አዲስ አበባ፡- የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከየካቲት 5 እስከ 7 ቀን 2012 ዓ.ም በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀው ከትናንት በስቲያ እኩለ ሌሊት ላይ ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ምክክር አድርገዋል፤ ከሀገራት መሪዎች ጋርም የሁለትዮሽ ውይይቶችና ስምምነቶችን ፈፅመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ጉብኝት የኢትዮጵ ያውያንን ክብርና ጥቅም ያረጋገጠ ከመሆኑም ባሻገር የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ስኬት እና ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር ያላትን የጠበቀ ወዳጅነት በግልፅ ያሳየ ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው መጀመሪያ ላይ 300 ከሚሆኑ ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የኮሙዩኒቲ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት ሀገር ከፍ የምትለው ዝቅ ብሎ ህዝብን ማገልገል ሲቻል እና የደሀውን ሀብት ከመስረቅ በመቆጠብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በውይይቱ በተለያዩ የቀጣናው ሀገራት ዜጎች ከገቡበት ችግር እንዲወጡ መፍትሄ መፈለግ ላይ ማተኮር እንደሚገባ ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ በፌስቡክ የሚለቀቁ አሉባልታዎችን እያናፈሱ በዚያ ላይ ጊዜ ማጥፋት ለዳያስፖራውም ለሀገርም አይጠቅምም ብለዋል፡፡
በዱባይ ሸባብ አልአህሊ ስታዲየም ከመካ ከለኛው ምስራቅ ሀገራት የተሰባሰቡ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በታደሙበት መድረክ ተገኝተው የኢትዮጵያን የወደፊት ብሩህ ተስፋ እና የዜጎቿን ብልፅግና የማረጋገጥ ጉዳይ አብራርተዋል፡፡ በመድረኩ ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በተጠናከረ መልኩ ሀገራቸውን እንዲለውጡና ሰላማቸውን በማስጠበቅ የብልፅግና ጉዞውን እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ሰርተው ኢኮኖሚያቸውን ማሳደግም ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሀገራት ዜጎች የስራ እድል መፍጠር የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ በሀገር ውስጥ መኖሩን ለመድረኩ ተሳታፊዎች ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤የተመቻቸና ሰላማዊ ህይወት ለኢትዮጵያውያን የሰርክ ኑሮ ይሆናል ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
በመድረኩ ኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ደስታቸውን ሲገልፁ የነበረ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የወደፊት እቅዳቸውንና የሚያልሟትን ኢትዮጵያን ስለገለፁላቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል:: መድረኩ ኢትዮጵያዊ አንድነት ጎልቶ መታየት የቻለበትም ነበር፡፡
ለዜጎች የስራ እድል ከመፍጠር አንፃር እኤአ ከኦክቶበር 20/2020 እስከ ኤፕሪል 10/2021 ድረስ በዱባይ ከተማ በሚካሄደው ዱባይ 2020 አለምአቀፍ ኤክስፖ 10 ሺህ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዱባይ ገዢ ሼክ ሼክ መሀመድ ቢን ረሺድ አልመክቱም ጋር በዱባይ በተወያዩበት ወቅት ስምምነት ላይ መደረሱን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሀላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በጉብኝቱ ማጠናቀቂያ ተናግረዋል፡፡
በዚህም በጥቂት ሳምንታት ውስጥ እነዚህን ዜጎች የመመልመልና ዝግጁ የማድረግ ስራ ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመሆን እንደሚከናወን አቶ ንጉሱ ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላለፉት 25 አመታት በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ለቤተክርስቲያን መስሪያ ቦታ ጥያቄ ስታቀርብ ብትቆይም መፍትሄ ሳያገኝ ቀርቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ውይይት የግንባታ ቦታው መፈቀዱ በርካቶችን አስደስቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለሼክ መሀመድ ያቀረቡላቸውን የኢትዮጵያውያን የስራ ፈቃድ ፣ የአምልኮ እና የኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት ግንባታ ቦታዎችን የማግኘት ጥያቄዎችን እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮችን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ከልዩ ልዩ ኃላፊዎች ጋር እንደሚመክሩበት ቃል መግባታቸውም ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ዲፕሎማሲያው ድል ተደርጎ የሚወሰድ ስኬት ነው፡፡
ሼክ መሀመድ እንደተናገሩት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይና ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ የጀመሩትን ለውጥ በቅርበት እንደሚያውቁትና እንደሚከታተሉ ለውጡም ለኢትዮጵያ እና ለቀጣናው እየጫረ ላለው ተስፋ እውቅና እንደሚሰጡ ገልፀዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቆይታቸው በእነዚህ ሀገራት የመስሪያም ሆነ የመኖሪያ ሰነድ ሳይኖራቸው በደላሎች ተታለው የገቡና በልዩ ልዩ ምክንያት በችግር ውስጥ ከሚገኙ፣ ጥቃት ከደረሰባቸው እና በመጠለያ ውስጥ ካረፉ ሴት ኢትዮጵያውያን ጋር በችግሮቻቸው እና በመፍትሄዎች ዙሪያ በአቡዳቢ ውይይት አካሂደዋል፡፡
ዜጎቹ ከሚደርስባቸው አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት ባሻገር በእስር ቤቶች አስቸጋሪ ጊዜያትን ማሳለፍም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወደ ሀገራቸው መመለስም ሆነ በገቡበት ሀገር መስራት የማይችሉት እነዚህ ዜጎች በአጣብቂኝ ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በጉብኝታቸው የእነዚህ ዜጎች ስቃይ ይቆም ዘንድ የሀገራቱን መሪዎች ጠይቀዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባቸው ሀገራት በዘርና በቋንቋ እየተከፋፈሉ አላስፈላጊ ጥላቻና ቁርሾ ውስጥ መግባታቸውን የታዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፤በኢትዮጵያዊ ስርዓትና ወግ መሰረት በመምከርና በማስታረቅም ጭምር አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ አድርገዋል፡፡
ይህም ወቅታዊ የሀገሪቱ ፈተና የሆነውን በብሄር የመከፋፈል ችግርን ለመቅረፍ፣ ኢትዮጵያዊ አንድነትን አስቀድሞ ከማስቀጠል አንፃር እና ለይቅርታ የተዘጋጀ ልብን በዜጎች ዘንድ በመፍጠር በኩል ትምህርት የተገኘበት ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ልዑካቸው የዱባይ ኤክስፖ 2020 ሳይትን በዱባይ ከተማ ተገኝተው በጎበኙበት ወቅት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኤክስፖን በምታዘጋጅበት ወቅት ሊከናወኑ ስለሚገባቸው ስራዎች ትምህርት መቅሰም ተችሏል፡፡
የኤክስፖው አዘጋጆች ኢትዮጵያ ኤክስፖው ከሚካሄድባቸው ቀናት በአንዱ ቀን ታሪኳን፣ ባህሏን፤ ምግቧን፣ ምርቶቿን፣ ቅርሶቿንና የቱሪስት መስህቦቿን እንዲሁም ሁለንተናዊ ገፅታዋን ለአለም የምታስተዋውቅበት መድረክ የፈቀዱ ሲሆን፤ በዚህ እድል በመጠቀም የኢትዮጵያን ገፅታ የማሳየት እድል መገኘቱ ትልቅ አጋጣሚ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አልጋ ወራሽ ሼክ መሀመድ ቢን አል ነኸን ጋር ሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚ በሚያደርጉ የሁለትዮሽ፣ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። በዚህም የሀገራቱ ግንኙነት አሁን የደረሰበትን ደረጃ በማድነቅ በቀጣይ የበለጠ እንዲጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው አልጋ ወራሹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀውላቸዋል፤ ይህም የወደፊቱን የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ያጠናክረዋል፡፡
በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእስር ላይ ያሉ እና አስፈላጊው ሰነድ ስለሌላቸው ከሀገራቱ መውጣት ያልቻሉ ዜጎች ተለቀው ወደ ሀገራቸው ይገቡ ዘንድ ባደረጉት መልካም ግንኙነት በጉብኝታቸው ማጠናቀቂያ 135 ኢትዮጵያውያንን ይዘው ወደ ሀገራቸው መልሰዋል፡፡
ድል እና ክብርን የተቀዳጀው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝት ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ተስፋን የሚፈነጥቅ በሀገራቱ የሚኖሩ ዜጎቿን ሕይወትም የሚቀይር ሆኖ መጠናቀቁን አቶ ንጉሱ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2012
ድልነሳ ምንውየለት