ሱራ ሽቅብ ሽቅብ ያቃስታል። ግዝፈቱ ያስጨንቀዋል። ልብስ አይበቃውም። የጫማው ቁጥር 48 ነው። የትከሻው ስፋት የሰውነቱ ግዝፈት የቁመቱ ርዝመት የሰማይ ስባሪ አስመስለውታል። አባ ግድየለሽ ሱራ ወግ ጨዋታ ይወዳል። ሰው አያስቀይምም። ውፍረቱ አስፈሪ አስደንጋጭ ነው።
የሰፈሩ ሰው ልጆች ሲያለቅሱና ሲረብሹ ዋ ሱራን ነው የምንጠራው ሲባሉ ያውቁታልና በፍርሀት ርደው ጭጭ ነው የሚሉት። ሲደሰትም ሲከፋም ሱራ የአላህ ልጅ፤ የአላህ ወዳጅ የሚለው ነገር አለው። ለወላጆች ምነው ምነው ሕጻናቱ እንዲጠሉኝ እንዲፈሩኝ ባታደርጉ ምን አደረኳችሁ ይላል – ሱራ።
በዛ ቁመቱና ውፍረቱ ሲንጎማለል ሲታይ የሞላለት ቱጃር ይመስላል። ጫማ ሰፊው ሱራ በቀን ሰርቶ ከሚያገኘው ውጭ ምንም የለውም። እጁ ሲያጥር ደምበኞቹ ከሆኑት ሴቶች ይበደራል። የድሀ ገንዘብ አታድርገኝ ይላሉ – እማማ ጌጤ።
ከቀናት በኋላ ሴቶቹ ከች ይሉና ብር መልስ ይሉታል። አንተ ሱራ ስማ እንጂ የተበደርከውን አታመጣም፤ አላበዛኸውም እንዴ እያሉ ሴቶቹ ወገባቸውን ሲነቀንቁበት ይጨነቃል። ሂጂ እዛው ምን ወገብሽን ትሰብቂያለሽ ይላል ሱራ፤ ሶርሷራው። ተናገር ምንድነው ሂጂ እዛው አንተ አይደለህም እንዴ ስንቱን … ይሉታል። ኧረ በሕግ አምላክ ስሜን አታጥፉ አልደረስኩባችሁም ይላል እንደ ማፈር ብሎ።
ጫማው መስፊያ ጎን ያሉት እማማ ጌጤ ይቺ ሙጢ አሁን እውነት ሱራ ቢጠጋት ትተርፋለች፤ ሹል አፍ ሙጢ እንደው መቀላመድ ትወዳለች ልጄ አሉና አጉተመተሙ። የመንደሩ ሴቶቹ የተቦተረፈ ጫማቸውን ይዘው ስፋልን እያሉ የሚወስዱት ለሱራ ነው። ብዙ የሴት ወዳጆች አሉት። አንዳንዶቹ የሚበላው ቋጠር አድርገው ያመጡለታል። አላህ እናንተን ባይጥልልኝ ኖሮ ምን እሆን ነበር ይላል ሱራ። ሱራ የሰማይ ስባሪው ሲሉት እናንተ ኮስማኖች በልታችሁ አይጠጋችሁ፤ ነገር ስትበሉ ውላችሁ ታድራላችሁ ፤ታዲያ ሱራ ምን ያድርጋችሁ ይላል።
መኖሪያ ቤቱ የቀበሌ ቤት ነች። ግን ማንንም አያስገባም። ቤት ውሰደን ሱራ ሲሉት ደሞ ምን ቀራችሁ፤ ከእኔ ቤት ምን ጉዳይ አላችሁ ይላል። ቤት እየመጡ እሱ ሲሰራ እየተቀመጡ በዚህ መዘዝ ድሮ ምን እንደመጣበት ሱራ ሲያስታውሰው ይዘገንነዋል። ራሱ አብስሎ ይመገባል። አንዳንዴ በጎርናና ድምጹ ያንጎራጉራል። ሱራ የአላህ ወዳጅ… የአላህ ልጅ እያለ። ተናግረው ሊያናግሩት ሲነካኩት አሁን ከእኔ ምን ታገኛላችሁ ተውኝ ስራ የላችሁም ይላል። ጫማ መስፋቱን ይቀጥላል። ይህን ዝምታ የወረሰው በደርግ ዘመን ከደረሰበት ችግር በመነሳት ነው። በማያውቀው ነገር ሊሞት ነበር። ጫማ የሚሰፋባት አንዲት ክፍል የኪራይ ቤት ነበረችው። ከበውት የሚውሉ የሚያመሹም ነበሩ።
ፖለቲካ አይወድም። እሱ ጋ የሚገቡና የሚወጡት ወጣቶች በዛን ዘመን ኢህአፓዎች ነበሩ። ወረቀት የሚበትኑ፤ ግድግዳ ላይ ቀለም የሚቀቡ፤ በቀይ ቀለምና በቀይ ጨርቅ ሀገሩን የሚያሸበርቁ። በፌስታል አምጥተው ሱራ የማያውቀውን እቃ ወረቀት ምናምን አመጣን ሱራየ ይቺ እዚህ ጋ ትቀመጥ ሲሉት ሱራ በመጡ ሰአት ተመልሰው ይወስዱታል እያለ ጫማውን መስፋት ይቀጥላል። የሚያውቀው ነገር የለውም ምስኪኑ ሱራ። እቃቸውን አይነካም። ተጠራጥሮም አይሸፍንም። በል ሲለው ያንጎራጉራል። ሱራ የአላህ ወዳጅ የአላህ ልጅ የምትለዋ ቃል ከአፉ አትጠፋም። በዚህ ይታወቃል።
ጊዜው 1969ዓ.ም ነው። አዲስ አበባ መርካቶ አካባቢ። ሀገር ምድሩ ታምሷል። አንድ ቀን ቀበሌው የኢሕአፓ ወጣቶችን እያሳደደ ማሰር ሲጀምር እንዴ እነሱማ ተሰብስበው የሚውሉት ሱራ ጫማ ሰፊው ቤት ነው የሚል ጥቆማ አብዮት ጠባቂዎች ይሰጣሉ። ይታሰር ተብሎ ጠመንጃ ተሸክመው ሱራ ጋ ይሄዳሉ። ሱራ አይሞቀው አይበርደው አባ ግዴለሽ። እንደውም ቤቱ ይከበብ ተብሎ ከውጭ ብዙ ጥበቃዎች ይከቡታል። ሱራ ጫማውን አቀርቅሮ ይሰፋል። መሳሪያ ደግነው ዘው ብለው ገቡ። እጅ ወደ ላይ አሉት። ሱራ የአላህ ወዳጅ አለና ጠመንጃው ምን ያደርጋል ለአንድ ድሀ ጫማ ሰፊ የእኔ እጅ ስራ ይዟል ለምንድነው እጄን ወደላይ የማደርገው በእንጀራዬ ለምን መጣችሁ ይላቸዋል።
ና ውጣ አንተ ኢህአፓ አሉት። ሱራ መለሰ ምንድነው ኢሕአፓ አላቸው። እሱንማ አንተ ታውቃለህ በደምብ ትመልሳለህ አሁን እስረኛ ነህ ና ውጣ ቀበሌ እንሂድ አሉት። ተውኝ ቢል ማን ሰምቶት። እያመረሩ ሄዱ። ሌሎች ሱራ ቀበሌ ሂድላቸውና ቃልህን ስጥ ምን ትሆናለህ አሉት። ሱቁን ቆለፈና በብዙ አብዮት ጠባቂዎች ታጅቦ የሠማይ ስባሪው ሱራ ቀበሌ ጽህፈት ቤት ገባ። ግቢው ውስጥ እሱ ጋ ገባ ወጣ ከሚሉት ወጣቶች ውስጥ የታሰሩ እንዳሉ አየ። ጮክ አለና ምን ሰርቃችሁ ነው የተያዛችሁት አላቸው። አብዮት ጥበቃዎቹም ወጣቶቹም ሳቁ። ሱራ ለምርመራ ገባ። ጠያቂዎቹን ያውቃቸዋል። የጫማ ደምበኞቹ ናቸው። ጫማቸው ሲቀደድ የሚሰፋላቸው።
ሱራ አንተም አሉት። ተገረመና ምን አላቸው። ኢህአፓ አሉት። ምንድነው የምትሉት እሱን ሰውየ አላውቀውም። ቅድምም አብዮት ጥበቃዎቹ እንደሱ አሉኝ። የእኔ የጫማ ደምበኛ አይደለም። አሰርቶ አያውቅም። እኔም አላውቀውም አላቸው። ሱራ የአላህ ወዳጅ የአላህ ልጅ አለ ሰው በተሰበሰበበት።
እስኪጣራ ታስረህ ትቆያለህ አሉት። ክፉኛ አዘነ። አላህ እንደ ስራየ ይስጠኝ፤ በተንኮል ለወነጀሉኝም ፍርዱን ይስጥ አለ- ደገመና። እስር ቤቷ ውስጥ ግዙፉ ሱራ አንገቱን አዝምሞ ገባ። ታሳሪው በተጨናነቀው ቤት ውስጥ ለሱራ ተጣበው ቦታ ሰጡት። ግድግዳውን ደገፍ ብሎ እንደቆየ ድብን አድርጎ እንቅልፍ ወሰደው። ማንኮራፋት ጀመረ።
ቢጠሩት መች ሰምቶ። ለሊቱን እነዛን ልጆች ወደማይታወቅ ስፍራ ወስደዋቸዋል። ሲነቃ ልጆቹ የሉም። የሰፈሩ ሰው ሱራ ቀበሌ መታሰሩን ሲሰማ በእጅጉ አዘነ። ከፊሉ አሽሟጠጠ። ደሞ ሱራ ብሎ ፖለቲከኛ እያለ። ጠጅ ቤት መነጋገሪያ ሆነ። ሱራ ታሰረ— ሱራ ታሰረ — ባዩ በዛ። የሰፈሩ ሰው ጫማ የሚሰፋላቸው ሴቶች እየተጋገዙ ምግብ ያቀብሉት ጀመር። ቀለብ የማያገኙት እስረኞች ረሀባቸው ጠፋ። ሱራ ሱራ አሉት አቤት አላቸው። እንኳን ታሰርክ እንዲያውም መውጣት የለብህም አሉት። ተንከትክቶ ሳቀ። አንተ በመታሰርህ እስር ቤቱ ምግብ በምግብ ሆነ ሲሉት ቀበል አደረገና እኔ ፖለቲካ አላውቅም። ጫማ ሰፊ ነኝ። እኔን በሀሰት በወነጀሉኝ ሰዎች ላይ አላህ ፍርድ ይስጥ፤ ሱራ የአላህ ወዳጅ የአላህ ባሪያ አለና አይኖቹ በእምባ ተሞሉ። አይዞህ ሱራ አሉት። አይዞህ አይዞህ ሱራ።
ለሊት በቀበሌያቸው አካባቢና ዙሪያ የቀለጠ ተኩስ ተሰማ። እስረኞቹ በተኙበት ይሰማሉ። ሱራ አላህ –አላህ ይላል። የመትረየሱ ድምጽ ተረረረረረም ሲል ሱራ አላህ ድረስ፤ የታሰሩት ልጆች አውጣን አውጣን ሆነ። አይነጋ የለም በጭንቅ ነጋ። ጠዋት ለሽንት ሊወጡ ሲሉ ሱራ ነበር የቀደመው። ያገኛቸውን ሰዎች ምንድነው ጉዱ አላቸው። መጥተው ፈጅተውን ሄዱ፤ አመለጡ አሉት። እነማን ናቸው አላቸው – ሱራ። ኢህአፓዎቹ ናቸዋ አሉት። ሰው ተጎዳ ብሎ ጠየቀ። ምን ሰው ተረፈ ብለህ ነው። በቀደም አንተን ከሱቅህ አስረው ያመጡህ በሙሉ ሞተዋል አሉት። ምን አለ ሱራ ደንግጦ። ደገመና ሱራ የአላህ ወዳጅ የአላህ ልጅ። እቺ ኢህአፓ የምትሏት አላህ ነች እንዴ አለ ሱራ። ሰዎቹ በሳቅ አሽካኩ። ሱራ ሱራ።
ወንድወሰን መኮንን
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2012