አዳማ፡- እራሳቸውን ነጻ አውጪዎች ነን ብለው የሰየሙ ሽፍቶች በህብረተሰቡና በመንግሥት መዋቅር ላይ ጉዳት ስላደረሱ መንግሥት እርምጃ ለመውሰድ መገደዱን የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
ጨፌ ኦሮሚያ ትናንት አምስተኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ስብሰባውን ሲጀምር የክልሉን የግማሽ ዓመት አፈጻጸም ያቀረቡት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ፤ ሽፍቶች ለውጡን ተከትሎ የታየውን የዴሞክራሲ ጭላንጭልና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ለማጨናገፍ የጥፋት ተልዕኮ ወስደው በህብረተሰቡና በመንግሥት መዋቅር ላይ ጉዳት በማድረሳቸው ይህንን ሲፈጽሙ በተገኙ አካላት ላይ መንግሥት እርምጃ ለመውሰድ መገደዱን ተናግረዋል፡፡
የታጠቁ ሃይሎች ትጥቃቸውን ፈትተው በሰላማዊ መንገድ ህብረተሰቡን እንዲቀላቀሉ መንግሥት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመሆን ለበርካታ ጊዜ ጥረት ሲያደርግ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሽመልስ፤ የዴሞክራሲውን ምህዳር ለማስፋት ሲል መንግሥት ያሳየውን ሆደ ሰፊነት እንደ አቅም ማጣት ቆጥረው ከጥፋታቸው ባለመመለሳቸው የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሲል እርምጃ ለመውሰድ መገደዱን ጠቁመዋል፡፡
አቶ ሽመልስ በታጣቂዎቹ ጉዳት ለደረሰባቸውና ህይታቸውን ላጡ ንጹሃን ዜጎች የተሰማቸውን ሀዘን በመግለጽም በቁርጥ ቀን የክልሉ ልጆች የህይወት መስዋዕትነት የተገኘው ለውጥ ወደ ኋላ እንዳይመለስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የጥፋት ሃይሎቹ አደረሱ ያሉትን ጉዳት አቶ ሽመልስ ሲዘረዝሩም ፤ በሰዎች መካከል የብሔርና የሃይማኖት ግጭትን በመቀስቀስ በንብረት ፣በአካልና በህይወት ላይ ጉዳት ማድረስ፣ በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች መካከል ግጭት በመቀስቀስ የነገ ተስፋዎች እንዲቀጩ ማድረግ፤ በየጊዜው ከሚያደርሱት የንብረት መውደም ፣ የአካል መጉደልና የህይወት መጥፋት በተጨማሪ በህብረተሰቡ ላይ የስነ ልቦና ጫና በማሳደር ተረጋግቶ እንዳይኖር ማድረግ፡፡ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲገደብና አንዳንድ የልማት ፕሮጀክቶችም እንዲስተጓጎሉ ምክንያት መሆናቸውን አቶ ሽመልስ ጠቅሰዋል፡፡
መንግሥት ህግን የሚጻረሩ እንቅስቃሴዎችን ሁሉ እያጤነ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ቁርጥ አቋም ይዞ እየሰራ እንዳለ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸው፤ ባለፉት ስድስት ወራት በአጎራባች ካሉ ክልሎች ጋር ልማትና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማጠናከር እየተሰራ እንዳለም ተናግረ ዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በተለያዩ ዘርፎች የተከናወኑ የሉዋቸውን መንግሥት ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ ለሚያደርገው ሽግግር የግብርናውን ዘርፍ ችግሮች በመፍታትና አዳዲስ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ አበረታች ሥራ መሥራቱን ጠቅሰዋል፡፡
የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቡና ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በጫት ፣በሻይቅጠል ምርቶች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን ያብራሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የእንስሳት እርባታና የእርሻ መካናይዜሽንም እንዲሁ ትኩረት ማግኘታቸውን፤ በይበልጥም መስኖን በመጠቀም በበጋ ወራት ስንዴን የማምረት ዕቅድ ተይዞ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በትምህርት፣ በጤና፣ በገቢ አሰባሰብ፣ በኢንቨስትመንት፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በመንገድ ግንባታ፣ በንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ በሃይል አቅርቦት፣ ቋንቋና ባህልን በማሳደግና በሌሎችም ጉዳዮች በስድስት ወሩ የነበሩ አፈጻጸሞች በሪፖርቱ ቀርበው በጨፌው አባላት አስተያየት ተሠጥቶባቸዋል፡፡
የጨፌው አባላት ካነሷቸው ጥያቄዎች ውስጥ የህግ የበላይነትንና የክልሉን ሰላም የማስጠበቅ ጉዳይ እምብዛም ትኩረት አልተሠጠውም፤ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያለው ወሰን አልተከበረም፤ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች አልተመለሱም ፤ ለወጣቱ በቂ የሥራ ዕድል አልተፈጠረም የሚሉ ይገኙበታል፡፡
ለጥያቄዎቹ በተሰጠው ምላሽም መንግሥት የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ እርምጃ እየወሰደ እንዳለና ወደፊትም እንደሚቀጥል፤ በየአካባቢው የተለያዩ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች እንዳሉና እነዚህን በአንድ ጊዜ ሳይሆን በሂደት ለመመለስ እየተሰራ እንዳለ ፤ ኢንቨስትመንትን፣ የገጠርና የከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራን በማስፋፋት የሥራ እድል ተጠቃሚዎችን ቁጥር ለማሳደግ ሥራ መከናወኑን እንዲሁም ከወሰን ጋር በተያያዘ ችግሮች በጥናት እንደሚመለሱ አስረድተዋል፡፡
ስብሰባው የሁለት ቀን ቆይታ ሲኖረው በቀጣይም የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች እንደሚጸድቁበትና ሹመቶችም እንደሚሠጡበት ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2012
ኢያሱ መሰለ