አዲስ አበባ፡- በላሊበላ ከተማ የነበረው የዘንድሮው የገና በዓል አከባበር ለሌሎች አካባቢዎች አርአያ የሚሆኑ ተግባራት የተከናወኑበት እንደነበር የላሊበላ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የከተማው ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ስጠው ኃይሉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት የላሊበላና አካባቢው ኅብረተሰብ፣ በተለይም ወጣቶች፣ በዘንድሮው የገና በዓል አከባበር ላይ ያከናወኗቸው በጎ ተግባራት ለሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎችም በአርአያነት የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡
ወጣቶች በዓሉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የጥበቃና የፍተሻ ሥራ ከማከናወናቸውም በተጨማሪ በቡድን ተደራጅተው እግር ያጥቡ፣ የደከመ ያሳርፉና ስንቅ ላለቀበትም ምግብ ያቀርቡ እንደነበርና በከተማው ከንቲባ የሚመራ ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራው በኮሚቴው ዝርዝር ክትትልና ድጋፍ መሠራቱን የጽሕፈት ቤት ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
እንደርሳቸው ገለጻ፣ የዘንድሮው የገና በዓል ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ሲደረግበት ቆይቷል፡፡ የቤተ-ክርስቲያን አገልጋዮችን ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪና የመንግሥት አካላት ቅንጅታዊ የአደረጃጀት ሥራ በመሥራት እንግዶችን ከታኅሣሥ 21 ቀን ጀምሮ ሲቀበል ነበር፡፡
በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም በባለቤትነት መንቀሳቀስ ስለነበረበት የመንግሥት የፀጥታ አካላት በየአካባቢው በመንቀሳቀስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሠራቱን የገለጹት ኃላፊው፣ በዓሉ ካለምንም የጸጥታና የትራፊክ አደጋ ችግር እንደተጠናቀቀ፤ አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ትልቁ የትኩረት አቅጣጫ የፀጥታ ሥራ እንደነበርና ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር የተሠሩ ሥራዎች ውጤታማ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 3/2011
አንተነህ ቸሬ