አዲስ አበባ:- እ.አ.አ በ2019 የኤሌክትሮኒክስ ቪዛን በመጠቀም 169 ሺ ጎብኚዎች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውን የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጅብ ጀማል በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ እ.አ.አ በ2019 የኤሌክትሮኒክስ ቪዛን በመጠቀም ወደ አገር ውስጥ ለመግባት አስፈላጊውን መረጃ አሟልተው በኤጀንሲው ድረ ገጽ ያመለከቱ 169 ሺ ጎብኚዎች ገብተዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ የውጭ አገር ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ውጭ አገር ከሚገኙ የአገሪቱ ኤምባሲዎች የመግቢያ ቪዛ ለማግኘት የሚያጠፉትን ጊዜና ድካም በመቀነስ የጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ እ.አ.አ በ2019 በኤሌክትሮኒክስ ቪዛ እንዲገቡ ተፈቅዷል።
በዚህም እ.አ.አ በ2019 የኤሌክትሮኒክስ ቪዛን በመጠቀም ወደ አገር ውስጥ ለመግባት አስፈላጊውን መረጃ አሟልተው በኤጀንሲው ድህረ ገጽ ካመለከቱት መካከል 99 በመቶ የሚሆኑት ወይም 169 ሺ ጎብኚዎች የገቡ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ አንድ በመቶዎቹ አስፈላጊውን መረጃ ባለማሟላታቸውና በትክክለኛው መንገድ ባለማመልከታቸው ጥያቄያቸው ውድቅ መደረጉን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ የአፍሪካ አገራት ለቪዛ ጥያቄ የሚሰጡትን ምላሽና የሰዎችን ነፃ ዝውውር የማሳለጥ ተግባር ላይ የሚገኙበትን ደረጃ አስመልክቶ ያወጣውን ሪፖርት ዋቢ አድርገው አቶ ሙጅብ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከዓመታት በፊት በቀላሉ ቪዛ ወይም የይለፍ ወረቀት ከማይገኝባቸው አገሮች ተርታ ነበረች።
ነገር ግን እ.አ.አ በ2019 መንግስት የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ በወሰደው እርምጃ ቀደም ሲል በመዳረሻ ቪዛ (arrival visa) ሲገቡ ከነበሩ 37 የምዕራባውያን አገራት ዜጎች በተጨማሪ፤ 54ቱም የአፍሪካ አገሮች ዜጎች በመዳረሻ ቪዛ ወደ አገሪቱ እንዲገቡ ተፈቅዷል።
አቶ ሙጅብ የአገሪቱን የቱሪስት ፍሰት ለማሳደግ የውጭ አገር ዜጎች በቀላሉ በኤሌክትሮኒክስ ቪዛ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ በመደረጉ፤ ከዓመታት በፊት ለቪዛ ጥያቄ በምትሰጠው ምላሽና የሰዎችን ነፃ ዝውውር የማሳለጥ ተግባር ከአፍሪካ አገራት ከነበረችበት 50ኛ ደረጃ ወደ 18ኛ ደረጃ በአንድ ዓመት ውስጥ ከፍ ማለት መቻሏን ተናግረዋል፡፡
በተለያየ ምክንያት ወደ አገሪቱ የሚመጡ የውጭ አገር ዜጎች የኤሌክትሮኒክስና የመዳረሻ ቪዛን በቀላሉ በመጠቀም ሳይጉላሉ ጊዜያቸውን ቆጥበው መግባት መቻላቸው የአገሪቱን የጎብኚዎች ፍሰት እንደጨመረው የሚናገሩት አቶ ሙጅብ፤ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከኤምባሲዎች፣ ከቱሪዝም ኮሚሽን፣ ከቱሪዝም ኢትዮጵያ፣ ከባለሆቴሎች እና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር ተቀናጅቶ የማስታወቂያ ሥራዎችን በሰፊው በመስራት በኤሌክትሮኒክስ ቪዛ የሚስተናገዱ የውጭ አገር ዜጎችን ቁጥር እ.አ.አ በ2020 ወደ 500 ሺ ማድረስ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
አገሪቱ ለቪዛ ጥያቄ በምትሰጠው ፈጣን ምላሽና የሰዎችን ነፃ ዝውውር በማሳለጥ ለገጽታ ግንባታዋ ትልቅ አስተዋጽፆ ከማበርከቱ ባለፈ የጎብኚዎችን ፍሰት በመጨመር ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ የሚያስችላት መሆኑን አቶ ሙጅብ ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2012
ሶሎሞን በየነ