የዛሬው ባለውለታችን ከኢትዮጵያም አልፎ የአፍሪካ ኩራት መሆን የቻለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ታሪክ ሲወሳ አብረው የሚነሱት፣ የንግድ ጄት (Jet) በማብረር የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሆን የቻሉት ካፒቴን ዓለማየሁ አበበ ናቸው።
ዓለማየሁ ከአቶ አበበ ደስታ እና ከወይዘሮ ጥሩነሽ ጎበና በቀድሞው የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት፣ ጨርጨር አውራጃ የካቲት 16 ቀን 1916 ዓ.ም ተወለደ።የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በሐረር ከተማ ራስ መኰንን እና በካቶሊክ ሚሲዮን ትምህርት ቤቶች በአማርኛና በፈረንሣይኛ ተከታትሏል። ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ትምህርቱን አቋርጦ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ነበር።የፋሺስት አስተዳደር ከተወገደ በኋላ ደግሞ ያቋረጠውን ትምህርት ለመቀጠል ወደ አዲስ አበባ ተጉዞ አባቱ በወልወል ጦርነት መሰዋታቸውን የሚገልፅ ማስረጃ በማቅረብ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሎ አጠናቀቀ። በትምህርቱ ባስመዘገበው ከፍተኛ ውጤትም ከንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ እጅ ሽልማት ተቀብሏል። በወቅቱ ዓለማየሁ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጣሊያንኛ፣ አረብኛና እንግሊዝኛ መናገር ይችል ነበር።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በከፍተኛ ውጤት ያጠናቀቁ ተማሪዎች ወደ አቪዬሽን (የበረራ ሙያ) ትምህርት እንዲገቡ ሲደረግ ዓለማየሁ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው በከፍተኛ ውጤት እንዲሁም አካላዊ ቁመናውም ለበረራ ትምህርት የሚመጥን ስለነበርና የቀረቡለትን የመመዘኛ ጥያቄዎች በብቃት በመመለሱ የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን ቻለ። ከዓለማየሁ በተጨማሪ ሌሎች ሦስት ተማሪዎችም ወደ ሲቪል አቪዬሽን መስሪያ ቤት ሄደው እንዲያመለክቱ ተነገራቸው።
ወቅቱ የአቪዬሽን ትምህርት ቤት የሚገኘው ከአዲስ አበባ ወደ ሰበታ መውጫ መንገድ በኩል ‹‹አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ›› በሚባለው ስፍራ ነበር። የመጀመሪያው የአየር ኃይል የአቪዬሽን ትምህርት ቤት የተቋቋመውም በዚያው ግቢ ውስጥ ነው። በኮሎኔል ጆን ሮቢንሰንና በሌሎች ሦስት አፍሪካ-አሜሪካውያን አስተማሪዎች አማካኝነት የበረራ ትምህርት ተጀመረ። ይሁን እንጂ የዓለማየሁ የአቪዬሽን ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ዓመት ቆይታ እጅግ ፈታኝ ነበር። የአስተማሪና የአውሮፕላን እጥረት የነዓለማየሁን ጉዞ ከባድ አድርጎባቸው የነበረ ቢሆንም ቮን ሮዘን የተባሉ ስዊድናዊ አንድ አውሮፕላንና ሦስት አሰልጣኞችን ይዘው አዲስ አበባ መግባታቸው ትልቅ ለውጥ አመጣ። ዕጩ መኮንን ዓለማየሁ አበበም ካፒቴን ቤንሰን በተባሉ አሰልጣኝ መሰልጠን ቻለ።
ከስዊድን የበረራ አሠልጣኞች በቀሰመው ትምህርት ስልጠናውን በብቃት በማጠናቀቅ በ1938 ዓ.ም የመጀመርያውን የብቻ በረራ (Solo Flight) ማድረግ ቻለ። በልጅነቱ ወደ ሰማይ በማንጋጠጥ የሚበሩ አውሮፕላኖችን በመመልከት አብራሪ የመሆን ፍላጎት ያደረበት ዓለማየሁ፣ ከሰማይ ሆኖ የኢትዮጵያን ምድር ቁልቁል መቃኘት ቻለ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢትዮጵያ አምስት ስዊድን ሠራሽ አውሮፕላኖችን ስትገዛ ዓለማየሁና ሌሎች አራት ኢትዮጵያውያን አውሮፕላኖቹን ይዘው ከስዊድን ወደ ኢትዮጵያ በርረዋል። በርካታ አፍሪካውያን የነፃነትን ሕልም በሚያልሙበት በዚያ ወቅት ኢትዮጵያውያን ግን የአፍሪካንና የአውሮፓን አየር እየሰነጠቁ ያልፉ ነበር።
ዓለማየሁ ቀስ በቀስ ከባለ አንድ ሞተሩ ሳፊር ወደ ባለሁለት ሞተሩ ሴስና ተሸጋገረ።ከዚያም በቢ-17 (B-17) እና በኤል-5 (L-5) አውሮፕላኖች በተደረጉ በረራዎች ከሰለጠኑና አውሮፕላኖቹን ከሚያበርሩ መካከል አንዱና ዋነኛው ለመሆን በቃ። ለተጨማሪ የበረራ ትምህርት ስልጠና ወደ ስዊድን ሄደ። ዓለማየሁ በስካንድኔቪያ የነበረው የአንድ ዓመት ቆይታ ፍሬያማ ነበር። ከስዊድን እንደተመለሰ በታኅሣሥ 1942 ዓ.ም ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በተገኙበት የአየር ኃይል የምክትል መቶ አለቃነት ማዕረግ የበረራ ክንፍ (ዊንግ) አገኘ፤ልዩ ሽልማትም ተቀበለ፡፡
ምክትል መቶ አለቃ ዓለማየሁ ከተዋጊ አውሮፕላን አብራሪነት ወደ በረራ አስተማሪነት አዘነበለ። ለተጨማሪ ትምህርት ወደ እንግሊዝ ለመጓዝ እየተዘጋጀ በነበረበት ወቅት በተፈጠረ አጋጣሚ ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ አዞረ። ዓለማየሁ የኢትዮጵያ አየር መንገድን መቀላቀል የቻለው በኢትዮጵያ አየር ኃይል በኩል በማለፍ ነው። በ1943 ዓ.ም ብቃታቸው የተመሰከረላቸውና ምርጥ የሚባሉ አብራሪዎች ከአየር ኃይል ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲዛወሩ በተወሰነው መሠረት፣ ዓለማየሁ ከተመራጮቹ መካከል አንዱ መሆን ችሎ መድረሻው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሆነ፡፡
ዓለማየሁ አየር መንገዱን ከተቀላቀለ በኋላ የክፍል ትምህርቱንና የምስለ በረራ ስልጠናውን በካይሮ ተከታተለ። ቀደም ባሉት ጊዜያት በተሠሩ አውሮፕላኖች አየር መንገዱን ውጤታማ ማድረግ ስላልተቻለ ምቾትና ፍጥነት ያላቸው አውሮፕላኖች ተገዙ። ዓለማየሁም የእነዚህ አውሮፕላኖች ረዳት አብራሪ ሆኖ ተሰማራ። በወቅቱ የአየር መንገዱን አስተዳደር ይዘው የነበሩት አሜሪካውያን በዘረኝነት ዕሳቤ ምክንያት ዓለማየሁ የካፒቴንነት ማዕረግ/ደረጃ የሚያገኝበትን ጊዜ አራዘሙበት። በጥር 1950 ዓ.ም የካፒቴንነት ማዕረግ አግኝቶ የአየር መንገዱ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ካፒቴን መሆን ቻለ።
ካፒቴን ዓለማየሁ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓቢይ ተግባራቸውን ማከናወን የጀመሩት በ1950 ዓ.ም የመጀመሪያው የንግድ አውሮፕላን (ዲሲ-3/ሲ47 (DC-3/C47)) አዛዥ በመሆንና አውሮፕላኑን ብቻቸውን በማብረር ነበር።ካፒቴን ዓለማየሁ ገና ከአስር ዓመታቸው ጀምሮ አውሮፕላን በሰማይ ላይ ሲበር ሲያዩ አውሮፕላን አብራሪ የመሆን ሕልም እንደነበራቸው ታሪካቸው ያስረዳል። ሕልማቸውን ለማሳካት ጠንካራ ትጋትና መልካም ድስፕሊን የነበራቸው ካፒቴን ዓለማየሁ፣ በ1950 ዓ.ም የመጀመሪያውን ጀት (Commercial Jet) በማብረር በዘርፉ ፈር ቀዳጅ ኢትዮጵያዊ እንዲሁም አፍሪካዊ ለመሆን በቅተዋል። ከዚያ ቀደም ባለው ጊዜ በነበረው የኢትዮጵያ የንግድ አውሮፕላን ታሪክ ላይ ስማቸው ሰፍሮ የሚገኙት የውጭ አገራት አብራሪዎች ናቸው። በዚያ ታሪክ ላይ ስሙን በቀዳሚነት ማስፈር የቻለው ኢትዮጵያዊ በወቅቱ የ34 ዓመት ወጣት የነበረው ካፒቴን ዓለማየሁ አበበ ደስታ ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ ወደ ጄት ዘመን ሲሸጋገር ከፋና ወጊ አብራሪዎች ተጠቃሹ ካፒቴን ዓለማየሁ አበበ ነበሩ።በ1950ዎቹ መጀመሪያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጄት አውሮፕላኖችን ከውጭ ለማስመጣት ቢያቅድም አሮጌው የአውሮፕላን ማረፊያ (የልደታ ኦልድ ኤርፖርት) ጄቶችን ለማሳረፍና ለማስተናገድ ምቹ አልነበረም። ስለሆነም መሠረታዊ መስፈርቱን ለማሟላት አሮጌውን የአውሮፕላን ማረፊያ መቀየር አስገዳጅ ሆኖ ተገኘ። በዚህም ምክንያት አዲስ አውሮፕላን ማረፊያ በቦሌ እንዲታነፅ ተደረገ።በኅዳር 1955 ዓ.ም ጄት አውሮፕላኑ (ቦይንግ 720-B) በካፒቴን ዓለማየሁ አበበና ካፒቴን አዳሙ መድኃኔ አማካይነት አዲስ አበባ ገባ። ከ57 ዓመታት በፊት የመጀመሪያው ቦይንግ 720-ቢ (Boeing 720-B) አውሮፕላንን በዋና አብራሪነት (ካፒቴንነት) ያበረሩት ካፒቴን ዓለማየሁ፣ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ጄት አብራሪም መሆን ችለዋል።
ካፒቴን ዓለማየሁ በሦስት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገልግሎት ዘመናቸው ከመጀመርያ የበረራ መኰንንነት እስከ ካፒቴንነት (ከመጀመርያው የቦይንግ 720-B ጄት ካፒቴንነት) እስከ አየር መንገዱ የበረራ ዘርፍ ምክትልና ዋና ኃላፊነት (ከ1948 እስከ 1960 ዓ.ም) ድረስ ሠርተዋል። ከ1961 እስከ 1972 ዓ.ም ደግሞ የዓለም አቀፍ በረራዎች ዳይሬክተር፣ የበረራ ኦፕሬሽን ረዳት ሥራ አስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል። በ1968 ዓ.ም የመጀመርያው አፍሪካዊ የቦይንግ 707 ጄት ካፒቴን ሆነው ሲሾሙ፣ በ1972 ዓ.ም የጄት አብራሪዎች (ካፒቴኖች) ፈታኝ በመሆን አገልግለዋል።
ካፒቴን ዓለማየሁ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አገልግሎታቸውን በ1974 ዓ.ም ፈጽመው ከተሰናበቱ በኋላ፣ በኡጋንዳና በየመን አየር መንገዶች ውስጥ በአሠልጣኝነትና በአማካሪነት ለአምስት ዓመታት ያህል ሠርተው የበረራ ምዕራፋቸውን ቋጭተዋል።
ካፒቴን ዓለማየሁ አበበ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሥራ አስፈፃሚ የነበሩትን ኮሎኔል ስምረት መድኃኔን አየር ኃይል ውስጥ በነበሩበት ወቅት እንዳስተማሯቸው ታሪካቸው ያስረዳል። ጉዳዩን በተመለከተም ካፒቴን ዓለማየሁ፣ ‹‹ … ኮሎኔል ስምረት ወደ አየር መንገዱ የመጡት የድርጅቱ አመራር ሆነው ነው፤ ተማሪዬ አለቃዬ ሆነ …›› በማለት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሚያሳትመው ‹‹ሰላምታ›› መጽሔት እየሳቁ ተናግረው ነበር፡፡
‹‹ሰላምታ›› መጽሔት በአንድ ወቅት ባሳተመው ዕትሙ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ‹‹የአፍሪካ ስኬታማው አየር መንገድ እንዲሆን ያስቻሉት ግለሰቦች›› ብሎ በግንባር ቀደምትነት ከጠቀሳቸው ሰዎች መካከል አንዱ ካፒቴን ዓለማሁ አበበ ናቸው፡፡
በሦስቱ መንግሥታት ዘመን በከፍተኛ የአገርና የሙያ ፍቅር አገራቸውን ያገለገሉት ካፒቴን ዓለማየሁ፣ በሰማይ ላይ ተግባር የተፈተነውን ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውን ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ በማሰብ በ1997 ዓ.ም ‹‹ሕይወቴ በምድርና በአየር›› የሚል መጽሐፍ አሳትመዋል። በመጽሐፋቸው ውስጥ በልጅነታቸው አውሮፕላኖች ሲበሩ ሲመለከቱ እርሳቸውም አውሮፕላን አብራሪ የመሆን ፍላጎት እንዳደረባቸው ጠቅሰዋል። ከዚህ በተጨማሪም በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ተወልደው ባደጉበት የምሥራቅ ኢትዮጵያ የአየር ክልል ላይ የተመለከቱትና በእንግሊዝና በኢጣሊያ የጦር አውሮፕላኖች መካከል የነበረው የአየር ላይ ፍልሚያ አውሮፕላን አብራሪ የመሆን ፍላጎታቸውን እንዳጠናከረው ታሪካቸው ያመለ ክታል።ካፒቴን ዓለማየሁ መጽሐፋቸው ላይ ትውስታቸውን እንዲህ አስፍረዋል …
‹‹. . . የአብራሪነት ኃላፊነቱን ከተረከብኩ በኋላ አንዳንድ መንገደኞች አብራሪው ነጭ ባለመሆኑ ከሚያሳዩት መደናገጥ በቀር ምንም እንከን ሳያጋጥመኝ አየር መንገዱ በሚገለገልባቸው አፍሪካና አውሮፓ መብረር ጀመርኩ።በስልሳዎቹ መጀመርያ ላይ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ገዥዎች ቀንበር ነፃ ለመውጣት የሚታገሉበት ወቅት ስለነበር ጥቁር ፓይለት በሚያበረው ዘመናዊ ጄት ለመሳፈር እንኳን ለባዕዳን ለወገኖቻችንም ቢሆን መደናገጥን ፈጥሮ ነበር።ይኸው የመጀመርያ ዓለም አቀፍ በረራ አብቅቶ መሬት እንዳረፍን መንገደኞቹ ሲሰናበቱን ከልብ የመነጨ ምሥጋና ያቀርቡልን ነበር።አንዳንዶች ኢትዮጵያውያንማ ማመኑም እየቸገራቸው ሳይሆን አይቀርም በአድናቆት ይመለከቱንና ያነጋግሩን ነበር። በተከታታይ በረራዎች የመንገደኞቼ ሥጋትና ጥርጣሬ ወደ መተማመን ተለውጦ ባየሁትና በሰማሁት ቁጥር የሥራ ባልደረቦቼም ሆኑ እኔ ደስታ ይሰማን ነበር።በሥራ ውጤት እምነት ከማግኘት የበለጠ ምን ነገር ይኖራል? እርግጥ ነው ስንት ፈተናና በትዕግሥት አልፌ ለዚያ ደረጃ እንደበቃሁ መንገደኞቼ አያውቁም ነበር።ቢያውቁስ ኑሮ ‹አፍሪካዊ ጄት ሲያበር ለመጀመሪያ ጊዜ በማየታችሁ ለምን ትፈራላችሁ? ለምንስ ትጠራጠራላችሁ?› ብሎ መጠየቅስ ይቻል ነበር ? በእኔ ላይ የደረሰው ዓይነት በተከታዮቹ አብራሪዎች ላይም ደርሶ እነሱም በትዕግሥትና በጽናት አልፈውታል … ››
ካፒቴን ዓለማየሁ ለጥቂት ቀናት ያህል ታመው ቆይተው፣ በተወለዱ በ94 ዓመታቸው፣ ታኅሣሥ 26 ቀን 2010 ዓ.ም አርፈዋል። ስርዓተ ቀብራቸው ታኅሣሥ 28 ቀን 2010 ዓ.ም በጴጥሮስ ወጳውሎስ የካቶሊክ መካነ መቃብር ተፈጽሟል። ካፒቴን ዓለማየሁ፣ ባለትዳርና የአራት ሴቶችና የአራት ወንዶች ልጆች አባት፣ እንዲሁም የአራት የልጅ ልጆች አያት ነበሩ፡፡
በካፒቴን ዓለማየሁ ስርዓተ ቀብር ላይ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የሥራ ሚኒስትርና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሊቀመንበር የነበሩት ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም፣ የልዑል መኰንን ኃይለሥላሴ ባለቤት የነበሩት ልዕልት ሣራ ግዛው፣ ልዑል በዕደ ማርያም መኰንን ኃይለ ሥላሴ እንዲሁም የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኮሎኔል ስምረት መድኃኔ ተገኝተው ነበር።
በአትላንቲክ ሰማይ ላይ የበረሩት የመጀመሪያው (ጥቁር) አፍሪካዊ የንግድ ጄት (Commercial Jet) አብራሪው ካፒቴን ዓለማየሁ አበበ፣ ከልጅነታቸው ጀምሮ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈው ለትልቅ ደረጃ የበቁ ታላቅ አርዓያ ናቸው። መሰናክሎችን በብቃት በማለፍ ምኞታቸውን ማሳካት በመቻላቸውም …
‹‹ … በምድር እንደጉንዳን ታተረ፣
በሰማይ እንደአሞራ በረረ፡፡
ጽናትን ተምሮ ከትዕግሥት ሞግዚቱ፣
ታተረ እንደጉንዳን በወጣትነቱ፣
ሕልሙን እውን ሊያደርግ ተግቶ በመሥራቱ፣
በረረ እንደንስር በጎልማሳነቱ …›› የሚል የውዳሴ ግጥም ተገጥሞላቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 4/2012
አንተነህ ቸሬ