ደሎ መና:- በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ደሎ መና ወረዳ ውስጥ በሦስት ቢሊዮን ብር ወጪ 11 ሺ 40 ሄክታር መሬት የሚያለማ የወልመል መስኖ ልማት ሥራ በይፋ ተጀመረ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ፣ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለና የፌዴራል የመስኖ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሚካኤል መሃሪ ትናንት በስፍራው ተገኝተው የፕሮጀክቱን ሥራ በይፋ አስጀምረዋል።
የፌዴራል የመስኖ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሚካኤል መሃሪ ፕሮጀክቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደገለጹት፤ በፌዴራል መንግሥት ከታቀዱት ሁለት የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች መካከል 11 ሺ 40 ሄክታር መሬት ላይ የሚያለማው የወልመል ፕሮጀክት የወልመል ወንዝን በመጥለፍ የሚለማ ሲሆን፤ 22 ሺ አባወራ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል። ሁለተኛው ደግሞ በአራት ሺ 600 ሄክታር ላይ የሚለማውና ከሮቤ 170 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የጨልጨል ፕሮጀክት ነው።
ቆላማና የመልማት አቅም ባላቸው አካባቢዎች ሰፊ የመስኖ ልማት ዝርጋታዎችን የማከናወን ሥራ በመንግሥት ታቅዶ እየተከናወነ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ሚካኤል፤ እነዚህ ፕሮጀክቶች ከዚህ ቀደም ከነበሩት የተለየ ባህሪ ያላቸው፣ አገራዊ ለውጥ የሚያመጡና የተፋጠነ የመስኖ ልማትን ለማከናወን የሚያስችሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፤ በክልሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ይህ አሁን ይፋ የሆነውን ጨምሮ ለአገልግሎት የበቁት ፕሮጀክቶች ትልቅ የልማት አቅም እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።
አቶ ሽመልስ ፕሮጀክቶቹ ዝናብ ጠብቆ ከማልማት ለመላቀቅ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዙ ገልጸው፤ በዚህ ረገድ የፌዴራል መንግሥት ክልሉ ለሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች ትልቅ እገዛ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። ምርትን ወደ ገበያ ለማውጣት እንደ መንገድ ያሉ የመሰረተ ልማት ስራዎች ጎን ለጎን እንደሚከናወኑም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው፤ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ እና አንቱ የተባሉ የክልሉን ጀግኖች ስም ለማስጠራት እንዲህ ያሉ የልማት ስራዎች ወሳኝ በመሆናቸው በከፍተኛ ርብርብ ማከናወን ከህዝቡ በተለይም ከወጣቶች እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ሁሉም ወደ ልማት ፊቱን እንዲያዞር እና አካባቢውን እና አገሩን በጋራ እንዲያለማ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ የኦሮሚያ ክልል ህዝብ በልማት፣ በአብሮነት፣ በፍቅርና በመተሳሰብ የሚታወቅ እንደሆነም ገልጸዋል። ዶክተር ዐብይ መደመር፣ አብሮነት፣ ፍቅርና መተሳሰብ አንዱ ለሌላው ማሰብን፣ በጋራ ማልማትን የሚያመለክት መሆኑን ገልጸዋል።
ይፋ የሆነው ፕሮጀክት በፌዴራል መንግሥት በጀት የሚሸፈን ሲሆን በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል። የፕሮጀክት ስራውን እንዲያከናውኑም የኦሮሚያ ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝና አለማየሁ ከተማ ጄነራል ኮንስትራክሽን ለተባሉ ድርጅቶች መሰጠቱ ተጠቁሟል።
አዲስ ዘመን ጥር 27/2012
ለምለም መንግስቱ