አዲስ አበባ፡- በታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚካሄደው ድርድር ኢትዮጵያ ታዛቢን ፈርታ አሳልፋ የምትሰጠው ብሔራዊ ጥቅም እንደሌለ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ረዳት ፕሮፌሰር እና የዩኒቨርሲቲው የውጭ ግንኙነት ትብብር እና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ደመቀ አጭሶ ገለፁ።
ዶክተር ደመቀ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፤ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል በቅርቡ በተደረጉት ድርድሮች ላይ የዓለም ባንክና አሜሪካ በታዛቢነት በመሳተፋቸው ኢትዮጵያ አሳልፋ የምትሰጠው ጥቅም የለም።
‘’ታዛቢ ማለት ሦስቱ ሀገራት እንዴት እየተደራደሩ እንደሆነ የሚታዘብ አካል ማለት እንጂ የሚጫን ማለት አይደለም’’ ያሉት ዶክተር ደመቀ ታዛቢዎች ሚና ገለልተኛ ሆነው ድርድሩ ዲፕሎማሲያዊ መርህን በተከተለ መልኩ እየሄደ ነው ወይ የሚለውን መታዘብ እንጂ ተደራዳሪዎችን ‹ይህን ተቀበል ያንን ተቀበል› እያሉ ጫና ማሳደር አለመሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በዓባይ ወንዝ ላይ ግድቦችን ለመገንባት ድጋፍ ስትጠይቅ የዓለም ባንክ ድጋፍ መከልከሉን እንደ ምክንያት በመጥቀስ ዛሬ የዓለም ባንክ በታዛቢነት መግባት የለበትም የሚለው ትናንት የበደለን አካል ዛሬም ይበድለናል ከሚል አስተሳሰብ የሚመነጭ መሆኑን ዶክተር ደመቀ አብራርተዋል። ይህ አይነት አመለካከት ግን ለዲፕሎማሲ ጠቃሚ አይደለም ብለዋል።
ግብጽ ባላት የጂኦ ፖለቲካ ከኢትዮጵያ በተሻለ መልኩ ለአሜሪካ ጠቃሚ ልትሆን ትችላለች፤ የአሜሪካ መንግ ሥት ለግብጽ የሚያደርገው ድጋፍ ለኢትዮጵያ ከሚያደርገው ሊበልጥ ቢችልም የአሜሪካ መንግሥት የግብጽ ብቻ ወዳጅ አይደለም። አሜሪካ የኢትዮጵያም የረጅም ጊዜ ወዳጅ መሆኗን አስታውሰዋል።
እንደ ዶክተር ደመቀ ማብራሪያ፤ ታዛቢዎቹ መሳተፋቸው በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድረው ጫና ይኑር አይኑር ሳይታወቅ በጥርጣሬ የኢትዮጵያ ወዳጆችና የልማት አጋሮች በድርድር እንዳይሳተፉ ማገድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ለአብነት ያህል የአሜሪካ መንግሥት በታዛቢነት እንዳይሳተፍ ብሎ መከልከል ግብጽን ደግፍ ብሎ እንደመፍቀድ ነው።
በዲፕሎማሲ መድረክ ሁሉንም ነገር በጥርጣሬ ዓይን መመልከት እና ሁሉንም ነገር ቀድሞ መደምደም ተገቢ አይደለም ያሉት ዶክተር ደመቀ፤ ለዲፕሎማሲ መተማመንና ጥሩ መንፈስ ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል። የአሜሪካ መንግሥትና የዓለም ባንክ በታዛቢነት ለምን ተሳተፉ በሚል የሚቀርበው ትችትም ተገቢነት የጎደለው መሆኑን ያብራሩት ዶክተር ደመቀ፤ የዓለም ባንክና አሜሪካ መንግሥት እንደታዛቢ መግባታቸው ለኢትዮጵያ እንደ ሽንፈት የሚታይ አይደለም።
እንደ ዶክተር ደመቀ ገለጻ፤ ታዛቢዎች እንዲሳተፉ መፍቀድ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ እንደመስጠት አድርጎ ማሰብም ተገቢነት የጎደለው ነው። የኢትዮጵያ ጥቅም የሚከበረው በኢትዮጵያዊያን ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት የሚቸግረው ነገር ካለ መርዳት እንጂ፤ ብሄራዊ ጥቅማችንን አሳልፎ ሰጠ እያሉ እንደባዳ፤ ወይም እንደ ቅኝ ገዥ መንግሥትን መውቀስ ተገቢ አይነት አመለካከት አይደለም ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 28/2012
መላኩ ኤሮሴ