አዲስ አበባ፡- የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች በአካባቢ ደህንነት ላይ እያስከተሉት ያለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ለመገደብ እንደሚያስችል ተገለጸ።
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን በትናንትናው ዕለት ያካሄደ ሲሆን የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ተመልክቷል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ለምለም አድጎ እንደገለጹት፣ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች በአካባቢ ደህንነት ላይ እያስከተሉት ያለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ከተወሰነ ዓመት በላይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ለመገደብ እንዲሁም ለጤና ጎጂ በሆኑ ምርቶች ላይ ያለውን የኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔን በመፈተሽ ማስተካከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አዋጁ ተዘጋጅቷል።
አዋጁ ላይ በተደረጉ ማሻሻያዎች ላይ ከአንድ ሺህ 300 ሲሲ ያልበለጠ የፈረስ ጉልበት ያላቸው ተሽከርካሪዎች እና ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ላይ ተጥሎ የነበረው ኤክሳይዝ ታክስ አዲስ በሀገር ውስጥ የሚገጣጠሙ፣ ሙሉ በሙሉ ተበትነው የቀረቡ፣ በሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪ እንዲገጣጠሙ በከፊል ተበትነው የገቡ እና አዲስ ሙሉ በሙሉ ተገጣጥመው የቀረቡ ላይ እንዲጣል የሚጠይቀው የኤክሳይዝ ታክስ ከ30 በመቶ ወደ 5 በመቶ ዝቅ እንዲል ማሻሻያ እንደተደረገበት ገልጸዋል።
በሥራ ላይ ያለው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ለረጅም ጊዜ በሥራ ላይ የቆየ በመሆኑ እና የማምረቻ ወጪን መሠረት አድርጎ የሚሰላ በመሆኑ ግልፅነት የሚጎድለው መሆኑን አውስተው ይህን ለማስቀረትም አዲሱ አዋጅ መፍትሄ የሚያበጅ ነው ብለዋል።
በሲጋራ ላይ የተጣለው የኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔ በፓኬት በዋጋው 30 በመቶ እንዲሁም በፍሬ አምስት ብር የነበረው በኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻያው ሦስት ብር ተጨምሮ ስምንት ብር እንዲሆን መደረጉንም ተናግረዋል። የታሸገ ውሃም ላይ ተጥሎ የነበረው ኤክሳይዝ ታክስ ከ15 በመቶ ወደ 10 በመቶ ዝቅ እንዲል መደረጉን ተብራርቷል። የቀረበውን አዋጅ በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አዋጁን በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።
በተያያዘም ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን ሕጋዊ ሰውነት ለመስጠት የወጣ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሕግ፣ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአንድ ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ መርቷል። ምክር ቤቱ በትናንት ውሎው ሰባት አዋጆችን ሲያጸድቅ ሁለቱ ደግሞ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ የመራቸው መሆኑ ታውቋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2012
ሙሐመድ ሁሴን