አዲስ አበባ፡- ‹‹የቀጣዩን ዘመን ትውልድ አመራርና ሙያተኛን መፍጠር ወሳኝ ነው›› ሲሉ የቀድሞው የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ ገለፁ፡፡የአመራር ትውልድ ለመፍጠር የበኩላቸውን ጥረት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡
አቶ አባዱላ ገመዳ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ በስልጣን ዘመናቸው ከሰሯቸው ስራዎች መካከል ደስ ከሚሰኙባቸው አንዱ ኦሮሚያ ውስጥ ወጣቶች የስርዓቱ ባለቤት እንዲሆኑ ከፍተኛውን አስተዋፅኦ አድርገዋል። የዩኒቨሲቲ ተማሪዎች በስፋት ወደ ስርዓቱ እንዲገቡና አዳዲስ መሪዎች እንዲሆኑም ጥረዋል።
እርሳቸው እንደገለፁት፤ አንድ ሰው ሁሌም ጠንካራ ሆኖ መቀጠል አይችልም። ምክንያቱም የእድሜ፣ የእውቀት፣እንዲሁም የቴክኖሎጂና መሰል ነገሮች አሉና አንድ ቦታ ላይ ‹እኔ ካልኖርኩ› የሚል አስተሳሰብ አይሰራም። ስለዚህ አገርን ሊመራ የሚችል ቀጣዩን ትውልድ በአመራር ደረጃ ሆነ ሙያውን በማብቃቱ በኩል ከወዲሁ መስራት አስፈላጊ ነው።
‹‹አንድ አመራር ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል በዓይን የሚታይና በእጅ የሚዳሰስ እንደ መንገድ፣ መስኖ አሊያም ትምህርት ቤት ሊጠቀስ ይችላል፤ እነዚህ የልማት ሥራዎች የመጀመሪያዎቹ ሲሆኑ፣ ሁለተኛውና ዋነኛው ደግሞ ሰውን መስራት ነው›› ያሉት አቶ አባዱላ፣ ‹‹ አመራር
ሁለቱን ሥራዎች ካላከናወነ በጣም ብዙ ህንፃዎችን ቢሰራ ሊያስቀጥል የሚችል ኃይል አይኖርምና ይፈርሳሉ። ስምጥ ሸለቆ ላይ በጣም ምርጥ መስኖ ቢሰራ ለጥቂት ሰከንዶች በሚቆይ የመሬት መንቀጥቀጥ ድባቅ ሊመታ ይችላል። ጥሩ ትውልድን ግን ሊያጠፋ የሚችል አይኖርም። ›› ብለዋል።
እንደ አቶ አባዱላ ገለፃ፤ ትውልድን በመገንባት ረገድ ውጤታማ ሥራ ሰርተዋል። በወቅቱም የነበራቸው እምነት ትውልድ ላይ መስራት ሲሆን፣ ዛሬም ያላቸው አመለካከት ይኸው ነው።
አቶ አባዱላ ገመዳ በአሁኑ ወቅት የዲቦራ ፋውንዴሽን መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ እንዲሁም የኦሮሚያ ልማት ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ሲሆኑ፣ ከሰሞኑን ስልጣን ተሰጣቸው ተብሎ እየተነገረ ያለው ነገር ግን ስህተት መሆኑን አስረድተው፤ ምንም ስልጣን እንዳልተሰጣቸውና ስልጣንም እንደማይፈልጉ ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 27/2012
አስቴር ኤልያስ