ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በመገናኛ ብዙኃን ከተለመዱ ዜናዎች መካከል በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በሰዎች ሲዘዋወር በቁጥጥር ስር የሚውለው ገንዘብ ጉዳይ አንዱ ሆኗል፡፡ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በቁጥጥር ስር የዋለው ገንዘብ የአገር ውስጥና የውጭ አገራት ገንዘቦችን ያካተተ ነው፡፡
ድርጊቱ ደጋግሞ ከመከሰቱና በአገሪቱ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ሊያስከትለው ከሚችለው ተፅዕኖ አንፃርም ችግሩን በቀላሉ መመልከት እንደማይገባና መንግሥት ዘላቂ የመፍትሔ ዕርምጃዎችን እንዲወስድ እየተጠየቀም ይገኛል፡፡
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ዶክተር አረጋ ሹመቴ በሕገ-ወጥ ገንዘብ ዝውውሩ መንስኤዎች፣ በሚያስከትላቸው ጉዳቶችና ችግሩን ለመቆጣጠር መወሰድ ስላለባቸው የመፍትሔ ዕርምጃዎች ላይ የሰጡንን ማብራሪያ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
የችግሩ መንስዔዎች
ግለሰቦች ደብቀው ያቆዩትን ገንዘብ ሕጋዊ ባልሆነ መልኩ ለማዘዋወር ምክንያት ከሚሆናቸው ነገሮች መካከል አንዱ የፖለቲካ አለመረጋጋት (Political Instability) ነው፡፡ የፖለቲካ መረጋጋት በማይኖርበት ጊዜ ሰዎች ለገንዘባቸው ደህንነት መተማመኛ ዋስትና በመስጋት ገንዘባቸውን ይደብቃሉ፤ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድም ያንቀሳቅሳሉ፡፡
ከዚህ ባሻገርም የተሻለ ትርፍ ለማግኘት በማሰብም ገንዘብን የመደበቅና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የማንቀሳቀስ ተግባር ያከናውናሉ፡፡ ለአብነት ያህል ኢትዮጵያ ውስጥ የተሻለ ትርፍና የኢንቨስትመንት ውጤት ማግኘት ካልቻሉ ወደ ሌላ አገር ወስደው ማስቀመጥ ይፈልጋሉ፡፡ ሀብት ማሸሽ (Capital Outflow) እንዲፈጠር ምክንያት ከሚሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ ይኸው ድርጊት ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ የሽግግር ጊዜ በመሆኑ ሰዎች ለገንዘባቸው ደህንነትና መተማመኛ በማጣት ስጋት ላይ ይወድቃሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ባለሥልጣናትን ተገን አድርገው ሲሠሩ የነበሩ ግለሰቦች ገንዘብ ያሸሻሉ፡፡
ጉዳቶች
ገንዘብን መደበቅና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ማዘዋወር የሚያስከትላቸውን ጉዳቶች በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የአገር ውስጥ ገንዘብ (ብር)ን መደበቅና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ማዘዋወር ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች መካከል አንዱ ሰው ሠራሽ የሆነ የገንዘብ እጥረት እንዲፈጠር ማድረጉ ነው፡፡ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ መዘዋወር ያለበት ገንዘብ እንዲደበቅ በማድረግ በሕጋዊ መንገድ መንቀሳቀስ ያለበት ገንዘብ እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በገበያ ላይ የሚሽከረከረውን ገንዘብ (Currency in Circulation) እንዲሁም በተፈለገ ጊዜ ሊወጣ የሚችለውን ገንዘብ (Demand Deposit) በጣም ይጎዳቸዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ የዋጋ ንረትን ያስከትላል፡፡
ሕጋዊ ያልሆነ የንግድ ውድድር እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ገንዘብ የደበቁና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚያዘዋውሩ አካላት በንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ላይ ሲሳተፉ የንግድና የጨረታ ስርዓቱ ይዛባል፡፡
የዋጋ ንረት የሚከሰትበት ሌላ አጋጣሚም አለ፡፡ ገንዘብን መደበቅና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ማዘዋወር የገንዘብ ሽክርክሪትን ያዛባል፡፡ ድርጊቱ በእያንዳንዱ ግለሰብ እጅ የሚዘዋወረውን ገንዘብ ቀንሶ የዋጋ ንረት እንዲከሰት በማድረግ መንግሥትን ትክክለኛ ወዳልሆነ የፖሊሲ አቅጣጫ ሊመራው ይችላል፡፡ መንግሥት ገንዘብ የለም በሚል እሳቤ ገንዘብ ታትሞ ወደ ኢኮኖሚው እንዲለቀቅ ሊያደርግ ይችላል፤ በዚህ ጊዜ ገንዘብ የደበቁና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚያዘዋውሩ አካላት የደበቁትን ገንዘብ ወደ ገበያ (ወደ ኢኮኖሚው) ያወጡና የሁለቱ ግጭት ውጤት የኑሮ ውድነቱን ያባብሰዋል፡፡ መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን የገንዘብ መጠን ገምቶ አዲስ ገንዘብ አሳትሞ ወደ ገበያው ሲያስገባው የዋጋ ንረቱን በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ያደርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ የመንግሥትን የገንዘብ ፖሊሲ በመጉዳት የፖሊሲ እቅድና ትግበራ መዛባትን ያስከትላል፡፡
የውጭ አገር ገንዘብን መደበቅንና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ማዘዋወር የአገር ውስጥ ገንዘብን ከመደበቅና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ከማዘዋወር የበለጠ ጉዳት አለው፡፡ አገሪቱ ለልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች የምታውለውን ገንዘብ ይቀንስባታል፡፡ ለከፍተኛ ብድርና ዕርዳታ ይዳርጋታል፡፡ ይህ ደግሞ የአጭርና የረጅም ጊዜ ተፅእኖ ይኖረዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ሊከሰቱ ከሚችሉ ጉዳቶች አንዱ የኢንቨስትመንት እና የልማት ሥራዎች መስተጓጎልና መቀነስ ነው፡፡ አገሪቱ ዕርዳታና ከፍተኛ ወለድ ባለው ብድር ውስጥ እንድትዘፈቅ በማድረግ በልማት ሥራዎች ላይ መዋል የነበረበት ገንዘብ ብድሩን ለመክፈል መዋሉ ችግሩ በረጅም ጊዜ ከሚያስከትላቸው ተፅዕኖዎች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡
በሌላ በኩል የውጭ አገር ገንዘብን መደበቅና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ማዘዋወር በገቢና ወጪ ንግድ (Import-Export Trade) ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለማስገባት የሚያስፈልግ ገንዘብ እጥረት ስለሚከሰት አገሪቱ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ያለባትን ዕቃ እንዳታስገባ ያደርጋታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ለማካካስ ሲባል አገሪቱ ወደ ውጭ መላክ የማይጠበቅባትን ምርት በርካሽ ዋጋ እንድትልክ ያስገድዳታል፡፡
የመፍትሔ አማራጮች
የአገር ውስጥ ገንዘብን መደበቅንና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ መዘዋወርን ለመቆጣጠር ከሚያስችሉ የመፍትሔ ዕርምጃዎች መካከል አንዱ ጥብቅ ቁጥጥር ማካሄድ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአገሪቱን የገንዘብ ዝውውር (Currency Circulation)፣ ወደ ባንክ የገባውን ገንዘብ፣ ሰዎች በሚፈልጉበት ጊዜ ከባንክ ሊያወጡት የሚችሉትን ገንዘብ እንዲሁም በከበሩ ማዕድናት መልክ የሚቀመጠውን ንብረት ማወቅና መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡
ተቋማት ከባንክ የሚበደሩትንና የሚያወሩትን ገንዘብ ሊደብቁትና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ሊያዘዋውሩት ስለሚችሉ ይህን ገንዘብ መቆጣጠርና ገንዘቡን ለተበደሩት ዓላማ ማዋላቸውን መከታተል ያስፈልጋል፡፡ ለአብነት ያህል ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ባለሀብቶች ለእርሻ ልማት በሚል ጥያቄ ከባንክ ገንዘብ ከተበደሩ በኋላ በእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ ከመሰማራት ይልቅ በሪል ስቴትና በሌሎች ዘርፎች ተሰማርተው ይታያሉ፡፡ ስለዚህ መንግሥት ተበዳሪዎች ከባንክ የወሰዱትን ገንዘብ በተበደሩለት ዓላማ ላይ ማዋላቸውን መከታተል አለበት፡፡
ብድር በሚፈቀድበት ጊዜም ብድሩን በአንድ ጊዜ ከመስጠት ይልቅ በተለያየ ጊዜ (Installment System) መስጠት የሚቻልበትን አመራጭ መፍጠርም ችግሩን ለመቆጣጠር አንዱ መፍትሔ ነው፡፡
ሌላውና ብዙ ሰዎች ለችግሩ እንደመፍትሔ እያቀረቡት ያለው ዘዴ የገንዘብ ኖቶችን መቀየርን ነው፡፡ የገንዘብ ኖት ሲቀየር በቂ ጥናት ያስፈልጋል፡፡ አዲስ የገንዘብ ኖቶችን ለማሳተም ብዙ ወጪ ያስወጣል፡፡ ስለዚህ በሰዎች እጅ ያለው ገንዘብ ሳይመለስ ቢቀር ሊያደርሰው የሚችለው ጉዳት የገንዘብ ኖቶችን ለማሳተም ከሚያስፈልገው ወጪ ጋር መነፃፀር አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አሁን ጥቅም ላይ ያለው የገንዘብ ኖት ከገበያው ውጪ ሲሆን፤ እንደ ዋጋ ንረት ያሉ ኪሳራዎች ይኖራሉ፡፡ በመሆኑም የገንዘብ ኖቶችን የመቀየር ፋይዳና ውጤታማነት እነዚህ ኪሳራዎች ተደምረው ከሚያስገኙት ጥቅም አንፃር መታየት ይገባዋል፡፡ ይህ የመፍትሔ አማራጭ የአገር ውስጥ ገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር ብቻ እንደሚያገለግልም መዘንጋት የለበትም፡፡
የውጭ አገር ገንዘብን መደበቅንና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ መዘዋወርን ለመቆጣጠር መወሰድ ከሚገባቸው የመፍትሔ ዕርምጃዎች መካከል አንዱ በገቢና ወጪ ንግድ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማካሄድ ነው፡፡ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች አስፈላጊ የሚባሉና የተመረጡ መሆን አለባቸው፡፡ አገር ውስጥ መተኪያ ያላቸውና ውድ የሆኑ የቅንጦት ዕቃዎች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸው ፋይዳ የለውም፤ እንዲያወም ጉዳታቸው ያመዝናል፡፡ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማስፈፀም የሚያስችሉ ግብዓቶች አስፈላጊና አስገዳጅም ስለሆኑ ለእነዚህ ምርቶች ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡
ሌላው የመፍትሔ አማራጭ ደግሞ በገንዘብ ወጪና ገቢ ላይ ቁጥጥር ማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ከውጭ የሚላክ ገንዘብ (Remittance) አገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ከምታገኝባቸው መንገዶች አንዱ በመሆኑ በዚህ ላይ የሚደረግ ቁጥጥር ወሳኝና አስፈላጊ ነው፡፡ ከውጭ አገራት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሰዎች ምን ያህል ገንዘብ ይዘው እንደገቡ፣ መቼና የት መመንዘር እንዳለባቸው ቁጥጥር ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
ጥቁር ገበያውን መቆጣጠርና የተሻለ ጥቅም ሰጪ እንዳይሆን ማድረግም ሌላው አማራጭ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥት በገንዘብ ገበያው ውስጥ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት (ቁጥጥር) የኢኮኖሚ ስርዓቱን በማይጎዳ መልኩ ሊሆን ይገባል፡፡
አማራጭ የውጭ አገር የገንዘብ ኖቶችን መጠቀምም እንዳንድ የመፍትሔ ዕርምጃ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በዚህም ሁልጊዜም በአሜሪካ ዶላር ላይ ጥገኛ በመሆን ሊከሰት የሚችለውን ጉዳት መቀነስ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ያህል ዩሮ (Euro)ን፣ ዩዋን (Yuan)ን፣ ፓውንድ ስተርሊንግ (Pound Sterling)ን እና ሌሎች የውጭ አገር የገንዘብ ኖቶችን በአማራጭነት መጠቀም ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 3/2011
አንተነህ ቸሬ