ነጌሌ ቦረና፡- ‹‹ትኩረታችን ለጨረስነው መፎከር ሳይሆን ለምንጀምረው መታጠቅና መዘጋጀት›› ያስፈልጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት የገናሌ ዳዋ ሦስት የውሃ ሃይል ማመንጫ ግድብን በመረቁበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ትኩረታችን በጨረስነው ነገር ላይ መፎከር ሳይሆን ለምንጀምረው ነገር መታጠቅ ፣መዘጋጀት፣ ሀብት ማሰባሰብ እና ካለፈው ልምድ በመውሰድ ሥራን በአጭር ጊዜ መፈጸም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም የነጌሌ ዳዋ ስድስት ሃይል ማመንጫ ግድብን የመጀመር ዕቅድ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡
የውጭ ባለ ሀብቶች ፕሮጀክቱን ለመገንባት ብዙ ጥያቄ እንደሚያቀርቡ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ፍላጉት ያላቸው የሀገር ወስጥ ባለሀብቶች በግንባታ የመሰማራትፍላጎት ቢያሳዩ ከመንግሥት ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ተናግረዋል፡፡ ባለሀብቶች ይህ ዕድል እንዳያመልጣቸውም ምክር ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሚያሥፈልጋት ሥራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የገናሌ ወንዝን ወደ ልማት በማስገባት አካባቢውን በመስኖ፣ በሃይል ማመንጨትና በዓሳ ምርት ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል። የጉጂ ህዝብ ሲበላም ሲጠጣም ሲመርቅም በዳዲና(በልጽጉ) ማለቱ የድህነትን መጥፎነት ከመረዳት የመነጨ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በተረጋጋ መንፈስ ወደ ልማት በመግባት ሀገር እንዲቀየር ፣ወንድማማችነት እንዲጠነክር፣ አንድ ሆነን ለሌሎች የምንተርፍ እንድንሆን፣ በባዕድ ሀገር ተሰደው የሰው ሰራተኛ የሆኑ ወገኖቻችን በሀገራቸው ሰርተው እንዲለወጡ ተባብረን ወደ ሥራ መግባት እንደሚገባ መክረዋል።
የፕሮጀክቱን የሲቪልና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎችን ያከናወነውን የቻይናውን ሲጂጂሲ ኩባንያና በማማከር ሥራ ላይ ለተሰማሩት ኩባንያዎች በሙሉ ምስጋና በማቅረብ ይህ የድል ዜና በቅርብ ጊዜያት በሌሎች ሥራዎችም እንደሚቀጥል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ዶክተር ስለሺ በቀለ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢኮኖሚያችን በፍጥነት እያደገ በመጣ ቁጥር የሃይል ዘርፍ እድገት ፍላጎትም በዚያው ልክ እንደሚጨምር ገልጸዋል። የሃይል አቅርቦት ፍላጎት በዓመት ከ19 በመቶ በላይ ሲሆን የሚቀርበው የኤሌክትሪክ አቅርቦት ግን ከ8 በመቶ አለማለፉን ጠቅሰው፤የፋይናንስ እጥረት፣ የመሰረተ ልማት አለመሟላት፣ እና የአጠቃቀም ችግር ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።
የሀገራችን ተፋሰሶችና መልክዓ ምድሮች ከውሃ የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት ምቹ ቢሆኑም ያለንን እምቅ አቅም ሀብት በአግባቡ መጠቀም ሳንችል በርካታ ዓመታትን ማሳለፋችን የሚያሥቆጭ እንደሆነ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። የህብረተሰቡን የሃይል ፍላጎት ለማሟላት በቀጣይ ጊዜያት በተለያዩ ተፋሰሶች ላይ የአዋጭነት ጥናት ለማካሄድ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ትናንት የተመረቀው የገናሌ ዳዋ ሦስት ሃይል ማመንጫ የውሃ ሃይል ማመንጫ ግድቦችን ቁጥር ወደ 15 ያሳደገ ሲሆን፤ በዓመት ሁለት ጊዜ የክረምት ጸጋ ያለው መሆኑ ከሌሎች ይለየዋል ብለዋል። ግድቡ 110 ሜትር ቁመትና 426 ሜትር ርዝመት ያለው ነው። 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም ያለው ይህ ግድብ እያንዳንዳቸው 84 ነጥብ 7 ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚችሉ ሦስት ተርባይነሮች / መዘውሮች/ አሉት።
ግድቡ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ በየዓመቱ 254 ሜጋ ዋት ሃይል ያመነጫል። ዓመታዊ የሃይል ምርት አቅሙም በአማካይ በሰዓት አንድ ሺ 640 ጌጋ ዋት ነው። ግድቡ 12 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የውሃ ማስገቢያ ዋሻ እና 380 ሜትር ርዝመት ያለው የውሃ መልቀቂያ ዋሻ የተሰራለት ነው። በአጠቃላይ ግንባታው 451 ሚሊየን ዶላር የወጣበት ሲሆን ፤ከዚህም ውስጥ 60 በመቶ ከቻይና ኤክዚም ባንክ በብድር የተገኘ ቀሪው 40 በመቶ ደግሞ በኢትዮጵያ መንግሥት የተሸፈነ ነው።
ሲጂጂሲ የተሰኘው የቻይና ኩባንያ የሲቪልና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎችን ሲሰራ የአሜሪካው ኤም.ደብሊው.ኤች ኩባንያ ከኢትዮጵያዊያኑ አኩሬትና ኢንተግሬትድ ኩባንያዎች ጋር በመጣመር የማማከሩን ሥራ ሰርተዋል። የገናሌ ዳዋ ሦስት የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ግንባታ የተጀመረው በ2003 ዓ.ም እንደሆነ ይታወሳል። ግድቡ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በጉጂና ባሌ ዞኖች መዋሰኛ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከአዲስ አበባ በስተደቡብ 630 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ጥር 27/2012
ኢያሱ መሰለ