በኢትዮጵያ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ እየተካሄደ ያለው ለውጥ እንዲመጣ በርካታ ወጣቶች መስዋዕትነት ከፍለዋል። በወጣቶች ግንባር ቀደም ተዋናይነት የተደረገው ትግል ገዥው ፓርቲ ለጥልቅ ተሃድሶ እንዲቀመጥና የአመራር ለውጥ እንዲያደርግ አስገድዶትም ነበር። ከጥልቅ ተሃዲሶ በኋላ የአመራርነት መንበር የተቆናጠጡት አመራሮች የወሰዷቸው ቁርጠኛ እርምጃዎች የኢትዮጵያ ስም በዓለም ደረጃ ከፍ ብሎ እንዲጠራ አድርገዋል።
ይሁን እንጂ ለውጡ እንከን አልባ አይደለም። ብዙ ውጣ ውረዶችም የበዙበት ነው። ኢትዮጵያዊያንንና ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን ያሳዘኑ ክስተቶችም ተስተናግደዋል። በአንዳንድ አጋጣሚዎች ወጣቱ በመስዋዕትነት ያመጣውን የራሱን ለውጥ አደጋ ላይ የሚጥል ብሎም የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት የሚፈታተኑ ተግባራት ላይ ሲሳተፍ ተስተውሏል። በሀገሪቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጸሙት እኩይ ተግባራት ወጣቶች ተሳታፊ ሆነው መታየታቸው ሁኔታውን አሳሳቢ አድርጎታል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰላምና ጸጥታ ጥናት ኢንስቲትዩት ሁለተኛ ዲግሪዋን እየሰራች የምትገኘው ወጣት ሶፊያ አማን እንደምትገልፀው፤ ለውጡ ያመጣቸውን መልካም ውጤቶች ቆም ብሎ አለማሰብ ይታያል። ለውጡ በወጣቶች የስሜታዊ ውሳኔዎች ችግር ውስጥ እንዲገባ ምክንያት ሲሆን ይስተዋላል። በአንዳንድ አካባቢዎች ወጣቱ በለውጡ ያገኛቸውን ወርቃማ እድሎችን በአግባቡ ከመጠቀም ይልቅ ለውጡንም ሀገሪቱንም አደጋ ላይ በሚጥሉ ተግባራት ላይ ሲሳተፍ ይታያል።
እንደ ሶፊያ ማብራሪያ ወጣቱ የመስዋዕትነቱ ውጤት የሆነውን ለውጥ እንደራሱ ሊንከባከበው ይገባል። የወጣቶች እያንዳንዱ እርምጃ ስክነት የተሞላበት ሊሆን ይገባል ስትል መክራለች። ዛሬ ላይ ካለው ጥሩ ነገሩን እያጣጣመ፤ መጥፎ ነገሮች እንዲታረሙ በሰከነ መንገድ በመታገል ነው። በለውጡ የተገኙ ፍሬዎች እንዲጎመሩ የበኩሉን በመወጣት ለውጡን እንዴት ማስቀጠል እንዳለበት ማሰብ አለበት እንጂ የታየውን የለውጥ ጅማሮዎች ሊቀለብሱ በሚችሉ ተግባራት ላይ ሊሳተፍ አይገባም።
ለውጡን ማስቀጠል ካልተቻለ ሀገሪቱንም ወደ ፊት ለማስቀጠልም ሆነ የወጣቶችን ፍላጎት ለማሳካት አዳጋች ነው። ስለዚህ ወጣቱ ለራሱ ቡድን ብቻ ከመቆርቆር ወጥቶ ሀገራዊ ችግሮች የሚፈቱበትን፤ ሀገራዊ ችግሮች ሲፈቱ ደግሞ የሁሉም ቡድኖች ችግሮች እንደሚፈቱ በማሰብ ሀገራዊ ለውጡ ወደታሰበበት ደረጃ እንዲደርስ ሊረባረብ ይገባል። ለዚህም ከቡድን ሰውነትን ማስቀደም አስፈላጊ ነው።
‹‹የወጣቱ አንድን ቡድን ወይም ግለሰብ በጭፍን መከተል ሀገሪቱንም ሆነ ለውጡን አደጋ ውስጥ የመክተት አደጋ አለው›› የምትለው ሶፊያ፤ ወጣቱ ግለሰብን ወይም ቡድንን በጭፍን ከመከተል ይልቅ እያንዳንዱን ነገር በራሱ መንገድ መመርመር መተንተን መጀመር አለበት ስትልም ትመክራለች።
በወጣቶች ጫና በኢትዮጵያ ውስጥ የመጣው ለውጥ በአፍሪካ ምድር ያልተለመደ አይነት ነው የሚለው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ጸጥታ ኢንስትቲዩት የሁለተኛ ዲግሪ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ እና የምስራቅ አፍሪካ ተማሪዎችና ወጣቶች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አብርሃም አበበ፤ በአፍሪካ ምድር እጅግ ሰላማዊ የሚባል የስልጣን ሽግግር የተካሄደበት ነው። ይህ ደግሞ ለዚህ ለውጥ ዋጋ ለከፈለው ወጣት ትልቅ ስኬት ነው።
ለውጡ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በዓለም እንዲጎላ ያደረገ ከመሆኑም ባሻገር በርካታ ውጤቶችንም አስገኝቷል። ሆኖም ለለውጡ አደጋ የሆኑ ክስተቶችም ተበራክተዋል። ለለውጡ ከባድ አደጋ ከሆኑት መካከል ህግ በማስከበር ረገድ የሚስተዋለው ከፍተኛ ክፍተት ነው። ያለውን ክፍተት ያወቁ አካላት በየአካባቢው ወጣቶችን በስሜት በመገፋፋት ንብረት የማውደም፣ የሀይማኖት ተቋማት ላይ ጥቃት መሰንዘር፣ ብሄርን ማዕከል ያደረጉ ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ሲያደርጉ ታይተዋል።
በየአካባቢው ሲታዩ የነበሩት የንብረት መውደም፣ የሰው መፈናቀል፣ የአካል መጉደል ወጣቱ ለዲሞክራሲ፣ ለነጻነት፣ ለእኩልነትና ለፍትህ ያደረገው ትግል መና እንዲሆን የሚያደርግ ነው። ወጣቱ ይህን ሊገነዘብ እንደሚገባ አብርሃም አብራርቷል።
እንደ አብርሃም ማብራሪያ፤ አንዳንድ ወጣቶች በስሜት ተገፋፍተው ለውጡን በሚጎዱ እኩይ ተግባራት ሊሳተፉ ቢችሉም በዋናነት የሀሳቡ ጠንሳሽ አካላት ሌሎች ናቸው። የእነዚህ አካላት ዋና ዓላማ ለውጡን መቀልበስ ነው። ወጣቱ እንዲህ አይነት ወጣቶችን ስም ከማጠልሸት አልፎ ለውጡን የሚጎዳ ነገርን በግልጽ ሊታገል ይገባል። መሰል ተግባራት ላይ የሚሳተፉ አካላት ከወጣቶች አይን ሊሰወሩ አይችሉም።
እንደ አብርሃም ማብራሪያ ባለፉት ትውልዶች የነበሩት ወጣቶች ያካሄዱት ትግሎች የስርዓት ለውጥ ማምጣት ቢችሉም ኢትዮጵያን ወደሚፈለገው ዲሞክራሲ፣ ፍትህና እኩልነት አላሸጋገራትም። አንድን ገዥ መደብ አስወግዶ ሌላ ገዥ መደብ ነበር ሲጭንብን የነበረው። በዚህ ትውልድ ግንባር ቀደም ተዋናይነት የመጣው ለውጥም ያለፉት ለውጦች ያጋጠማቸው እድል እንዳያጋጥም፤ ኢትዮጵያ ወደ ዲሞክራሲ፣ እኩልነትና ልማት እንዲያሸጋግራት ወጣቱ በጥንቃቄ ሊንቀሳቀስ ይገባል።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት በ2011 ዓ.ም ተመርቆ ስራ በማፈላለግ ላይ የሚገኘው ሳሙኤል ተስፋዬ በበኩሉ ለውጡ በማዕከል ደረጃ ከፍተኛ ውጤቶች እያስመዘገበ ቢሆንም በታችኛው መዋቅር ላይ ከፍተኛ ችግር አለ። በታችኛው እርከን ላይ ያሉት አመራሮች ሆን ብለው ስልጣናቸውን ለማራዘም ለውጡ አቅጣጫውን እንዲስት ሲያደርጉ ይታያል። ይህ ደግሞ ወጣቱ ለለውጡ የሚጠበቅበትን እንዳይወጣ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
በመሆኑም ወጣቱ ለለውጡ የሚያስፈልገውን አስተዋጽኦ እንዲወጣ መንግስት የታችኛውን የመንግስት መዋቅር ሊፈትሽ ይገባል። ለውጡ አቅጣጫውን እንዳይስት ማድረግ ግን የለውጡ መሪዎች ስራ ብቻም ሳይሆን የወጣቱ ጭምር ነው። ለውጡን የወጣቱ እንደመሆኑ መጠን ለውጡን ሆን ብለው አቅጣጫ የሚያስቱ አካላት ላይ ጫና በማሳደር የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብሏል። አሁን ባለው ሁኔታ ወጣቶች የሚፈልጉትን ያህል ተጠቃሚ ላይሆኑ ይችላሉ። ስራ አጥነት ከባድ ችግር እንደሆነ ይታወቃል። ስራ ቢገኝም ባይገኝም ግን ኢትዮጵያ ሀገራቸው ነች። ለኢትዮጵያ ዘብ መቆም ከወጣቶች ሁሌም ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ጥር 28/2012
መላኩ ኤሮሴ