“መንገዱ ተሰርቶ ካየነው እንደገና የተወለድን ያህል ይሰማናል!” የሚሉት በናንሴቦ ወረዳ የእምነት መቻቻል አባቶች ሰብሳቢ አቶ ከድር ቦሩ ናቸው፡፡ መንገዱ ለህብረተሰቡ የሚሰጠው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ የጎላ ነው፡፡ ለረጅም ዓመታት በርካታ እናቶች በመንገዱ አስቸጋሪነት ምክንያት የተሻለ ህክምና ለማግኝት ወደ ሆስፒታል እየሄዱ እያለ ለህልፈት ተዳርገዋል ፡፡የመንገዱ አስቸጋሪነት በህብረተሰቡም ገቢ ሆነ በከተማዋ ዕድገት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡
ለአብነት ያህል የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችንና የፍጆታ ዕቃዎችን ገዝቶ ለማምጣት አስቸጋሪ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በክረምት ወቅት ሰው ከቤቱ መውጣት አይችልም፡፡ አካባቢው ለምና ቡና አብቃይ ቢሆንም ገበሬው ባመረተው ልክ ተጠቃሚ አልሆነም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መንገዱ አስቸጋሪ ስለሆነ ነው፡፡ የተጀመረው መንገድ ግንባታ በወቅቱ ከተጠናቀቀ ገበሬው ያመረተውን ምርት በቀላሉ ወደ ገበያ በማቅረብ መሸጥና መለወጥ ይችላል፡፡ይህም ገበሬውን ተጠቃሚ ከማድረጉ ባለፈም ለአካባቢው የሚተርፍ ይሆናል፡፡ ስለዚህ መንገዱ በተባለለት ጊዜ ተሰርቶ እንዲጠናቀቅ መንግስት ክትትል ሊያደርግ ይገባል፡፡ ማህበረሰቡም መንገዱ ተጠናቆ የተቀላጠፈ የትራንስፖርት ተጠቃሚ እንዲሆን አስፈላጊውን ሁሉ ትብብር ማድረግ ይኖርበታል ሲሉ አቶ ከድር መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የኤዶ-ሰሮፍታ-ወርቃ የመንገድ ፕሮጀክት በምዕራብ አርሲ ዞን፤ ከአዲስ አበባ 300፤ ከሻሸመኔ ከተማ ደግሞ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ኤዶ ከተማ ተነስቶ የዶዶላን እና የናንሴቦ ወረዳዎችን ያገናኛል፡፡ መንገዱ እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ የአካባቢው ነዋሪ ለዘመናት ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና ውስጥ ቆይቷል፡፡
ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የመንገዱ መገንባት በናንሴቦ ወረዳ በ16 ቀበሌዎች የሚመረቱትን በዓለም ገበያ ተፈላጊነት ያላቸው የቡና ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል፡፡ በተጨማሪም አካባቢው በወርቅ፤ በእምነበረድ እና በሌሎች ማዕድናት ሀብት የታደለ በመሆኑ የአካባቢውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ማሳደግ ያስችላል፡፡
የመንገዱ መሰራት ለህብረተሰቡ የሚያበረክተው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው የሚሉት ደግሞ በናንሴቦ ወረዳ ተወልደው ያደጉት አቶ በቀለ ባልቻ ናቸው፡፡ የመንገዱ ችግር እጅግ የከፋ እንደመሆኑ አንድ መኪና ተገዝቶ አንድ አመት ሳይሰራ ለብልሽት ይዳረጋል፡፡ የመገልበጥ አደጋ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ሲሆን በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል፡፡ “መኪናው እኛን ሳይሆን የሚሸከመው እኛ ነን መኪናውን ተሸክመን የምንሄደው ማለት ይቻላል፡፡ ከጧቱ 12 ሰዓት ከናንሴቦ ተነስተን ቀኑን ሙሉ መኪናውን ስንጎትት ውለን ዶዶላ ምሽት 12 ሰዓት እንገባለን፡፡ በዚህ መሐል እናቶችና ሕጻናት ለከፋ ጉዳትና ለሞት ይዳረጋሉ፡፡ መንገዱ እንዲሰራ መጠየቅ ከጀመርን ብዙ ዓመታት አልፈዋል፡፡ እስካሁን ይሰራል ብቻ ነበር የሚባለው አሁን ግን ይኸው ጅማሮውን ማየት ችለናል፤ ለዚህም በጣም ደስተኞች ነን፡፡ ከዚህም በላይ መንገዱ ከተባለው ጊዜ ባጠረ መንገድ እንዲሰራ እንፈልጋለን፡፡ ስለዚህ በጉልበትም ሆነ በገንዘብ ለመንገዱ ስራ ለመተባበር ዝግጁ ነን” ይላሉ፡፡
“የናንሴቦ ወረዳ የመንገድ ችግር የከፋ ነው” የሚሉት ቄስ ድጋፌ ወልደማርያም የታመመ ሰው በሸክም ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ 50 እና 60 ብር የነበረው ትራንስፖርት ዋጋ በአሁኑ ጊዜ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከ200 መቶ እስከ 250 ብር ድረስ የሚጠይቁበት ሁኔታ አለ፡፡ አሁን መንገዱ ከተጀመረ ህብረተሰቡ በማንኛውም መንገድ ተባብሮ ከችግሩ ለመላቀቅ ይፈልጋል፡፡ አራት ዓመት ለእኛ አራት ወር እንደማለት ነው፡፡ ስለዚህ መንግስት ሥራውን ለስራ ተቋራጭ ሰጠሁ ብሎ መቀመጥ የለበትም፡፡ ከፍተኛ ክትትል በማድረግ መንገዱ ከፍጻሜ እንዲደርስ ማድረግ ይጠበቅበታልም ብለዋል፡፡
ወረዳዋ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩባት ወረዳ መሆኗን የገለጹት የናንሴቦ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ በረንዳ ቃበቶ ናቸው፡፡ የኦሮሞ፤ የሲዳማና የአማራ ብሄሮች በወረዳው ተቻችለውና ተከባብረው ይኖሩባታል፡፡ ወረዳዋ የምትታወቀው በቡና ምርት ሲሆን፤ በዓመት ከ70 ሚሊዮን 600 ሺህ ብር በላይ ለመንግስት ገቢ ይደረጋል፡፡ በሌላ በኩል ህብረተሰቡ ዕድሜ ልኩን በመንገድ በመቸገሩ፤ ላለፉት 20 ዓመታት መንገዱ ይሰራል የሚል ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ በተለይም የመንግስት ሰራተኞች ባለው የመንገድ ችግር የሚደርስባቸውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና መቋቋም ስላቃታቸው ሥራቸውን ትተውና አካባቢውን ለቅቀው ይሄዳሉ፡፡
እንደ ወረዳው አስተዳዳሪ ገለጻ አሁን መንገዱ ግንባታ መጀመሩ የማህበረሰቡን የረጅም ጊዜ የመንገድ ጥያቄ ስለሚመልስ በጣም ደስተኞች ነን፡፡ ወረዳዋ የደቡብን ክልል የምታዋስን እንደመሆኗ መንገዱ በደቡብ ከበንሳ እስከወርቃ፤ በኦሮሚያ በኩል ደግሞ ከኤዶ መገንጠያ እስከወርቃ ይሰራል፡፡ መንገዱ የተያዘለት ጊዜ አራት ዓመታት ቢሆንም እኛ በፍጥነት ተሰርቶ እንዲጠናቀቅ የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን፡፡ ምክንያቱም የመንገዱ መሰራት ከማንም በላይ ጥቅሙ ለአካባቢው ማህበረሰብ ነው፡፡
በተለይም የደቡብና የኦሮሚያ ክልሎችን በማገናኘት ለህዝቡ የሚያበረክተው ኢኮኖሚያዊ እድገትና ማህበራዊ ትስስር የላቀ ድርሻ አለው፡፡ ወረዳዋ ለገበያ ተፈላጊ የሆኑ ከብቶች ጨምሮ እንደ ቡና፤ ማርና ፍራፍሬ ምርቶች በማቅረብ ትታወቃለች፡፡ የአካባቢው ቡና፤ በተለይም ቡልጋ በሚባል ቀበሌ ውስጥ የሚገኘው ቡና በተፈጥሮ መልኩ የሚመረት(ኦርጋኒክ) በመሆኑ በጣም ተመራጭ ነው፤ የተመረበት አካባቢ ታሽጎ ነው ቀጥታ ወደ አውሮፓ ገበያ የሚላከው፡፡ ይህም ወረዳዋ በኢኮኖሚ የተሻለ ዕድገት እንድታስመዘግብ ያግዛታል ሲሉ አቶ በረንዳ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
መንገድ የልማት አውታር መሆኑን የገለጹት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ፤ “73 ኪሎ ሜትር የመንገድ ስራ ትልቅ ብር የሚጠይቅ እንደመሆኑ መንገዱ ሲሰራ አጠቃላይ የአካባቢውን ኢኮኖሚ ያንቀሳቅሳል፤ ለወጣቶችም የስራ እድል ይፈጥራል” ብለዋል፡፡ ቦታው ቁልፍና ብዙ ሀብት ያለው አካባቢ ስለሆነ የመንገዱ መሰራት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡ ህብረተሰቡ መንገዱ እንዲጀመር ያደረገውን ትግል አስታውሰው፤ በቀጣይም መንገዱ እስኪጠናቀቅ ድረስ እንዲተባበር በአደራ ጭምር አሳስበዋል፡፡
በሌላ በኩል የናንሴቦ ወረዳ ወርቃ ከተማ ነዋሪው ሀጂ ሙስጠፋ የወረዳው ቡና ከዚህ በፊት በሲዳማ ስም ይጠራ እንደነበር ገልፀው፤ አሁን ግን ወረዳው ባደረገው እንቅስቃሴ በወረዳው ስም እንዲጠራ ተደርጓል፤ ይላሉ፡፡አሁን የአካባቢው ቡና መጠሪያው ‹‹ምዕራብ አርሲ ዞን ናንሴቦ ቡና›› በመባል በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ተሰይሟል፡፡ ቡናው ተወዳጅና እውቅና ያለው በመሆኑ መንገዱ ከተሰራ ወደፊት ጥሩ ዋጋ ያወጣል፡፡ ይህም ገበሬው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ይጨምራል፡፡ እስካሁን ግን ገበሬው ቡናውን በጣም በአነሰ ዋጋ ነበር የሚሸጠው፤ በዚህም የገበሬው ትርፍ ድካም ብቻ ነበር፡፡ አሁን ግን መንገዱ ተሰርቶ ሲጠናቀቅ ቡናችንን ቀጥታ ጭኖ ወደ ማዕከላዊ ገበያ ይቀርባል፤ በመሆኑም በአካባቢው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ የጎላ ድርሻ ይኖረዋል የሚል ሃሳብ አላቸው፡፡
የኤዶ-ሰሮፍታ-ዋርቃ መንገድ በጠጠር መንገድ ደረጃ ያለ ሲሆን፤ ካለው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ አንጻር ታይቶ በአስፋልት ደረጃ ለመገንባት በብር አንድ ቢሊዮን 687 ሚሊዮን 343ሺ 877ብር ጨረታውን ካሸነፈው ዓለማየሁ ከተማ ኮንስትራክሽን ጋር ታህሳስ 4 ቀን 2011 ዓ.ም የኮንትራት ስምምነቱ ተፈርሟል፡፡ ለመንገዱ ግንባታ የሚውለው ወጪም ሙሉ በሙሉ የሚሸፈነው በኢትዮጵያ መንግስት መሆኑም ታውቋል፡፡ ግንባታው የድልድይ ሥራዎች፣ የአነስተኛ የውሃ ማፋሰሻ ቱቦዎችና ሌሎች ሥራዎችንም ያካትታል፡፡ የመንገዱ ስፋት በከተማ የመንገድ ትከሻን ጨምሮ ከ12 እስከ 19 ሜትር ሲሆን በገጠር ደግሞ ከስምንት እስከ አስር ሜትር ነው፡፡
በአጠቃላይ የመንገዱ ግንባታ ሲጠናቀቅ በአካባቢው የነበረውን የትራንስፖርት ችግር ይቀርፋል፡፡ይህም የአካባቢው ህብረተሰብ በቀላሉ ከሌሎች አካባቢዎች ጋር እንዲገናኝ ከማስቻሉ ባሻገር፤ ባለሃብቶች ምርታቸውን በቀላሉ ወደ ገበያ ማውጣት ያስችላል፤ አዳዲስ ባለሀብቶችም በአካባቢው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ተነሳሽነትን ይፈጥራል፡፡በተጨማሪም በአካባቢው የሚገኙ ትንንሽ መንደሮች በከተማ ደረጃ እንዲስፋፉና እንዲያድጉ ያደርጋል፤ ከዚህም በላይ የጤና፣ የትምህርት እና ሌሎች የማህበራዊ ተቋማት አገልግሎት እንዲስፋፉ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይታወቃል፡፡
የመንገድ ግንባታውን ሥራ ለማስጀመር የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡ ሲሆን፤ የፌዴራል፣ የኦሮሚያ ክልል እና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የዞኑ መስተዳድር አካላትም በሥነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 1/2011
ፍሬህይወት አወቀ