አዲስ አበባ:- የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ለአዲስ አበባ አዳማ የፍጥነት መንገድ እና ለለቡ ጎሮ መጋቢ መንገድ ፕሮጀክቶች ማሰሪያ ከተበደረው 11 ነጥብ 27 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከሶስት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር በላይ እዳ መከፈሉን አስታወቀ።
በኢንተርፕራይዙ የፋይናንስ ዳይሬክተር አቶ ቴድሮስ አስራት በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቶቹ የተከናወኑት ከቻይናው ኤግዚም ባንክና ከኢትዮጵያ መንግሥት በተገኘ 11 ነጥብ 27 ቢሊዮን ብር ብድር ሲሆን፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት በኢንተርፕራይዙና በመንግሥት ከሶስት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር በላይ እዳ ተከፍሏል።
እንደዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ ፕሮጀክቶቹ የተከና ወኑት ከቻይናው ኤግዚም ባንክ በተገኘ ስድስት ነጥብ 42 ቢሊዮን ብርና ከኢትዮጵያ መንግሥት በተገኘ አምስት ነጥብ 85 ቢሊዮን ብር በጥቅሉ በ11 ነጥብ 27 ቢሊዮን ብር ብድር ተጠናቆ በ2007 ዓ.ም ወደ ሥራ ገብቷል።
ኢንተርፕራይዙ ሁለት ዓመት የእፎይታ ጊዜ ከወሰደ በኋላ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ለፕሮጀክቶቹ ማስፈጸሚያ የተበደረውን እዳ መክፈል የጀመረ ሲሆን፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት በመንግሥት ሶስት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር እና በኢንተርፕራይዙ 347 ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ብር እዳ መከፈሉን ተናግረዋል።
ኢንተርፕራይዙ ከኤክዚም ባንክ ጋር እዳውን ለመክፈል የተዋዋለው በ20 ዓመታት ውስጥ ከፍሎ ለማጠናቀቅ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመው፤ መንግ ሥትና ኢንተርፕራይዙ ብድሩን ዕቅድ አውጥተው እየከፈሉ በመሆናቸው በውሉ መሰረት እዳው ተከፍሎ እንደሚጠናቀቅ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2012
ሶሎሞን በየነ