ወደ ሽሮ ሜዳ ካቀኑ የባህል አልባሳት ገበያን የሚገዳደሩ በቻይና የተዘጋጁ ምርቶች መመልከትዎ አይቀርም። በባህል አልባሳት መልክ የተዘጋጁ በርካታ የቻይና ምርቶችም በዋጋ ደረጃም ዝቅ ያሉ በመሆናቸው ገበያውን ለመቀላቀል ብዙ ጊዜ ስላልወሰደባቸው በርካታ ኢትዮጵያውያንም ሲሻሟቸው ይውላሉ።
ይሁንና የውጭ ዜጎች ይበልጡን ዋጋ የሚሰጡትና የሚወዱት በእጅ የተሰሩትን ትክክለኛ የባህል አልባሳትን መሆኑን ይናገራሉ። በመሆኑም በኢትዮጵያውያን በእጅ የሚዘጋጁ ባህላዊ አልባሳት በቻይና አልባሳት ምክንያት የሚደርስባቸውን የገበያ ጫና ለመቀነስ ምን መደረግ አለበት? የሚለውን የተለያዩ የውጭ ሀገራት ዜጎች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
ከወደ አሜሪካ የመጣችው ሚዳ ሞሪ እንደገለጸችው፤ ኢትዮጵያ ከጥጥ የሚሰሩ ባህላዊ ልብሶችን በመስራት ረጅም ዘመናትን አስቆጠራለች። የጊዜውን ርቀት ያክል ግን ዘርፉ ላይ ባህላዊ መንገዱን የሚያሻሽሉ አሠራሮችን ማዳበር ያስፈልጋል። ምርቶቹ በብዛት ለውጭ ገበያ ሲቀርቡ ከአምራቾቹም ባለፈ ሴክተሩ በገቢ ደረጃ የተሻለ ጥቅም ይገኛል።
እንደ ሚዳ ሞሪም በርካቶች በአድካሚ የባህላዊ አልባሳት ሥራ ላይ ተጠምደው እንደሚውሉ ትናገራለቸ። እንደ አሜሪካውያኖቹ ሃሳብ ከቻይና በብዛት የሚገቡ ጨርቃጨርቅ ምርቶች ገበያውን ስለሚቆጣጠሩት ባህላዊ አልባሳቱ አምራቾቹን በገቢ ረገድ ተጠቃሚ ማድረግ አልተቻለም።
በመሆኑም ይላሉ አሜሪካውያኖቹ፣ ከቻይና የሚመጣው ምርት ገደብ እንዲኖረው አሊያም ከነጭራሹ እንዲቆም ማድረግ አንዱ አማራጭ ነው። ከዚህ ባለፈ ለባህላዊ አልባሳት አምራቾች አነስተኛ ተቋማት የገንዘብ እና የገበያ አማራጮች በማስፋት ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል። ድጋፉ በዝቅተኛ ክፍያ የሚቀርቡትን የቻይና ምርቶችን በመወዳደር በአነስተኛ ዋጋ ገበያው ላይ ባህላዊ ምርቶች እንዲቀርቡ ያግዛል። በተጨማሪም በከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ መሸጫ ሱቆች በየአካባቢው በመክፈት የገበያ ዕድላቸውን ማስፋት ይገባል።
ካናዳዊቷ ወይዘሮ ካቲ ማርሻል በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ 700ሺህ ዜጎች በባህላዊ አልባሳት አምራችነት ላይ የተመሰረተ ኑሮ እንዳላቸው ይገመታል። ነገር ግን የአምራቾቹ ተጠቃሚነት እንዳያድግ ከተጋረጡት በርካታ ችግሮች አንዱ ከቻይና የሚገቡ ምርቶች ገበያውን መቆጣጠራቸው ነው።
በኢትዮጵያ የእደ ጥበብ ልብሶችን የሚደግፍ የተለየ ፖሊሲ የለም የሚሉት ወይዘሮ ካቲ፤ በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥትም የባህል አልባሳት አምራቾችን የሚደግፍ ግልጽ ፖሊሲ እና ስትራቴጂዎችን በማዘጋጀት ሊያሳድገው እንደሚገባ ይናገራሉ።
በተጨማሪም የባህል አልባሳት የተሻለ ገበያ እንዲኖራቸው እና አምራቾች ግብዓቶቻቸውን በአነስተኛ ዋጋ የሚያገኙበት መንገድ መፍጠር ያስፈልጋል ባይ ናቸው።
እንደ ወይዘሮ ካቲ ማርሻል ከሆነ፤ እደጥበብ አምራቾች በርካታ ምርቶችን እንዲያዘጋጁ እና ገበያው ላይ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዕድሎችን ማስፋት ያስፈልጋል። ለአብነትም አምራቾቹን ለማበረታታት የትምህርት ቤት ዩኒፎርሞች በባህላዊ መንገድ በእጅ ብቻ የተሰሩ ቢደረግ ዘርፉ ይነቃቃል።
ከዚህ በዘለለ ግን የባህል አልባሳት አምራቾች የእራሳቸው ምርት የአዕምሯዊ ጥበቃ እንዲያገኝ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ቢደረግ ገቢያቸውን ለማሳደግ ወሳኝ ድርሻ አለው።
ሌላው አስተያየቱን የሰጠን እንግሊዛዊው ሞር ቴስተን ሲሆን፤ እንደ እሱ አስተያየት የኢትዮጵያን የእደ ጥበብ አልባሳት የሚያዘጋጁ ሰዎች በድካም ውስጥ አልፈው የተወደደ ምርት የሚያቀርቡ ናቸው። ይሁንና በቻይና የሚመረቱ እና በአነስተኛ ዋጋ የሚቀርቡ የተለያዩ አልባሳት በመኖራቸው የባህል አልባሳት አምራቾቹ ከገበያ እየወጡ ስለመሆኑ መታዘቡን ያስረዳል።
እንደ ሞር አገላለጽ፤ በርካታ ሀገራት በርካሽ ዋጋ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች የሀገራቸውን አልባሳት ገበያ እንዳይጎዱ ጠንከር ያለ እርምጃ ይወስዳሉ። በኢትዮጵያም ለመፍትሄነት የቻይና ምርቶች ላይ የቀረጥ ጭማሪ እና ሌሎች እቀባዎችን በማድረግ የሀገር ውስጡ ምርት የበለጠ ገበያው ውስጥ ተወዳዳሪ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል።
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2012
ጌትነት ተስፋማርያም