. 28 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የሚገመት የግብርና ምርት መያዙን ገለጸ
. ህገወጥነትን እንደማይታገስ አስታወቀ
አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ከግንቦት ወር 2011 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በከተማዋ የተስተዋለውን የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦች የዋጋ ንረት መንስኤ በመለየት ችግሮቹን ለመፍታት ባከናወናቸው ተከታታይ ዘመቻ መንስኤው ሰው ሰራሽ እንደነበር አረጋግጧል።
ቢሮው በዚህ ዘመቻ 28 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የሚገመት የግብርና ምርት በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር መያዙን ያስታወቀ ሲሆን፤ የዋጋ ንረቱን ማርገብ መቻሉንና ከዚህ በኋላም ህገወጥነትን እንደማይታገስ አስገንዝቧል።
በቢሮው የኢንስፔክሽንና ሬጉራቶሪ ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ጥላዬ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት ከግንቦት ወር 2011 ዓም መጨረሻ ጀምሮ የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ነበረው። ሽንኩርት ከገበሬው ማሳ ላይ በኪሎ በስድስት ብርና ከዚህም በታች እየተገዛ በከተማዋ ላይ 40 ብርና በላይ ይሸጥ እንደነበር ጠቁሟል።
የእህልና ጥራጥሬ ዋጋም ተከታታይ የዋጋ ጭማሪ ነበራቸው። ቢሮው ባካሄደው ዘመቻ ተዋናዮቹ ደላሎች እንደሆኑ ደርሶበት 28 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የሚገመት የግብርና ምርት በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር መያዝ ችሏል። ቢሮው ይህንን ምርት መልሶ ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በመሸጥም ገበያውን ማርገብ እንደቻለ አቶ ሀብታሙ አመልክተዋል።
እንደ ዳሬክተሩ ማብራሪያ ቢሮው ከገቢዎች፣ከአቃቤ ህግ፣ከፖሊስ፣ከደንብ ማስከበር ቢሮዎች ጋር በጋራ ባካሄደው ዘመቻ 62 መኪና አትክልትና ፍራፍሬ፣ 52 ኩንታል ጤፍና ስንዴ በንግዱ ውስጥ አስተዋጽኦ በሌላቸው አካላት ሲዘዋወር የተያዘ ሲሆን፤ በዚህም 10 ደላሎችን ይዞ ለህግ አቅርቧል።
እንደ ዘይት፣ዳቦ እና ሌሎች መሰረታዊ ሸቀጦች የሚያቀርቡትንም በተመሳሳይ ከዋጋ መረጋጋት ጋር ቢሮው ባከናወነው ሥራ ፈሳሽ የምግብ ዘይት አምስት ሊትር እስከ አምስት መቶ ብር ደርሶ እንደበር።
የዳቦ ዱቄት አየር ባየር በመሸጥ፣የዳቦ ግራም በመቀነስና ዋጋ በመጨመር ችግር ያስከተሉትን እንደደረሰባቸው አቶ ሀብታሙ አስታውቀዋል። በዚሁ መሰረትም ከጎበኛቸው 12ሺ 244 የንግድ ሱቆች አምስት ሺ ሁለት መቶ አስራ ሁለት ለሚሆኑት ከባድና ቀላል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። አንድ ሺ ሁለት መቶ አስራ ሁለት የሚሆኑትን ደግሞ አሽጓል።
‹‹የተወሰደው እርምጃ አስተማሪ እንደሆነ ቢሮው ያምናል›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ለምግብ ዋጋ መናር ህገወጥነት ብቻውን መንስኤ እንዳልሆነ መገንዘብ እንደሚገባና ችግሩም ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ብቻ እንደማይፈታ አመልክተዋል። በዘላቂነት ለዋጋ ንረቱ መንስኤ የሆኑ ሌሎች ምክንያቶችን በጋራ አጥንቶ መፍትሄ ማስቀመጥ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2012
ለምለም መንግሥቱ