ዘላቂ የኢኮኖሚያዊ እድገት ለማረጋገጥ የአምራቹ ክፍል ሚና ወሳኝ መሆኑ ይታመናል። በልዩ ልዩ ምርትና አገልግሎቶች ላይ የተሰማራው የሰው ሀይል ምርታማነት ለኢኮኖሚያዊ እድገቱ አዎንታዊና አሉታዊ ሚና ይጫወታል። የሰው ሀይሉ ምርታማ ከሆነ የምርትና የአገልግሎት ጥራት ደረጃ ከፍ ይላል፤ በአንፃሩ ደግሞ አምራቹ ወይም አገልግሎት ሰጪው ምርታማነቱ ከቀነሰ ውጤቱ ተቃራኒ ነው።
ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ በአለም አቀፍ ገበያ ተወደዳሪ የሆነ ምርት ጥራትና ብዛትን መሰረት ባደረገ መልኩ አምርቶ ማቅረብ የሚያስችል አቅም መገንባት ነው። በተመጠነ የሰው ሀይል ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያሟላ ብዛት ያለው ምርት ተመረተና እና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጠረ ማለት እንደ አገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ የሚያስችል ሁኔታ ተፈጠረ ማለት ነው።
ምርታማነት ለአንድ ሀገር እድገት ወሳኝ እደመሆኑ ኢትዮጵያም በዘርፉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ትገኛለች። በተለያዩ ኢኮኖሚ ዘርፎች ያለውን ምርትና አገልግሎት ምን ደረጃ ላይ እንዳለና በዘርፉ ዋነኛ ተዋናይ የሆነው የሰው ሃይል ምርታማነት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሚያመላክት የጥናት ሪፖርት በቅርቡ ይፋ ሆኗል።
በኢኮኖሚው ዘርፍ በኢትዮጵያ የሰው ኃይል ምርታማነት ያለበትን ደረጃ በዝርዝር የሚዳስሰው ጥናታዊ ሪፖርት ደረጃውን አመልክቷል። በኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት እና በናሽናል ግራጁየት ኢንስቲትዩት በጋራ የተሰራውና በጃፓን ናሽናል ኮኦ`
ፕሬሽን ኤጀንሲ የገንዘብ ድጋፍ የተደረገለት ጥናት በኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ዘርፍ ያለውን የሰው ሃይል ምርታማነት ያለበት ደረጃ በማመላከት የመፍትሄ ሀሳቦችን ጠቁሟል።
ጥናቱ እንደሚያመላክተው በሰው ሀይል ምርታማነት ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ስትነፃፀር እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በዚህ ለሶስት አመታት በተጠናው ጥናት መሰረት የሀገሪቱ ሰው ሀይል ምርታማነት በየዓመቱ ወደ አራት ነጥብ ዘጠኝ በመቶ እያደገ ቢሄድም ከታቀደው ኢኮኖሚያዊ እድገት አንጻር ፈፅሞ የማይሄድና በእድገቱም ላይ ከፍተኛ ጫና የፈጠረ መሆኑ ተመልክቷል።
ወደፊት በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚወጡ ፖሊሲዎች ግብዓት በመሆን ለሰው ሃይል ምርታማነት እድገት ትልቅ ሚና ይኖረዋል በተባለው ሪፖርት ላይ በኢኮኖሚው ዘርፍ፤ ማለትም በቆዳ ኢንዱስትሪ፣ ቴክስታይል፣ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎች ያሉበትን የምርታማነት ደረጃ ዳስሷል።
የኢንስትቲዩቱ ተጠባባቂ ጄኔራል ዳሬክተር ዶክተር ዮሀንስ አያሌው፤ በኢትዮጵያ የሰው ሀይል ምርታማነት ያለበትን ደረጃ የሚያሳየውን የጥናት ሪፖርት መሰረት አድርገው በሰጡት አስተያየት፤ በሀገሪቱ የሰው ሀብት ምርታማነት በየአመቱ እያደገ ቢሆንም፤ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነፃፀር ያለበት ደረጃ እጅግ አነስተኛ ነው ብለዋል።
በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን የሰው ሀይልን ምርታማነት ማሳደግ ወሳኙ ጉዳይ መሆኑን የሚናገሩት ጄኔራል ዳይሬክተሩ፤ የኢትጵያ ምርቶች ተወዳዳሪና ተፈላጊ እንዳይሆኑ የሆነበት ምክንያትም የምርታማነት ማነስ መሆኑን ይናገራሉ። ምርታማነትን ማሳደግ ውጤታማ የሆነ የምርት ጥራት ላይ ያድርሳል። እንደ ዶክተር ዮሀንስ፤
በኢትዮጵያ አሁን ያለው የምርታማነት ደረጃ ዕድገት አራት ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ብቻ መሆኑ፤ አገሪቱ አነስተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የሚያሳይ እንደሆነ ያስረዳሉ። በዚህም እንደ መንግስት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ለምርታማነት ማደግ መስራት ያለበት መሆኑንም ይጠቁማሉ።
ጄኔራል ዳሬክተሩ ጥናቱ በአጠቃላይ በኢኮኖሚው ሴክተር ላይ ሀገሪቱ በቀጣይ በሰው ሀብት ልማት ረገድ ለምታወጣቸው ፖሊሲዎች ግብዓት በመሆን ፋይዳው ከፍተኛ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የሰው ሀይል ምርታማነት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን የሚያስረዱት ጄኔራል ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ ቀደም እንደ አገር በሰው ሀይል ምርታማነት ላይ የተመሰረት ፖሊሲ ባለመኖሩ ምርታማነት እንዲቀንስ አድርጎታል። ነገር ግን፤ በአሁኑ ወቅት መንግስት ምርታማነትን ለማሳደግ ያለበት ደረጃ በመለየትና ችግሩን በመገንዘብ መፍትሄ የሚያመጡ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እያረገ መሆኑንም ይናገራሉ።
ትኩረት ሳይደረግበት የቆየው የሰው ሃይል ምርታማነት ማነስ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ መፍጠሩን የሚያስረዱት ሀላፊው፤ ከዚህ በፊት የነበሩ ፖሊሲዎች ኢንቨስትመንትን በመሳብ ላይ ያነጣጠሩ፤ ለምርታማነት እና ለምርት ጥራት ግን ትኩረት ያልሰጡ እነደነበሩ ያስታውሳሉ። በዚህም ባለፉት አመታት የተመዘገበው ሀገራዊ እድገት ዋነኛ ምንጩ የካፒታል ኢንቨስትመንት መሆኑን ገልፀዋል።
በኢንቨስትመንት ላይ ትኩረት ተደርጎ የተሰራው ስራ በብዛት ላይ የመሰረተ ስለነበር በጥራት ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩን ያብራራሉ። ነገር ግን፤ ውስን የሆነውን ሀገራዊ ሀብት በተገቢው መንገድ ለመጠቀም ጥራትን መሰረት በማድረግ መስራት እንደሚገባና ይህንንም የሚመራ የሰለጠነ የሰው ሀብት ልማት አስፈላጊ መሆኑን ያስረዳሉ።
በፖሊሲ ጥናት ኢንስትቲዩት መሪ ተመራማሪ፣ በጥናቱ ላይ ተሳታፊና አስተባባሪ የሆኑት ዶክተር ኪዳነ ማሪያም በርሄ፤ ጥናቱ የምርታማነት ማነስ ችግር በኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ተፅዕኖ መፍጠሩን ያስረዳሉ። ሀገሪቱ በሰው ሀይል ምርታማነት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መገኘቷ በኢኮኖሚው ላይ የተሻለ ውጤት እንዳይመዘገብ አድርጓል። በመሆኑም፤ ምቹ ፖሊሲ በመቅረፅና በመተግበር ጠንካራ ስራ የሚጠበቅባት መሆኑን ይመክራሉ።
“ሀገራዊ ኢኮኖሚን ለማሳደግ በትንሽ የሰው ሀይል ብዛት ያለውና ጥራቱን የጠበቀ ምርት ማምረት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል።” ይላሉ ተመራማሪው ዶክተር ኪዳነ ማሪያም፤ መንግስት በሰው ሃይል ምርታማነት ላይ ትልቅ ስራ መስራትም ይጠበቅበታል። የበለፀጉ ሀገራት የኢኮኖሚ እድገታቸው መሰረቱ ለዘርፉም ልዩ ትኩረት መስጠታቸው እና ምርታማ የሰው ሀይል በማፍራት ላይ ትኩረት ሰጥተው በመስራት ለውጥ ማምጣታቸው ያስረዳሉ።
“ሀገራዊውን ኢኮኖሚ በፈጣን ሁኔታ ለማሳደግ የሰለጠነ የሰው ሀብት ልማት ላይ ትኩረት መሰጠት አለበት” ያሉት ዶክተር ኪዳነ ማሪያም፤ ሀገሪቱ ዘርፉን ለማሳደግ የሚሰራና በባለቤትነት የሚመራ ተቋም ያስፈልጋታል ሲሉ አስተያየት ይሰጣሉ።
ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማረጋገጥ ከሚደረጉ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ባሻገር የሰው ሀይል ምርታማነት የማሳደጉ ስራ በዋናነት ሊተኮርበት ይገባል። በአነስተኛ የሰው ሀይል፤ ደረጃውን የጠበቀና ጥራት ያለው ምርት በተፈለገው መጠን በማቅረብ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ይቻላልና ለሰው ሀይል ምርታማነት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2012
ተገኝ ብሩ