አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ጥቅሞቿን ለማስከበር የሚያስችል ድርድር ማካሄዷን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ተናገሩ። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚናፈሱ መረጃዎችን በመውሰድ የኢትዮጵያ አቋም እንደተሸረሸረ ተደርጎ የሚገለፀው የማወናበጃ ሀሳቦች ተገቢ እንዳልሆኑም አስታውቀዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብፅ በቅርቡ ያካሄዱትን ድርድሮች አስመልክቶ ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ አገራቱ በአሜሪካና በዓለም ባንክ ታዛቢነት በአራት ጉዳዮች ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው። የግድቡን ቴክኒካዊ ጉዳዮች፣ የህግ ጉዳይ፣ የሚፈጠሩ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበት ሁኔታ እንዲሁም የመረጃ ልውውጥ የውይይቱ ማጠንጠኛ ጉዳዮች ናቸው።
ከእነዚህ ውስጥ በተለይም የግድቡን ቴክኒካዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የተደረገው ድርድር ላይ ከስምምነት የተደረሰ ሲሆን፤ የነበሩ አንዳንድ ልዩነቶ ችንም በድርድር መፍታት መቻሉን ተናግረዋል። ሦስቱ ሀገራት ያቋቋሙት የህግ ቡድን በጋራ በመሆን የህግ ሰነድ እያዘጋጀ ሲሆን የሰነዱ ዝግጅት እንደተጠናቀቀ ተገቢው ምርመራ ተደርጎበት እንደሚፈራረሙ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የሰነዱ ዝግጅት እስከ ቀጣይ ሳምንት ያልቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
የህግ ሰነዱ ላይ መጠነኛ ልዩነቶች የሚኖሩ ከሆነም በሚኒስትሮች ደረጃ ውይይት ተደርጎበት እንደሚፈታ አብራርተዋል። እንደ ዶክተር እንጂነር ስለሺ ማብራሪያ፤ በተካሄዱት ድርድሮች ሁሉንም ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስምምነቶች ላይ መድረሳቸውን የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ ስምምነት ባልተደረሰባቸው በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ጊዜ ወስዶ በመወያየት ከመግባባት ተደርሷል።
ስምምነት በተደረሰባቸው ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ሀገራቱ እንዲፈራረሙ ፍላጎቶች የነበሩ ሲሆን ኢትዮጵያ በበኩሏ አራቱንም ጉዳዮች በአንድ ላይ መፈራረም እንደሚሻል ሀሳብ በማቅረብ የፊርማ ስነ ስርዓቱ ለሌላ ጊዜ እንዲሆን ሀሳብ በማቅረብ ለቀጣይ ጊዜ እንዲራዘም መደረጉን አብራርተዋል፡፡ የተቀሩት ሶስቱ ጉዳዮች ላይ በቀጣይ በመወያየት አራቱንም ጉዳዮች በጋራ የሚያካትት ሰነድ እንደሚፈራረሙ ተናግረዋል፡፡
በድርድሮቹ ላይ ኢትዮጵያ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ ተጠቃሚነት መርህን ስታራምድ እንደነበርም አንስተዋል ብለዋል። በቅርቡ የተደረጉት ድርድሮች በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ቴክኒካል፣ የህግ፣ ልዩነቶች የሚፈቱበትና የመረጃ ልውውጥን የሚመለከት እንጂ የናይል ወንዝን እንደማያካትት ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በድርድሩ ዙሪያ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚናፈሱ መረጃዎችን በመውሰድ የኢትዮጵያ አቋም እንደተሸረሸረ ተደርጎ የማወናበድ ስራዎች ተገቢ እንዳልሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በዚህ ወቅት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት ሊቆም እንደሚገባም አብራርተዋል። በዚህ ወቅት ያልተፈጠሩ ነገሮችን በማንሳት ህዝብን ማወናበድ ለኢትዮጵያ የሚፈይዳት ነገር የለም ያሉት ሚኒስትሩ፤ ግድቡ ተጠናቆ ኢትዮጵያ ከግድቡ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ ሁሉም በጋራ ሊረባረብ ይገባል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 28/2012
መላኩ ኤሮሴ