. ዳያስፖራው ማህበረሰብ ለአገሪቱ ሰላም የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ቃል ገብቷል
አዲስ አበባ፡- ዳያስፖራው ሚዲያውን በአገሪቱ ውስጥ የተሰራጨውን የጥላቻ ተረክ ለመለወጥ እንዲጠቀምበት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጥሪ አቀረቡ:: የዳያስፖራው ማህበረሰብም ለአገሪቱ ሰላም የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ቃል ገብቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ትናንትና “ዳያስፖራው ለአገር ሠላም ግንባታ” በሚል መሪ ሐሳብ ባዘጋጀው አገር አቀፍ የውይይት መድረክ በክብር እንግድነት የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ዳያስፖራው ማህበረሰብ አገርን መጥቀም የሚችሉ በርካታ ሀብቶች እጁ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የሚዲያ ባለቤት የሆነው ዳስፖራው ማህበረሰብ በፍቅርና በመቻቻል ለዘመናት አንድነቷን አስጠብቃ በኖረችው አገር ውስጥ በህዝቡ መካከል ክፍፍልና ግጭት እንዲፈጠር እያደረገ ያለውን የተሳሳተ መንገድ ለመለወጥ እንዲጠቀምበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሚኒስትሩ ዳያስፖራው የያዘውን ሚዲያ የኢትዮጵያ ህዝቦች ለዘመናት የገነቡትን መልካም እሴት እንዲጎለብት በመሥራት የሚያራርቀውንና የሚከፋፍለውን ሳይሆን የሚያቀራርበውን፣ መናናቅንና መተላለቅን ሳይሆን መከባበርንና መደጋገፍን፣ መለያየትን ሳይሆን አንድነትንና ሕብረትን ለማጠናከርና በህዝቦች መካከል መቀራረብና ሰላማዊ ግንኙነት እንዲዳብር ለማድረግ ሊጠቀምበት የሚችል መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብራሃም ስዩም በበኩላቸው ማህበሩ ከተመሰረተበት ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ዳያስፖራው ማህበረሰብ በተደራጀ መንገድ በአገሩ ሁለንተናዊ ጉዳይ እንዲሳተፍ ለማስቻል በርካታ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውንና አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመው፤ ይሁን እንጂ ዳያስፖራው ያለ ልዩነት ሁሉም በአገሩ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እንዲሳተፍ ከማድረግ አኳያ በርካታ የሚቀሩ ሥራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
አቶ አብራሃም የሐሳብ፣ የሃይማኖትና የብሔር ልዩነቶች ቢኖሩንም ልዩነቶቹ ከፈጣሪ የተቸሩን ውበታችን እንጂ ችግሮቻችን ስላልሆኑ ሁላችንም በአንድነት ሆነን ለአገራችን ሰላም የምንችለውን ለማበርከት የምክክር መድረኩን ማዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡
እንደ አቶ አብራሃም ገለፃ እንደቀድሞው በልዩነቶች ውስጥ ተከባብሮና ተፈቃቅሮ በአንድነት መኖር ባለመቻሉ በአሁኑ ሰዓት በአገሪቱ ውስጥ የሰላም እጦት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል::
በሌሎች አገራት በሩቅ ሲሰሙ የነበሩ አሳዛኝ የግጭትና የሞት ዜናዎች በእኛም አገር እንደ ዋዛ በየቀኑ የሚሰሙና እየተለመዱ መምጣታቸው ማህበሩን በእጅጉ እያሳሰበው ነው፡፡ በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን መላው የዳያስፖራ ማህበረሰብ የበኩሉን ያበረክታል፡፡ ለዚህም ከምክክር መድረኩ በኋላ በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ሰላም ለማስጠበቅ የሚሳተፉበት ራሱን የቻለ የዳያስፖራ የሰላም ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 4/2012
ይበል ካሳ