በዶክተር አርከበ ዕቁባይ የሚመራው የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመልሶ ማልማት ፕሮግራምን ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ ባለፉት ዓመታት በርካታ ነዋሪዎች ከመሀል ከተማ እየተፈናቀሉ በከተማዋ ዳርቻዎች በተሠሩ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ውስጥ ለመኖር ተገደዋል፡፡ ይህም ለተለያዩ ማኅበራዊ ቀውሶች እንዳጋለጣቸው ነዋሪዎች ባገኙት አጋጣሚ ሲገልጹ ይስተዋላል፡፡ በምትክ ቦታ አሰጣጥና በካሳ አከፋፈል ላይም ከፍተኛ ቅሬታዎች ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የነበረው የመልሶ ማልማት ሥራ አኗኗርን እና እሴትን ያላማከለ እንዲሁም ያለ በቂ ዝግጅት የማይደረግበት በመሆኑ ከአካባቢያቸው ለልማት የተነሱ ሰዎች መሰረተ ልማቶች ባልተሟሉባቸው የከተማዋ ዳርቻዎች ላይ እንዲሰፍሩ ተደርጓል፡፡ በዚህም ብዙ የመሀል ከተማ ኗሪዎች የቀደመ ማህበራዊ ትስስራቸው ተበጣጥሶ ተበታትነው ቀርተዋል፡፡ አሁንም ድረስ መልሶ ማልማት ሕዝብን ከሚኖርበት አባርሮ ሌላን ማስፈር መሆን የለበትም በሚል በርካታ የልማት ተነሺዎች ቅሬታቸውን ሲገልጹ ይሰማል፡፡
አቶ ታምራት ተስፋዬ አራት ኪሎ ፊት በር አካባቢ በቀበሌ ቤት ውስጥ ኗሪ ነበሩ፡፡ ቦታው ለልማት እንደሚፈለገው ተነግሯቸው ፒያሳ ራስ መኮንንም ድልድይ አካባቢ ተለዋጭ ቤት ተሰጣቸው፡፡ ጥቂት እንደኖሩ ይህም ቦታ ለልማት ይፈለጋል ተብለው እንዲነሱ ተደረገ፡፡ ቀጣይ ማረፊያቸው ግን እንደመጀመሪያው ጊዜ ቅርብ አልነበረም፡፡ የካ አባዶ ኮንደሚንየም ገቡ፡፡ አቶ ታምራት ከመሃል ከተማ ተነስተው ዳር ላይ በመስፈራቸው መማረራቸውን ይናገራሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የተነሱበት አካባቢ ሳይለማ ጫካ ሆኖ መመልከታቸው ምሬታቸውን ከፍ አድርጎታል፡፡
‹‹ከመሃል ከተማ አምጥተው እዚህ ሲጥሉኝ ብዙ ጉዳት ነው የደረሰብኝ፡፡ የምሰራው አየር ጤና ነው፡፡ ከየካ አባዶ አየርጤና ለመሄድ አስራ አንድ ሰዓት ነው የምነሳው፡፡ ባለቤቴ በፊት በነበርበንበት አካባቢ እንጀራና ዳቦ ጋግራ በመሸጥ እኔ የማገኛት ገቢ አነስተኛ ስለሆነች ትደጉመኝ ነበር፡፡ አሁን ግን የምንኖርበት አካባቢ ምቹ አይደለም፡፡ ምንም አይነት ስራ መስራት አልቻለችም፡፡ በአካባቢው ይኖር የነበረው የሶስት ቀበሌ ሕዝብ ወደተለያዩ የከተማው ዳርቻዎች ሲበተን የኖረ ዕድራችንም አብሮ ተበትኗል›› ይላሉ፡፡
ከልደታ ተነስተው አያት ጣፎ ኮንዶሚንየም የከተሙት ወይዘሮ ጽጌ ደስታም ተመሳሳይ ታሪክ አላቸው፡፡ በልደታ ክፍለ ከተማ ሚቲዎሮሎጂ ፊት ለፊት በሚገኝ ሰፈር ውስጥ ጠባብ በሆነች የቀበሌ ቤት ውስጥ ይኖሩ እንደነበረ ይናገራሉ፡፡ በመልሶ ማልማቱ ምክንያት የቤት ባለቤት ስለሆንኩና በተሸለ ቤት ውስጥ ስለምኖር ደስተኛ ነኝ ይላሉ፡፡ ነገር ግን ከሰላሳ ዓመት በላይ ከኖሩበት አካባቢ ርቀው አሁን የሚገኙበት አያት ጣፎ ኮንዶሚንየም በመምጣታቸው ቅር ተሰኝተዋል፡፡ ‹‹ልደታ አዲስ የተሰራ ኮንዶሚንየም ነበረ፣ ምነው እዛ ቢተውኝ እዚህ አምጥተው ከሚጥሉኝ›› ይላሉ፡፡ ከልደታ ተነስተው አያት ጣፎ መስፈራቸው እንደሚቆጫቸው የሚናገሩት ወይዘሮ ጽጌ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሰል ቅሬታዎችን ለዓመታት ሲያስተናግድ እንደኖረ የአዲስ አበባ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ተሸመ ለታ ይናገራሉ፡፡ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ሁለት ስራዎችን ይሰራል፡፡ አንደኛው መሬት ማዘጋጀት ሲሆን ሁለተኛው መልሶ ማልማት ነው፡፡
ስራ አስኪያጁ አቶ ተሾመ በርካታ ቅሬታዎች የሚቀርቡበት መልሶ ማልማት ቅሬታዎቹን መፍታት በሚያስችል መልኩ በአዲስ መንገድ ሊተገበር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ስለጉዳዩ በዝርዝር ሲያብራሩም ‹‹መልሶ ማልማት ከዚህ ቀደም እንደነበረው እንዳይጓዝ መሪውን ቀይሯል፡፡ በፊት ዜጎች በቦታቸው የማልማት መብት አይሰጣቸውም፤ የልማቱ ተጠቃሚም አይሆኑም ነበር፡፡ ለምሳሌ ጨርቆስና ካዛንችስ ከዚህ ቀደም ብዙ ቤቶች ፈርሰዋል፡፡ ተነሺዎች ወደጫፍ እየተወሰዱ ነበር ሌሎች እንዲያለሙት መሬቱ የሚሰጠው፡፡ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እንደተናገሩት፤ አሁን ግን በቦታው ያሉ ሰዎች ሳይፈናቀሉ እዛው ባሉበት የልማቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
ለተጠቀሰው መርሃ ግብር አንዱ ማሳያ ለገሃር ላይ በቅርቡ የተዋወቀው ፕሮጀክት ነው፡፡ አንድ ቡድን ተዋቅሮ መልሶ ማልማት የሚመራበት የህግ ማዕቀፍ ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ ጥናት አድርገን ጥነቱን መነሻ በማድረግ ነው የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ያለው፡፡ አሁን የመጀመሪያው ረቂቅ አልቆ ቀርቧል ሁለተኛውን ረቂቅ ተመልክተን በሶስተኛው አጠቃለን ለቢሮ እናቀርባለን፡፡ ከዛ ለካቢኒ ቀርቦ ሲጸድቅ እንደ አዲስ አበባ መልሶ ማልማት የሚመራበት ይሆናል›› ብለዋል፡፡
ስራ አስኪያጁ እንደሚሉት ጥናት ማካሄድ ያስፈለገው ችግሩ የተወሳሰበ በመሆኑ ነው፡፡ ሁኔታውን አስቸጋሪ የሚያደርገው አንዱ ነገር የቀበሌ ቤቶች ጉዳይ ነው፡፡ በከተማዋ ከ1መቶ 53 ሺ በላይ የቀበሌ ቤቶች አሉ፡፡ እነዚህ የቀበሌ ቤቶች በአነስተኛ ቦታ ላይ ተጠባብቀው ነው ያሉት፡፡ በነባር ይዞታቸው ላይ የተለያዩ የኢኮኖሚ ጥቅሞችን እያገኙ መተዳደሪያቸውን በዚያ ያደረጉ ዜጎች ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡ እነዚህን ወገኖች ዝም ብሎ አንስቶ ሌላ ቦታ ማስፈር ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ መኖሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን መተዳደሪያቸውንም አብረው አጥተዋል፡፡ ስለዚህ ቀጣይ ህይወታቸውን በምን መንገድ መግፋት እንደሚችሉ አብሮ መታሰብ አለበት፡፡
የተነሺዎች አካባቢ በሚለማበት ወቅት በነበሩበት ቦታ በዘላቂነት እስኪሰፍሩ ድረስ በጊዜያዊነት በምን መልኩ ማረፍ እንዳለባቸው አቅጣጫ መቀመጥ አለበት፡፡ እነዚህንና ሌሎች ችግሮችን መፍታት የሚያስችል ጥናት ነው የተደረገው፡፡ የመልሶ ማልማት ሥራ ሲካሄድ ነዋሪዎችን አፈናቅሎ ሳይሆን አካቶ መሆን ይኖርበታል፡፡ የመልሶ ማልማት ሥራ ነዋሪዎችን የሚያካትትና የሚያሳትፍ ከጎስቋላ አኗኗር የሚያላቅቅና ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያደርስ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ረገድ አዲሱ የመልሶ ማልማት ፕሮግራም ለነዋሪዎች ቅድሚያ የሚሰጥ ነው፡፡ ይህም የሚረጋገጠው በዋናነት ነዋሪዎችን በተፈናቀሉበት ቦታ ላይ በሚካሄደው ልማት ተጠቃሚ በማድረግ ነው፡፡
የህግ ማዕቀፉ ጸድቆ ስራ ላይ እስኪውል ድረስም ቢሆን የሚሰሩ ስራዎች ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ብቻ ይሆናሉ፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ወንዞችን ተከትለው የተገነቡ ቤቶች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ቤቶቹ የተገነቡት ወደ ወንዞች በጣም ተጠግተው ነው፡፡ በዋነኝነት እንዲህ ባለ አሰፋፈር ምክንያት ነው የከተማዋ ወንዞች ለብክለት የተጋለጡት፡፡ በእነዚህ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች በቅርቡ እንዲነሱ ይደረጋል፡፡ ነገር ግን በዘላቂነት እንዲሰፍሩ የሚደረገውም ከወንዙ አቅራቢ በእዚያው አካባቢ ይሆናል፡፡
በቅርቡ ዶክተር አብይ አህመድ በይፋ የከፈቱት በአዲስ አበባ ለገሃር አካባቢ በ50 ቢሊዮን ብር የሚገነባው የተቀናጀ የመኖሪያና አገልግሎት መስጫ_የልማት ፕሮጀክት የአካባቢውን ነዋሪዎች ሳያፈናቅል፤ ተጠቃሚነታቸውን ባረጋገጠ መልኩ እንደሚገነባ መገለጹ ይታወሳል። ፕሮጀክቱ በሚገነባበት ወቅት በአካባቢው የሚኖሩ 1 ሺህ 600 ያህል ዜጎች አካባቢያቸውን የማይለቁ ሲሆን ከባለሃብቶቹ በተገኘ_ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የተሻለ መኖሪያ ቤት ይገነባላቸዋል። በወቅቱ ዶክተር ዓብይ አህመድ የፕሮጀክቱ ግንባታ የለገሃር አካባቢን ታሪካዊ ይዘት ሳይለቅ እንደሚካሄድ የገለጹ ሲሆን በቀጣይም መሰል የመንደሮች ግንባታ እንደሚካሄድ ተናግረው ነበር። በአዲሱ መንደር በአጠቃላይ ከ4 ሺህ በላይ የመኖሪያ አፓርታማዎች ይገነባሉ ። የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ግንባታ ከ5 እስከ 7 አመት ይፈጃል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ጥር 2/2011
የትናየት ፈሩ