አዲስ አበባ፡- በአማራ ክልል በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ በመስጂዶችና ንብረቶች ላይ የደረሰውን ጉዳት መልሶ ለመገንባትና ተጎጂዎችን ለማቋቋም ባዘጋጀው የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ከ208 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ።
ምክር ቤቱ ትናንት በጽሕፈት ቤቱ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ የኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊና የድጋፍ አሰባሳቢ አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሼህ ቃሲም መሃመድ እንደገለፁት፤ ከጥር 22 ቀን 2012ዓ.ም ጀምሮ በሀገርና ከሀገር ውጪ ሁለት ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ በአገር ውስጥ በዓይነት የተለገሰውንና በውጭ አገር የተሰበሰበውን ገንዘብ ሳይጨምር ከ208 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ ተችሏል።
ከጥሬ ገንዘቡ በተጨማሪም በውጭ አገርና በአገር ውስጥ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ግምቱ ከ750 ሺ ብር በላይ የሚገመት የተለያዩ ከወርቅ፣ ከብርና ከነሐስ የተሰሩ ጌጣጌጦች፣ የእጅ ሰዓትና የሞባይል ቀፎዎች ገቢ መደረጋቸውንም ሰብሳቢው አስታውቀዋል።
በድጋፍ ማሰባሰቡ ሂደት በኢኮኖሚያዊ ችግር ምክንያት በልመና ከሚተዳደሩ ወገኖች አንስቶ ከፍተኛ ባለሀብቶች የተሳተፉ መሆናቸውንም ሰብሳቢው ጠቅሰው፤ ይህ እንዲሳካ ከሕዝበ ሙስሊሙ በተጨማሪ አዲስ አበባንና ድሬዳዋን ጨምሮ የሁሉም የክልል፣ የዞንና የወረዳ እስልምና ጉዳይ ምክር ቤቶች፣ የመስጂድ ኢማሞች፣ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች መሻኢሆችና ዱአቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።
የሞጣ አካባቢ ተወላጆች፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ ታዋቂ ሰዎችና የሀገር ሽማግሌዎች፣ በየአካባቢው የሚገኙ የመስጂድ ወጣት ጀምኣዎች፣ የክርስትና እምነት ተከታዮች፣ ባንኮች፣ የፌዴራልና የክልል ፀጥታ አካላት ለዚህ በጎ ተግባር የድርሻቸውን መወጣታቸውንም ሰብሳቢው አያይዘው ጠቅሰዋል።
በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በተከፈተው የዶላር አካውንት እስከ መጪው የካቲት 24 ቀን 2012ዓ.ም ድረስ ያሰባሰቡትን ገንዘብ ገቢ እንዲያደርጉም ሰብሳቢው ጥሪ አቀርበው፤ ከዚህ በኋላ በማንኛውም ሁኔታ በመስጅድ ውስጥ በሞጣ ተጎጂዎችና በጠቅላይ ምክር ቤቱ ስም የሚደረግ የገቢ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ የማይኖር መሆኑንም አመልክተዋል።
ጠቅላይ ምክር ቤቱ ተጎጂዎችን ለማቋቋሚያ የተሰበሰበውን ገንዘብ ለተጎጂዎች በአፋጣኝ መድረስ የሚችልበትን ሁኔታ የሚያመቻች ግብረ ኃይል አዋቅሮ ወደሥራ እንዲገባ በማድረግ ወገኖች ወደሥራቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተመልሰው እንደከዚህ ቀደሙ ራሳቸውንና አገራቸውን እንዲጠቅሙ የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።
የፈረሱት መስጂዶች ተመልሰው እንዲገነቡና ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ ግልጋሎት የሚሰጡ ተቋማት ግንባታን በተመለከተም በመስኩ ልምድ ካላቸው ባለሞያዎችና አማካሪ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት በአጭር ጊዜ ወደ ግንባታ እንዲገቡ የሚደረግ መሆኑንም ሰብሳቢው ገልጸው፤ ሕዝበ ሙስሊሙ በሞጣ ጉዳይ ያሳየውን መነቃቃትና ቀናነት ከመሪ ድርጅቱ ጋር በመሆን በቀጣይ ለሚኖረው ተልዕኮም ሁለንተናዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2012
አስናቀ ፀጋዬ