በፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን የ2012 ዓ.ም የመጀመሪያው ዙር አገር አቀፍ የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ኤግዚብሽንና ባዛር ላይ 176 ተሳታፊዎች ተገኝተዋል። ከእነዚህ መካከል ከተግባረዕድ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት ሁለት ማሽኖችን ይዞ የቀረበው መምህር ታረቀኝ ዘለቀ ይገኝበታል።
ታረቀኝ፤ በተግባረዕድ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት የቴክኖሎጂ ሽግግር ኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን መምህር ነው። በኤግዚቢሽኑ ይዞ የመጣው ሁለት ማሽኖችን ሲሆን፤ አንደኛው ማሽን ጥሬ የሆኑ ነገሮችን መከካት የሚችል እና ሁለተኛው ደግሞ በርበሬና ሽንኩርት መፍጨት የሚችል ማሽን ነው። በተማሪዎች እና በመምህራን የተሰሩት እነዚህ ማሽኖች በተግባር ተሞክረው ውጤታማ እንደሆኑ ይናገራል።
ማሽኖቹ የተሰሩት ለቴክኖሎጂ ዕድገት በመሆኑ መምህሩ ፕሮጀክቱን ቀርፆ ከተማሪዎች ጋር በመተጋገዝ የተሰሩት እነዚህ ማሽኖች ችግር ፈቺና ሥራን ማቀላጠፍ የሚችሉ መሆናቸው ተገልጿል። እንደ ተግባረዕድ ትምህርት ቤት በርካታ ተማሪዎች በማኑፋክቸሪንግ፣ በአውቶ እና በማሽኒንግ ሙያ ተሰማርተው ስልጠና የሚወስዱ ሲሆን፤ ስልጠናው በአብዛኛው በተግባር የሚሰራ በመሆኑ ተማሪዎች እጅግ በላቀ ፍላጎትና በደስታ እየተማሩ በመሆኑ በዘርፉ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ መምህሩ ያብራራሉ።
የቴክኖሎጂ ሽግግርን በተመለከተም በየጊዜው እየተሻሻለ የሚመጣ ሲሆን፤ በተያዘው በጀት ዓመት ለተግባረዕድ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት የተሰጠው 50 ቴክኖሎጂን ማሸጋገር ነው። ይህን 50 ቴክኖሎጂ ለማሸጋገርም እንደ ተቋም በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም መምህር ታረቀኝ ይገልፃል። በዚህም እያንዳንዱ ተማሪም ሆነ መምህር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ይሰራል ፤ከእነዚህም ውስጥ ተለይተው አዋጭና የሚሸጋገሩ መሆናቸው ሲረጋገጥ ለኢንተርፕራይዞች እንደሚቀርብ መምህሩ ተናግረዋል።
ሌላኛው ባለሙያ በፋውንደሪ ቴክኖሎጂ አሰልጣኝ ወጣት አበበ በላይ ነው። ወጣቱ በፌዴራል የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን የሚሰሩ የተለያዩ ምርቶችን በመስራት ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ለቴክኒክና ሙያ አሰልጣኞችም ጭምር አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ የተለያዩ ስልጠናዎችን ይሰጣል። ኢንተርፕራይዞቹ ከውጭ መግዛት የማይችሉትን ነገሮች በባለስልጣኑ እየተመረተ እንደሚቀርብ ወጣት አበበ ጠቁሟል።
ከዚህም ባለፈ ቴክኒካል በሆኑ ነገሮች ሁሉ ስልጠና እንደሚሰጡ የሚናገረው አሰልጣኙ፤ ተደራጅተውም ሆነ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የሚመጡ ተማሪዎች ባለስልጣኑ ያስቀመጠውን መስፈርት ካሟሉ፤ በእንጨት ሥራ፣ በብረታብረት፣ በቀርከሃ፣ በጌጣጌጥ፣ በፕላስቲክ ጠርሙሶች፣ በሻማ እንዲሁም ቾክና ሶፍትን ጨምሮ በፈለጉት ሙያ ላይ በመሰማራት ስልጠናውን ማግኘት ይችላሉ። ሰልጥነው የወጡትን ባለሙያዎችም ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙና ያጋጠማቸው ችግር ካለም እገዛ ለማድረግ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማስፋፊያ ባለሥልጣን የኮሙኒኬ ሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ መለሰ፤ ዘርፉ በርካታ ጥቅሞች ያሉትና ዘላቂ የሆነ የገበያ ትስስር መፍጠር የሚችሉበት መሆኑን በመግለፅ፤ ኢግዚብሽኑ አከፋፋዮች እና ሸማች ማህበረሰብ የሚገናኙበት እንዲሁም ከማኑፋክቸሪንግ ምርትና ምርታማነት ጋር የተያያዘ እርስ በርስ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ ዕድል እንደሚፈጥር አብራርተዋል።
ከሁሉም ክልሎች ተውጣጥተው በባዛርና ኤግዚቢሽኑ ላይ የተሳተፉት በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ የሚገኙ፣ አምራቾች እና ሌሎችም ተሞክሮ ማካፈል የሚችሉ እንደሆኑ ዳይሬክተሩ ገልፀዋል። በባዛርና ኢግዚቢሽኑ የተገናኙ የተለያዩ ተቋማት በቀጣይ በጋራ መስራት እንዲችሉ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ባለፈ በአገር አቀፍ ደረጃ ዘርፉ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መረዳት ያስችላልም ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 28/2012
ፍሬህይወት አወቀ