‹‹ለውጡ አስደናቂ የሆነው ኢትዮጵያውያን በራሳቸው የጀመሩትና እያከናወኑት የሚገኝ በመሆኑ ነው›› የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያና አሜሪካ ከሁለትዮሽ ትብብሮቻቸው በተጨማሪ ለባለብዙ ወገን ግንኙነቶችም ትኩረት ሰጥተው በቅርበት እንደሚሰሩ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ፡፡
አቶ ገዱ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ከሚገኙት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ ጋር በሰጡት መግለጫ፣ አሜሪካ ከጠንካራ የኢትዮጵያ አጋሮች መካከል አንዷ በመሆኗ ኢትዮጵያና አሜሪካ በቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ካሏቸው የሁለትዮሽ ትብብሮች ባሻገር ለባለብዙ ወገን ግንኙነቶቻቸውም ትኩረት እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡
አገራቱ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እንዲሁም በፀጥታና ደህንነት ዘርፎች ዙሪያ ባሉ የባለብዙ ወገን ትብብሮቻቸው ላይ አተኩረው እንደሚሰሩም አቶ ገዱ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያና አሜሪካ ከመቶ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዳላቸው የጠቆሙት አቶ ገዱ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማይክ ፖምፔዮ ጉብኝት የኢትዮ- አሜሪካን ሁለንተናዊ ግንኙነት የሚያጎለብት እንደሆነና ሁለቱ አገራት በምጣኔ ሀብትና በጸጥታ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ትብብሮቻቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመልክተዋል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለው ታሪካዊ የለውጥ ተግባር ከኢትዮጵያውያን በመነጨ ፍላጎት የተጀመረና በኢትዮጵያውያን እየተመራ የሚገኝ መሆኑ ለውጡን ልዩና አስደናቂ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡
ማይክ ፖምፔዮ ‹‹አሜሪካና ኢትዮጵያ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረና ጠንካራ የሆነ ግንኙነት አላቸው፡ ፡ የምጣኔ ሀብትና የጸጥታ ጉዳዮችን ጨምሮ በሌሎች
ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ትብብሮቻችንን የሁለቱን አገራት ሕዝቦች በሚጠቅም መልኩ አጠናክረን ለማስቀጠል ተወያይተናል›› ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለቢዝነስና ኢንቨስትመንት ተግባራት ምቹ የሆነ ከባቢ እንዳላትና የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የለውጥ ተግባራት የአገሪቱን እድገት የሚያበረታታና የአሜሪካ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችል እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
የዶክተር አብይ አስተዳደር ተጠያቂነትን ያሰፈነና አካታች የሆነ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት የሚያከናውነውን ተግባር አሜሪካ እንደምትደግፍ ገልፀው፣ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ድጋፍና ያላትን አጋርነት አጠናክራ እንደምትቀጥልም ተናግረ ዋል፡፡
ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ የሚያደርጉት ድርድር በመግባባት እንዲጠናቀቅ አሜሪካ ድጋፍ እንደምታደርግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ጥንታዊትና አስደናቂ አገር መሆኗን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ ያላትን ተሳትፎም አድንቀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አሜሪካ በኢትዮጵያ፣ በኬንያና በሶማሊያ የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ መንጋ ለመከላከል የሚያግዝ የስምንት ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምትሰጥ ይፋ አድርገዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2012
አንተነህ ቸሬ