አዲስ አበባ፡- በቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ የወጣቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚመለከታቸው አካላት በተለይ ፖለቲከኞች የድርሻቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ኮንሰርቲየም ኦፍ ዩዝ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን ኢን ኢትዮጵያ የተሰኘው የሲቪክ ማህበር አሳሳበ፡፡
ማህበሩ ትናንት በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል ለጋዜጠኞች በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ደሳለኝ እንደገለፁት ፤ መንግስት በኃላፊነት ስሜትና ተጠያቂነት ባለው አሰራር የወጣቶችን ተሳትፎ ከዝግጅት አድማቂነትና ከችግር ተጋላጭነት ትርጉም ወዳለው ተሳትፎና እውነተኛ ውክልና ከፍ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
በቀጣዩ ምርጫም የወጣቶችን መብትና ግዴታዎችን የማስተማር፣ ከማህበራዊ ብዝበዛ የመታደግና በአገራቸው ላይ ተስፋ እንዳይቆርጡ የወጣቶችን ፖሊሲና ተቋማዊ ማሻሻያዎችን አሳታፊ በሆነ መንገድ ተቆጥሮ የሚመዘን የስራ አድል ፈጠራን ማመቻቸት እንደሚገባው ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከላይ እስከታች ባላቸው መዋቅር ለወጣቶች ተገቢውን ውክልና መስጠት እንዳለባቸውም የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ ፤ ፓርቲዎቹ አሸነፉም ተሸነፉም ባልተገባ መንገድ መቀስቀስና ማደራጀት የወጣቱን ሕይወት አደጋ ላይ እንደሚጥልና ተጠያቂነት እንዳለባቸው ተገንዝበው በጥንቃቄና ዘላቂ ሰላምን ታሳቢ ባደረገ ስልት ሊንቀሳቀሱ እንደሚገቡ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
በተመሳሳይም የምርጫ ቦርድ ወጣቶች በአግባቡ እንዲሳተፉ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ግዜና በድህረ ምርጫ በሰለጠነና ህጋዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ በሰፊው ከማስገንዘብ በተጨማሪ በተለይ ወጣቶችን ማሳተፊያ ስልቶችን ቀይሶና በቂ ሃብት መድቦላቸው አስከፊ ክስተቶችን መቀነስ እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡
መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የወጣት አደረጃጀቶችም ገለልተኛ በመሆንና ግልፅና ተጠያቂ አሰራሮችን በመከተል የወጣቶች ዜግነታዊ ተሳትፎ እንዲያድግና ትኩረት የሚሹ አካል ጉዳተኛ ወጣቶችንና ሴቶችን የማካተት ሂደቶችን ለማሳደግ ተቀናጅተው መስራት እንደሚገባቸውም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፤ ለዚህም ልዩ ልዩ የውይይት መድረኮችን በመላ ሃገሪቱ ለሚገኙ ተፅእኖ ፈጣሪ ወጣቶች ማዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አያይዘውም ወጣቶች በማንበብ፣ በመጠየቅ፣ በመወያየትና በሰላማዊ መንገድ ልዩነቶችን ለማስተናገድ በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ በንቃት በመሳተፍ እንዲሁም የማህበራዊ ትስስር መገናኛ ብዙሃንን በሰብአዊነት በመገልገል በዘንድሮውና በቀጣይ በሚደረገው ምርጫ መካከል ሚዛናዊ ንፅፅሮችን ማስተዋል እንደሚጠበቅባቸውም ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
ሁሉም የሀገሪቱ ሚዲያዎች የወጣቶችን ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት እርስበርስ ከሚያጋጩና የወጣቱን ህይወት ከሚጎዱ ዘገባዎች ይልቅ አርቆ አሳቢነትን፣ የሀገር ፍቅርን፣ መተባበርንና ሚዛናዊ አተያይን ማስፋት ላይ በማተኮር ወጣቶች በራሳቸው ጉዳይ ላይ ራሳቸው መወሰን እንዲችሉ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡
ማህበሩ ባለፉት ስድስት ወራት በሰባት ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች በወጣቶች የቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ ተሳትፎ ዙሪያ ጥልቀት ያለው ጥናትና የተለያዩ ውይይቶችን ሲያካሄድ ቆይቷል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 29/2012
አስናቀ ፀጋዬ