አዲስ አበባ፡- ‹‹እኔም ሆንኩ የምመራው የብልጽግና ፓርቲ የትግራይን ህዝብ እንደ ዋነኛ አጋሩና አካሉ ያስባል›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትላንት የብልጽግናን ፓርቲ ከተቀላቀሉ የትግራይ ክልል ተወላጆች ጋር በተወያዩበት ወቅት፤ ምሁራኑን ወክለው ጥያቄ ያቀረቡት የትግራይ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ አመራር ዶክተር አብረሃም በላይ፤ የትግራይ ክልል ተወላጅ ወታደራዊና ሲቪል ባለሥልጣናት እስርን፣ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን፣ የጸጥታና የደኅንነት ስጋቶችን የተመለከቱ ጥያቄዎች አቅርበውላቸው ምላሽ በሰጡበት ወቅት ከትግራይ ህዝብ ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ህዝብ ችግር በመፍታት ብልጽግናን እንደሚያረጋግጡና እርሳቸውም ሆኑ የሚመሩት ፓርቲ የትግራይን ህዝብ እንደ ዋነኛ አጋሩና አካሉ እንደሚያስብ ተናግረዋል፡፡
ዶክተር አብረሃም እስር የሚፈጸመው የትግራይ ተወላጆች ላይ ብቻ ነው በማለት በህዝብ ዘንድ ቅሬታና የመጠቃት ስሜት እንዲፈጠር ማድረጉን አስታውሰው፤ አፍራሽ ሃይሎች ስለ ለውጡና በለውጡ ምክንያት ስለመጣው አዲስ አስተሳሰብ ሕዝቡ ለነገ በትኩረት እንዳይሰራ በማድረግ የትግራይ ህዝብ በፌዴራል መንግሥቱ ይልቁንም በለውጥ ኃይሉ እምነት እንዳይኖረው የሚያደርጉትን አፍ ለማዘጋት በትኩረት እንዲሰራ ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹የፌዴራል መንግሥት የትግራይ ክልል መንግሥትን እንደ ሁለተኛ ዜጋ ለአንዲት ሰከንድ አስቦ አያውቅም ። አብረው የነበሩ ሰዎችም በዚህ ረገድ የሚያሳማን ሀሳብ እንደሌለ ጠንቅቀው ያውቃሉ።
የትግራይን ህዝብ ያገለለ መንግሥት የማንንም ጥቅም አያስከብርም። ህዝብ እንዲከፋፈልና እንዲለያይ የሚያደርግ መንግሥት ኢትዮጵያን ጥቅም አልባ ያደርጋል። ህዝብን ገፍቶ ልማትና ብልጽግናን ማምጣት አይቻልም፤ ብዙዎቹም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ልብ እየገዙ ይመለሳሉ ››ብለዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ወታደርም ሲቪልም ሆነው በእስር ላይ ያሉ የሁሉም አካባቢ ተወላጆች ናቸው፤ በአሁኑ ወቅት ያለው የእስረኛ ቁጥር ዝቅተኛ ነው፤ የተለየ የሙስና ችግር ኖሮ መረጃ ተገኝቶባቸው የፍርድ ሂደት ላይ ያሉ ሰዎች ካልሆኑ በስተቀር ከህግ አንጻር ክፍተት የማያመጡና በህግ አግባብ ሊታዩ የሚችሉ ጉዳዮችን ዓቃቤ ህግ በፍጥነት እልባት እንዲሰጥ ይደረጋል ። በተቻለ መጠን ህዝቡን ሊያረጋጋ የሚችልና የፖለቲካውን ምህዳር ሊያሰፋ የሚችል ውሳኔ በመንግሥት በኩል ለመውሰድ ዝግጁነት አለ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ወንጀል ሳይሰራ እስር ቤት የሚገባ እንደሌለ በመጥቀስ ‹‹ነገር ግን አሁን ባለው ባህል ከአንድ አካባቢ ሰው ሲታሰር ‹እኛ ታሰርን› በሚል ሁሉም የራሱን ያነሳል። ሆኖም ወንጀለኛን ከብሄር ጋር ማገናኘት ተገቢ አይደለም›› ብለዋል።
የኢኮኖሚ ጉዳይን በሚመለከት ትግራይ ሳይለማ ሌላውን አካባቢ ማልማት እንደማይቻልና የበጀት ክፍፍሉም ለሁሉም ክልሎች ፍትሐዊ አሠራርን በተከተለ መንገድ መሰራቱን ገልጸው፤ ይህ ሂደት እንደሚቀጥልና የአገሪቷ ኢኮኖሚ ሲጨምር በጀት እንደሚጨምር አመላክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የትግራይ ህዝብ ከፌዴራል መንግሥትና ከጎረቤት አገራት ጥቃት ሊመጣ ይችላል በሚል ስጋት ውስጥ እንደሚገኝና መፍትሄው ምን እንደሆነ ለተጠየቁት ሲመልሱ፤ በትግራይ ሀዝብ ላይ ምንም አይነት ጫና አለመኖሩን፤ ህዝቡ ባለመብትና የአገሩ ባለቤት እንደመሆኑ መጠን ከየትኛውም አቅጣጫ የትግራይን ህዝብ የሚያሰጋ ጥቃት እንደሌለና ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ጥቃት ሲሰነዘር ሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ጥቃት አድርጎ መከላከሉን በማስታወስ፤ ወደ ፊትም ይህ ሁኔታ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ ጥቃት ቢታሰብ በቂ የሆነና ሉዓላዊነትን የሚያስጠብቅ ሀይል መኖሩን ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2012
አዲሱ ገረመው