ሞጆ፡- በሞጆ ከተማ የሚገኙ የቆዳ ፋብሪካዎች ደረቅ ቆሻሻ ያስወግዱበት በነበረው ቦታ እንዳይጥሉ በመታገዳቸው በየደረጃው ከከተማው አስተዳደሩ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ድረስ ቢያመለክቱም ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ገለጹ።
እስከ አሁን ተረፈ ምርቱን የሞጆ ከተማ ማዘጋጃ ቤት አዘጋጅቶት ወደነበረው የሉሜ ወረዳ ኩርማ ፋቶሌ ቀበሌ ሲደፉ መቆየታቸውን በመጠቆም፤ ላለፉት ስምንት ወራት ግን የአካባቢው ሰዎች እንዳይጣል በመከልከላቸው መቸገራቸውን ተናግረዋል።
የጂያንሲን ዛንግ ቆዳ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ጆቢ፤የቆሻሻ መጣያ ስፍራ በመጥፋቱ በፋብሪካው ጊቢ ቆሻሻ ለማከማቸት እንዳስገደዳቸውና መፍትሄ እንዲሰጣቸው የሚመለከታቸውን አካላት ተመላልሰው ቢጠይቁም እንዳልተሳካ አብራርተዋል።ጥር 27 ቀን 2012 ዓ.ም ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ቅሬታቸውን ማስገባታቸውንም አመልክተዋል።
ሆዳኦቼ /ፔሌ ሌዘር/ ቆዳ ፋብሪካ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ለለ ላለፉት ጊዜያት ቆሻሻ ሲጣልበት በነበረው ስፍራ እንዳይጣል በመታገዱ እየተከማቸ በሚገኘው ቆሻሻ ምክንያት ምርት ለመቀነስ መገደዳቸውን አመልክተው የሚፈጠረው ሽታ በፋብሪካዎቹ ብቻ ሳይሆን ለከተማውም መጥፎ ገጽታ ስለሆነ ውሳኔ እንዲሰጣቸው አመልክተዋል። በአካባቢው የሚገኙ ሌሎች ፋብሪካዎችም በተመሳሳይ መልኩ በመቸገራቸው እልባት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኢንቫይሮሜንታል ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ወይዘሮ ዘርፌ መኩሪያ፤ ፋብሪካዎቹ በየጊዜው እያከማቹት የሚገኙት ቆሻሻ በሰራተኞች ጤና ላይ ከፍተኛ ችግር ስለሚያስከትል ፈጣን መፍትሄ እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል።ኢንስቲትዩቱ ለሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩ አስቸጋሪ መሆኑን፣ ሊመለስ የማይቻልበት ደረጃ ከመድረሱ አስቀድሞ በየደረጃው የሚገኙ አካላት እርምጃ እንዲወስዱ ማሳሰቡንም ጠቁመዋል።
የሉሜ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መንግስቱ ኩመራ ከተማ አስተዳደሩ ሌላ አማራጭ ቢያዘጋጅ እንደሚሻል ገልጸው፤ ሆኖም አሁን ሽታን ለማጥፋትና አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ቢያስተካክል ሕብረተሰቡን በማሳመን አማራጭ እስኪገኝ ቢያንስ ከስድስት እስከ ስምንት ወራት ድረስ እንዲጣልበት ሊደረግ እንደሚችልም አክለዋል። ሰሞኑንም ከምስራቅ ሸዋ ዞን አመራሮች ጋር በጉዳዩ እንደተወያዩ በመጠቆም፤ በቀጣይም የህግ የበላይነትን እናስከብራለን ብለዋል።
የሞጆ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ መሰረት አሰፋ፤‹‹የሉሜ ወረዳ ችግር እችላለሁ፣ እፈጽማለሁ እያለ እስካሁን እያጓተተው ነው።አልችልም፣ ከአቅሜ በላይ ነው ብሎ ወደዞን አልያም ወደ ክልል ቢያስተላልፍ የሚቀጥለው አካል እስካሁን መፍትሄ ይሰጥ ነበር›› ብለዋል። ቦታ እያስጠናን በመሆኑ ከስምንት እስከ አስር ወራት እንዲደፋበት ጠይቀውም እንዳልፈቀዱላቸው ጠቁመ ዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2012
ዘላለም ግዛው