በድል ሊወጣ ይገባል። በተለይ ወጣቱ ከውጭም ከውስጥም ሊያናክሱት ለሚፈልጉ ሃይሎች ዕድል መስጠት የለበትም ይላሉ።
በተመሳሳይ የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት ቆሞስ አባወልደ ትንሳይ «ዛሬ ያለብን ችግር ጣልቃ ገብነት አለበት ቢባልም የምንጀምረውና የምናቀጣጥለው ራሳችን ነን። ስለዚህ መፍትሄውም ሊገኝ የሚችለው ከእኛው ዘንድ ነው።
ስለዚህ ርዕስ በርዕስ መደማመጥና መከባበር ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያዊ መሆን ብቻ በቂ ነው። ለፍቅር ለመቻቻል ለአብሮነት ጊዜና ትኩረት ብቻ ሳይሆን ራሳችንንም ልንሰጥ ይገባል” ይላሉ።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ዶክተር ሂሩት ካሳ ያስተላለፉት መልዕክት ይሄው ነው። «አያቶቻችን በጦር ሜዳ ውሎ ያስመዘገቡትን ዓለም ያደነቀው አንፀባራቂ ድል የአሁኑም ትውልድ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ዘርፈ ብዙ ችግር ለማላቀቅ የሞራል ስንቅ የሚጨብጥበት ነው።
ይህንን ማድረግ ሲቻል ደግሞ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ችግር ተላቃ እንደምንመኘውና እንደምናስበው እንደ ዓድዋ ተራራ ከፍ ከሚለው የብልጽግናና የሰላም ማማ መድረስ ትችላለች።» ብለዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 22/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ