እንደ አልጀዚራ ዘገባ እአአ ታኅሣሥ 30 ቀን 2018 በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተጭበርብሯል መባሉና ውጤቱም ይፋ ሳይደረግ መዘግየቱ ኮንጎን ውጥረት ውስጥ አስገብቷታል፡፡ በተለይም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የምርጫውን ውጤት መተንበዩን ተከትሎ በመንግሥትም ሆነ በተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች የሚሰማው ጉምጉምታ በኮንጎ ሁከት ይቀሰቀሳል የሚል ሥጋት አሳድሯል፡፡
የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምርጫ ኮሚሽን በሀገሪቱ የሚገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የምርጫውን ውጤት አስመልክቶ የሰጠው መሰረተ ቢስ ትንበያ ኃላፊነት የጎደለውና ህግን ያልተከተለ ነው ሲል ነቅፏል፡፡ ነቀፋውን ያስከተለው የቤተክርስቲያኑ ጳጳስ በድምፅ ቆጠራው የአሸናፊው ማንነት በግልጽ ተለይቷል ማለታቸውን ተከትሎ ነው፡፡ በኮንጎ ውስጥ ትልቅ ተሰሚነት ካላቸው ተቋማት ውስጥ አንዱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሲሆን፤ ከ80 ሚሊዮን የሀገሪቱ ዜጎች 40 በመቶው የቤተክርስቲያኑ ተከታዮች ናቸው፡፡ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በሀገሪቱ ባለው ተደማጭነት 40 ሺ የምርጫ ታዛቢዎችን በመላ ሀገሪቱ በማሰማራት የምርጫውን ሂደት እንዲከታተል ቢደረግም ከምርጫ ኮሚሽን ውጪ የትኛውም አካል የምርጫውን ውጤት ማሳወቅ አይችልም የሚለውን መመሪያና ደንብ በመጣስ ውጤቱን ለመግለጽ መሞከሩ አስተችቶታል፡፡
የፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ አማካሪ በርናቤ ኪካያ ፤ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን በኩል የተላለፈው መልዕክት ወገንተኝነት የተንጸባረቀበትና የደጋፊነት መልክ የታየበት ነው በማለት ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ ሌሎች የሀገሪቱ ባለሥልጠናትም እንዲሁ የቤተክርስቲያኑ አስተያየት ህገ መንግሥቱን ብቻ ሳይሆን የምርጫውን ደንብ የሚጻረርና ብዥታን የሚፈጥር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የተሰጠው አስተያየት ሁከትን ሊቀሰቅስ የሚያስችል ጸያፍ ተግባር ነው በሚል የምርጫ ኮሚሽኑንም አስቆጥቷል፡፡ የምርጫ ኮሚሽኑ የምርጫውን ውጤት ባለፈው ዕሁድ ለማሳወቅ ቢፈልግም የሁሉም አካባቢዎች የቆጠራ ውጤት ባለመድረሱ ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ ሊዘገይ እንደሚችል ማሳወቁ ይታወሳል፡፡
መንግሥት ምርጫው በጥሩ ሁኔታ እንደተመራና እንደተጠናቀቀ ቢገልጽም የተቃዋሚ ፓርቲ ተወዳዳሪዎቹ ማርቲን ፋዩሉ እና ፍሌክስ ስከዲ ግን አንዳንድ እንከኖች እንደነበሩበት ጠቅሰዋል፡፡ ያም ሆኖ ሁሉም ተወዳዳሪዎች በየበኩላቸው ምርጫውን እንደሚያሸንፉ እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡
ትክክለኛ ያልሆነ የምርጫው ውጤትን መግለጽ ሊያስከትል የሚችለውን ቀውስ በተመለከተ የተለያዩ አካላት አስተያየቶችን እየሰጡ ይገኛል፡፡ ምርጫው ለኮንጎ የመጀመርያው የዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር የሚታይበት ሊሆን ይችላል ነገር ግን የምርጫው ውጤት የሚጭበረበር ከሆነ ልክ በ2006 እና በ2011 የምርጫ ዘመን በሀገሪቱ እንደሆነው ሁከትና ብጥብጥ ሊከሰት እንደሚችል ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ባስተላለፈው መልዕክት የመካከለኛው አፍሪካ ሀገራት የምርጫው ውጤት በትክክልም የኮንጎ ህዝብ ድምፅ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል ብሏል፡፡ የዩናይትድ ስቴት መንግሥትም እንዲሁ የሀገሪቱ ምርጫ ቦርድ ትክክለኛውን የምርጫ ውጤት እንዲያሳውቅና በምርጫ ሂደቱ ላይ ቅሬታ በሚያቀርቡ ግለሰቦች ላይ ምንም ዓይነት ማስፈራራትና ወከባ እንዳያደርስባቸው አሳስቧል፡፡ የአፍሪካ ህብረትም ተመሳሳይ መልዕክት እያስተላለፈ ይገኛል፡፡
ይህ የምርጫ ሂደት ውስጥ ውስጡን የተጋጋመ ተቃውሞ እንዳለበት የሚያመላክቱ ነገሮች አሉ፡፡ ሄዶ ሄዶ የምርጫው ውጤት ሲታወቅ መፈንዳቱ አይቀርም በማለት በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቃል አቀባይ ራቪና ሻምደሳኒ ያሳስባሉ፡፡ አያይዘውም ሁኔታውን በጥንቃቄ እየተመለከትነው ነው በማለት ሁሉም ወገን ሁከትን ከሚቀሰቅሱ ነገሮች መቆጠብ እንዳለበት ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
የምርጫው ውዝግብ ወትሮም ያልተረጋጋውንና ሚሊዮኖች ለሞት፤ ለረሀብና ለበሽታ የተዳረጉበት፤ አሁንም ታጣቂዎች የሚንቀሳቀሱበትን ምሥራቃዊ የሀገሪቱን ግዛት ቀውስ እንዳያባብሰውም ተፈርቷል፡፡ ቀደም ሲል የተረጋጋ ቀጣና ነው ይባል የነበረው የሀገሪቱ ምዕራባዊ ክፍልም አሁን አሁን የስጋት ቀጣና እየሆነ መጥቷል፡፡ አስቀድሞም ሊደረግ ለነበረው ምርጫ መራዘም ምክንያት የሆነው በዚሁ አካባቢ ማይ ዱምቢ በተባለው ግዛት በብሄረሰቦች መካከል የተፈጠረው አለመግባባትና የኢቮላም መከሰት ነበር፡፡
ያም ሆኖ ግን የካቢላ አስተዳደር ትክክለኛ ያልሆነ የምርጫ ውጤት እንዳይተላለፍ በሚል አስቀድሞ የኢንተርኔት አገልግሎቶችን አቋርጧል፡፡ በሀገሪቱ ተሰሚነት የነበረውን የፈረንሳይ ዓለም አቀፍ የሬዲዮ ጣቢያንና አንዳንድ ሀገር በቀል የሬዲዮ ጣቢያዎችንም አዘግቷል፡፡ ከምርጫው ውጤት መዘግየት በተጨማሪ እንዲህ ዓይነቱም ድርጊት ውጥረቱን አባብሶታል፡፡
ዩናይትድ ስቴት በኮንጎ ባለው ውጥረት 80 የሚጠጉ የታጠቁና በጦር አውሮፕላኖች ጭምር የሚደገፉ ወታደሮቿን በአጎራባች ሀገር ጋቦን አሰማርታለች፡፡ ዶናልድ ትራምፕ የወታደሮቹን ተልዕኮ አስመልክተው ለኮንግረንስ አባላት እንደገለጹት የአሜሪካን ዲፕሎማቶችና ዜጎች በኮንጎ አስጊ ነገር ቢገጥማቸው ከኪንሻሳ በሰላም እንዲወጡ መርዳት ነው ብለዋል፡፡
ጆሴፍ ካቢላ እአአ በ2001 ከአባታቸው በትረ ስልጣን ተረክበው ሀገሪቱን መምራት ከጀመሩ ወዲህ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን አንድ አድርጎ መምራትና ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ማስመዝገብ እንደቻሉ የሚመሰክሩላቸው እንዳሉ ሁሉ በጨቋኝነታቸውና የሀገሪቱን ዜጎች ህይወት በሚፈለገው መልክ አልለወጡም በሚል የሚተቿቸውም አሉ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 2/2011
ኢያሱ መሰለ