አዲስ አበባ፡- ለ33ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በቂ የጸጥታ ጥበቃ ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ስለ ጸጥታው ዝግጅት ትናንት በጋራ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤አገር አቀፍ የጸጥታ ጥምር ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ከጥር 28 ዓ.ም እስከ የካቲት ሁለት 2012 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ለሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ በቂ የጸጥታ ጥበቃ ለማድረግ ዝግጅቱ ተጠናቆ ወደ ስራ ተገብቷል።
የ33ኛውን የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በቂ የጸጥታ ጥበቃ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ ዝግጅት መጠናቀቁን የገለጹት የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል አቶ መላኩ ፈንታ፤ ጉባኤው የአገሪቱን መልካም ገጸታ በማስተዋወቅ ያለውን ጉልህ ሚና በመገንዘብ ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን ህብረተሰቡ ባለቤትነት በመሆን የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ በበኩላቸው ፤ የጸጥታ ግብረ ሀይሉ ጉባኤው ላይ ችግር ለመፍጠር ቢፈለግ እንኳን መከላከል የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። በተያያዘም እንግዶች የሚያርፉባቸው 137 ሆቴሎች ተለይተው በቴክኖሎጂ የታገዘ የጥበቃና የአስተዳደር ሥራ እንዲሰሩ ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።
33ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ከየካቲት 1 እና 2 ፤2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን በጉባኤው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሀፊን ጨምሮ ከ45 በላይ የሕብረቱ አባል ሀገራት መሪዎች እና ከ13 በላይ የሕብረቱ አባል ያልሆኑ ሀገራት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ጥር 28/2012
ጌትነት ምህረቴ
ፎቶ፡- ከፌደራል ፖሊስ